በወያኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ አየር መንገዱ ችግር ላይ ነው፣ የህትመት ውጤቶች መሸጫ መደብር ባለቤት ታሰሩ

ከፍኖተ  ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ (ታህሳስ 3 ቀን 2009) – የወያኔ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባመጣው ቀውስ ምክንያት አየር መንገዱ ችግር ሊገጥመው ነው – የወያኔ አገዛዝን የሚተቹ መጽሀፍትና ጋዜጦችን ይሸጥ የነበረው መደብር ባለቤት ሰሞኑን ከታሰሩት መካከል አንዱ ናቸው – በፓርላማ ውስጥ ለተቃዋሚዎች ሊሰጥ የታቀደው የይስሙላ መድረክ ተቃውሞ ገጠመው በሱማሊያ ዋና ከተማ በሞቃዲሾ ወደብ የፈነዳው ቦምብ 16 ሰዎች መግደሉና 48 ሰዎች ማቁሰሉ ተነገረ #በግብጽም በአንድ አጥፍቶ ጠፊ 25 ሰዎች ሞቱ – አልበሽር በተቃዋሚው ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ ገለጹ።

የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በጫነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ተከትሎም በመጣው አጠቃላይ ቀውስ ምክንያት በወያኔ አባላትና ደጋፊዎች ቁጥጥር ስር ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ብሎምበርግ የተባለው የዜና ወኪል ገልጿል። አሜሪካና ሌሎች አገሮች ለዜጎቻቸው በሰጡት የጉዞ ማስጠንቀቂያ ምክንያትና ባጠቃላይም በአገሪቱ ውስጥ በሚገኘው አለመረጋጋት ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዘው የቱሪስት ብዛት እንዲሁም የሌሎች መንገደኞች ቁጥር እየቀነሰ የመጣ መሆኑ ይታወቃል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚጓጓዘው መንገደኛ ቁጥር መቀነስና አገሪቱ ከገጠማት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር ተዳምሮ የአየር መንገዱ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ ይችላል የሚል ግምት እየተሰጠ ነው። የኩባንያው ኃላፊዎች እስካሁን የገጠመ ችግር እንደሌለ አስረግጠው በመናገር ሁኔታውን ሊክዱ ቢሞክሩም ቱሪስቶችም ሆነ ሌሎች መንገደኞች አለስጋት መጓጓዝ የሚችሉት የፖለቲካው ችግር መፍትሄ አግኝቶ መረጋጋት ሲፈጠር ነው በማለት ሌሎች ወገኖች አስተያይታቸውን ይሰጣሉ።

በአስቸኳዩ ጊዜ አዋጁ ሽፋን የወያኔ አገዛዝ በርካታ ዜጎችን መያዝ የቀጠለ ሲሆን በቅርቡ ጃፋር የተባለው የመጽሐፍት መሸጫ መደብር ባለቤትን በቁጥጥር ስር ያዋለ መሆኑ ተነግሯል። የመጽሐፍት መሸጫው መደብር የአገዛዙ ወንጀሎችን የሚያጋልጡና የሚነቅፉ መጽህፍትና መጽሔቶች ከሚሸጡባቸው መደብሮች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል። የመደብሩ ባለቤት ለምን በቁጥጥር ስር እንደዋለ በወያኔ ባለስልጣኖች ያልተገለጸ ሲሆን ምናልባትም ወያኔን የሚነቅፉ መጽሐፍት እና ጋዜጦች በብዛት በመገኘታችው ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ወገኖች አሉ።

የወያኔ አገዛዝ ከሕዝብ የተቃጣበትን ተቃውሞ ለማርገብ መቶ በመቶ በሚቆጣጠረው ምክር ቤት ውስጥ የተቃዋሚ ድርጅቶች ተወካዮች በየሶስቱ ወሩ አንድ ጊዜ እየተገኙ ሀሳባቸውን እንዲያሰሙ የቀየሰውን ሴራ አንዳንድ የአገር ውስጥ የተቃዋሚ ድርጅቶች እየተቃወሙት ይገኛሉ። ሀሳቡን አንዳንዶቹ ተቀብለው ለመሳተፍ ዝግጁ የሚመስሉ ቢሆንም ብዙዎቹ ምርጫ ሳይካሄድ በምክር ቤት ተሳታፊ መሆን ህገ መንግስቱ እንደማይፈቅድ በመግለጽና ውሳኔ የማይሰጥበት ተሳትፎ ቲያትር ከመሆን እንደማያልፍ በመተቸት ሀሳቡን በጽኑ እየተቃወሙት ይገኛሉ።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ  የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ያዳምጡ