የውጭ ምንዛሬ ሲቀንስ የጥቁር ገበያ እንቅስቃሴ ጨመረ፣ ለቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ለምግብና ተጓዳኝ እርዳታ 900 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፣ የአሜሪካ ጉዳይ ፈፃሚ ወያኔ …

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ (ታኅሣሥ 04 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በባንክ የሚቀመጠው የውጭ ምንዛሬ ሲቀንስ የጥቁር ገበያ እንቅስቃሴ የጨመረ መሆኑ ተነገረ – በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት በኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ለሚከሰት የምግብና ተጓዳኝ እርዳታዎች 900 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ የተመድ ገለጸ  – በአዲስ አበባ የአሜሪካ መንግሥት ጉዳይ ፈጻሚ የኢንተርኔትና የሞባይል አገልግሎቶች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ የወያኔ አገዛዝን ጠየቁ – በዓለም በርካታ ጋዜጠኞችን ካሰሩ አምስት አገሮች ውስጥ የወያኔ አገዛዝ አንዱ መሆኑን ሲፒጄ አጋለጠ – ፎርየን ፖሊሲ የተባለው መጽሔት ፈይሳ ሌሊሳን በዚህ ዓመት በዓለም ጥልቅ አስተሳሰብ ካላቸው 100 ሰዎች መካከል አንዱ አድርጎ መረጠው – በታንዛኒያ የሰባት ኢትዮጵያውያን አስከሬን ወንዝ ውስጥ ተገኘ – በምርጫ የተሸነፉት የጋምቢያው ፕሬዚዳንት ሥልጣን የማይለቁ ከሆነ የጎረቤት አገሮች ወታደሮች ወደ ጋምቢያ ይገባሉ ተባለ – በምዕራብ ሳህራ የትጥቅ እንቅስቃሴ እንደገና የሚጀመርበት ሁኔታ እየታየ ነው።

ባለፉት ጥቂት ወራት በባንክ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ሲቀንስ በጥቁር ገበያ የሚካሄደው የውጭ ምንዛሬ የለውጥ እንቅስቃሴ እየጨመረ መሄዱን የአገዛዙ ደጋፊዎችን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች መረጃ እየሰጡ ይገኛሉ። በባንክ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ መጠን የቀነሰበት ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው ቢባልም ቱሪስቶች በከፍተኛ ደረጃ እየቀሩ መምጣታቸውና ወደ አገር ውስጥ በኢትዮጵያውያን የሚላከው ገንዘብ መቀነስ ዋናዎቹ ናቸው ተብለው ተጠቅሰዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ የሆቴል ባለቤቶች ኪሳራ የደረሰባቸው መሆኑንና ዕዳቸውን ለመክፈል የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳጋጠማቸው በመጥቀስ አገዛዙ ችግራቸውን እንዲያቃልላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ደብዳቤ ጽፈዋል ይባላል። በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ ለውጥ እንቅስቃሴው የጨመረውና የለውጡ መጠን ዋጋም ያደገው የአገዛዙ አባላትና ደጋፊዎች የዘረፉትን ንብረት እየሸጡና ብራቸውን ወደ ውጭ ምንዛሬ እየቀሩ ከአገር ማስወጣታቸው መሆኑም ይታወቃል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ድርጅት በሳምንታዊ መጽሄቱ ሰኞ ዕለት ባወጣው ዘገባ ለሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት ማለትም ከጥር 2009 እስከ ታኅሳስ 2010 ድረስ ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ በድርቅና በረሃብ ለሚጠቁ ወገኖች 900 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደሚያስፈልግ ገልጿል። ባጠቃላይ 9.2 የሚሆን ሕዝብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው የተገመተ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 1.5 ሚሊዮን የሚሆነው ቋሚ የሆነ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ይናገራል። 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጽናትና ነፍሰ ጡሮች አልሚ ምግብ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ድርጅቱ የተመነ ሲሆን 2.4 ሚሊዮን የሚሆኑ አባወራዎች ለከብቶቻቸው እርዳታ እንድሚያስፈልጋቸው ተገምቷል። 300 ሺ የሚሆኑ ሕጻናት በምግብ እጥረት ምክንያት የአካል ጉዳት ሊደርስባችው እንደሚችልም ተሰግቷል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ሚስተር ፒተር ቭሩማን የኢንተርኔትና የሞባይል አገልግሎት ሳይቋረጥ እንዲቀጥል የወያኔን አገዛዝ የጠየቁ መሆናቸው ተገልጿል። ጉዳይ ፈጻሚ ይህንን የተናገሩት የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት በተቋቋመበት ስነስርዓት ላይ ነው። ጉዳይ ፈጻሚው በዚሁ ንግግራቸው በአገር ውስጥ ያሉ የንግድና የሥራ ተቋሞች ሥራቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማከናወን ሆነ ከዓለም አቀፉ የንግድና የሥራ ማህበረሰብ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የኢንተርኔትና የሞባይል አገልግሎቶች መሠረታዊ ናቸው በማለት የወያኔ አገዛዝ ሁኔታውን ማመቻቸት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ሲፒጄ (CPJ) በሚል አህጽሮተ ቃል የሚጠራው የጋዜጠኞች ተከራካሪ ድርጅት ባወጣው መግለጫ በዚህ ዓመት እስከ ሕዳር 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ባለው ጊዜ በዓለም 259 ጋዜጠኞች እስር ላይ ያሉ መሆናቸውን ገልጾ የወያኔ አገዛዝ 16 እስረኞችን በማሰር ከፍተኛ ከሆኑት አምስት አሳሪዎች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጿል። በዓለም የወያኔ አገዛዝ በአሳሪነት የሚበልጡት 81 ቱርክ 81 እስረኞች በማሰር፤ ቻይና 38 እሰረኞች በማሰር፤ ግብጽ 25 እስረኞች በማሰር ግብጽ እና ሻዕቢያ 17 እስረኞች በማሰር ብቻ ናቸው። ባለፉት ሁለት ወራት በሕዝብ ላይ ከተጣለው አፋኙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ የወያኔ አገዛዝ 40 ሺ እስከ 60 ሺ የሚደርሱ ዜጎችን በእስር ቤት በማጎር አግሪቱን የዜጎች እስር ቤት አድርጓታል ተብሏል።

በመቀመጫው አሜሪካ የሆነው ፎሪየን ፖሊሲ የተባለው መጽሔት አትሌት ፈይሳ ሌሊሳን በፈረንጆቹ 2016 ዓ.ም. በዓለም ጥልቅና ከፍተኛ አስተሳሰሰብ ካላቸው 100 ሰዎች መካከል አንዱ አድርጎ መርጦታል። መጽሔቱ ለአትሌት ፈይሳ እውቅናን የሰጠው መጥፎ ሁኔታን በመጋፈጥና በማጋለጥ መመዘኛ ነው። በዓለፈው ዓመት በሪዮ ኦሎሚፒክ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ፈይሳ ሌሊሳ የዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ የስፖርቱን መድረክ ለፖሊቲካ ተቃውሞ መጠቀም የሚከለክል መሆኑን እያወቀና ከዚህ አንጻር ሊደርስበት የሚችለውን ጉዳት እየተገነዘበ በአገር ውስጥ በዜጎቹ ላይ የሚደርሰውን በድልና ግፍ ሁለት እጆቹን አጣምሮ ከፍ በማድረግ በሩጫው ማጠናቀቂያ ላይ ለዓለም ሕዝብ አሳውቋል። ይህንን መሰረት በማድረግ መጽሔቱ እውቅና ሰጥቶታል። ከአፍሪካ ሌላ እውቅና የተሰጣቸው የዚምባብይወ ፓስተር ኢቫን ማውሪሬ (Pastor Evan Mawrire) ናቸው።

ባለፈው ሳምንት በታንዛኒያ ባጋምዮ በሚባለው አካባቢ ወንዝ ላይ ተንሳፈው የተገኙት ሰባት አስከሬኖች ኢትዮጵያውን ስደተኞች መሆናቸውን የታንዛኒያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጸዋል በማለት ሲትዝን የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል። ስድስቱ አስከሬኖች የተገኙት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ሲሆን አንደኛው ደግሞ አርብ ዕለት መሆኑ ታውቋል። ማቿቹ ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 35 የሚገመት ሲሆን በምን ዓይነት መንገድ እንደሞቱና በማን እንደተገደሉ የታወቀ ነገር የለም ተብሏል። የወያኔ አስከፊ አገዛዝ በመሸሽ በተለያዩ አቅጣጫዎች አገር ጥለው የሚወጡ ወገኖች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ሲሆን በየቦታው ከአስተላላፊዎችም ሆነ ከአካባቢው ሕዝብ ከፍተኛ በደልና ስቃይ የሚደርስባቸው መሆኑ በየጊዜው መዘገቡ ይታወሳል።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ያዳምጡ