በባህርዳር ከተማ ውጥረቱ ተባብሷል፣ ኢትዮጵያዊያን በዚምባብዌ ፍርድ ቤት ቀረቡ . . .

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ታኅሣሥ 28 ቀን 2009 ዓ.ም.) – በባህር ዳር ከተማ ውጥረቱ ተባብሷል  – በዚምባብዌ እርሻ ውስጥ ተደብቀው የተገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ፍርድ ቤት ቀረቡ – በአይቮሪ ኮስት ታላላቅ ከተሞች ወታደሮች የአመጽ እንቅስቃሴ አደረጉ።

ባህር ዳር ከተማ የጸጥታ ውጥረት የቀጠለ መሆኑን ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው። በባህር ዳር በግራንድ ሆቴል አጠገብ ረቡዕ ምሽት የፈነዳው ቦምብ በሆቴሉም ሆነ በከተማው የገና በዓልን አስመልክቶ ምንም ዓይነት የሙዚቃ ዝግጅት እንዳይደረግ ለተላለፈ መመሪያ ማስጠንቀቂያ ነው የሚሉ ወገኖች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን በተለያዩ የከተማይቱ ክፍሎች ዜጎች በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች በመገደላቸው ምክንያት ከተማዋ የሰዓት ዕላፊ አዋጅ የታወጀባት አስመስሏታል። አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ ሰራተኞቹ ወደ ባህር ዳር እንዳይሄዱ ለጊዜው ያገደ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ለሚጓዙ ዜጎቹም የጉዞ ማስጠንቀቂያ በድጋሚ ሰጥቷል። በባህር ዳር የሚገኙ የወያኔው ኮማንድ ፖስት ባለስልጣኖች ሐሙስ ዕለት ሕዝቡን በመሰብሰብ የወያኔ የጸጥታ ኃይሎች በዜጎች ላይ ግድያ አልፈጸሙም በማለት ወንጀላቸውን ለመሸፋፈን ቢሞክሩም ነዋሪዎቹ ግን ሀሰት በማለት ተከራክረዋል። በተለይ የእስማኤል አህመድ ቤተ ዘመዶች እስማኤልን የገደሉት የፖሊስ መታወቂያ ያሳዩ፤ ዩነፎርም የለበሱና የታጠቁ ፖሊሶች መሆናችውን በመናገር አጋልጠዋል። በተያያዘ ዜና እንደሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ሁሉ በከተማዋ የቱሪስት እንቅስቃሴ በጣም የቀነሰ መሆኑም እየታየ ነው። ታኅሣስና ጥር ወራት በባህር ዳርና በሌሎች የሰሜን ክፍለ ሀገሮች ቱሪስቶች በብዛት የሚንቀሳቀሱበት ወሮች ሆነው ሳለ በዚህ ዓመት የቱሪስቱ ቁጥር በጣም በመቀነሱ ባለሆቴሎች የመኝታ ክፍሎችን የኪራይ ዋጋ በግማሽ ለመቀነስ ተገደዋል።

በዚምባብዌ እርሻ ውስጥ ተደብቀው ተገኝተዋል የተባሉ 34 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሐሙስ ታኅሣሥ 27 ፍርድ ቤት የቀረቡ መሆናቸውን ኒውስ ዴይ የተባለ የዚምባብዌ ጋዜጣ ገልጿል። ከፍርድ ቤቱ ሰነድ የተገኘው መረጃ ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ ታኅሣሥ 17 ቀን በአስተላላፊዎች አማካይነት ወደ ዚምባብዌ የገቡ መሆናቸውና እርሻ ውስጥ ተደብቀው እንዲቆዩ የተደረጉ መሆናቸው ይገልጻል። ፖሊስ ጥቆማ ስለደረሰው ከእርሻው ቦታ ሄዶ ሊያስራቸው ችሏል ተብሏል። ከ34 ስደተኞች መከአከል አራቱ ከ11 እስከ 12 ዓመት እድሜ ያላቸው ልጆች መሆናቸውም ተነግሯል፡ ፤ ስደተኞች እንግሊዘኛ ቋንቋ የማይችሉ በመሆናቸው አስተርጓሚ መጥቶ እስኪረዳችው ድረስ ጉዳያቸው ለጥር 11 ቀን የተቀጠረ መሆኑን ጋዜጣው ዘግቧል።

በአይቮሪ ኮስት ሶስት ታላላቅ ከተሞች ወታደሮች የደሞዝ ጭማሪ በመጠየቅ አመጽ ያካሄዱ መሆናቸው ታወቀ። አርብ ታኅሣሥ 28 ቀን ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ የአገሪቱ ሁለተኛ ከፍተኛ ከተማ በሆነችውና ቡአኬ ተብላ በምትጠራው ከተማ ተከታታይ የተኩስ ድምጽ ሲሰማ የነበረ መሆኑ ታውቋል። ዳሉዋ በሚባለው በአገሪቱ ማዕከላዊ ክፍል በሚገኘው እና በአግሪቱ ስሜን በሚገኘው ኮርሆጎ በተባለችው ከተማም ተመሳሳይ አመጾች መካሄዳችው ታውቋል። በሁሉም ቦታዎች ወታደሮች ከጦር ስፈራቸው በመውጣት ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ የከተሞቹን ቦታዎች የተቆጣጠሩመሆናቸው የተሰማ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው በመውጣት የሸሹ መሆናቸው ይነገራል። ከቡርኪና ፋሶ ወደ አይቮሪ ኮስት የሚያስገባውን መንገድም የዘጉ መሆናቸው ታውቋል። ፈረንሳይ አይቮሪ ኮስት ውስጥ ከ900 በላይ የሚሆኑ የሰላም አስከባሪ ጦር ያላት ሲሆን የአይቮሪ ኮስት መንግስት የወታደሮቹን አመጽ ለማፈን የፈረንሳይን እርዳታ መጠየቁና አለመጠየቁ አልታወቀም።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ያዳምጡ