የኢትዮጵያ ፈተናዎችና መፍትሔ መንገዶች አስተያየት

በቀለ ገሠሠ (ዶ/ር): እዚህ ላይ አንድ እዉነታን ማስጨበጥ እፈልጋለሁ። ኢትዮጵያ ያፈራቻቸዉ እጅግ በጣም ብሩህ የነበሩ ወጣቶች፤ መምህራን፤ መሃንዲሶች፤ ነርሶች፤ ዶክተሮች፤ ወዘተ ለዲሞክራሲና ለእኩልነት ሲሉ የከፈሉትን የሕይወት መስዋዕትነት ታሪክ ሲያስታዉስ ይኖራል።  ዛሬ ወደኋላ እየተመለከቱ እነዚያ ተማሪዎች ተሳስተዋል፤ እግዚአብሔርን ረሱ፤ ፀሐዩን ንጉሥ መንካት አልነበረባቸዉም፤ የባሰዉን አመጡብን፤ ወዘተ እያሉ ባለማወቅ የሚኮንኗቸዉ ወገኖች ሲያጋጥሙኝ እጅግ በጣም አድርጌ አዝናለሁኝ። እላይ እንደተጠቀሰዉ በትግሎቹ ረጅም ሂደቶች ዉስጥ አንዳንድ ስህተቶች አልተሠሩም አልተባለም። በሃይማኖት ላይ ግን ሁን ብሎ የዘመተ ትዉልድ አልነበረም። አብዛኞቹ በቤተክርስቲያን ወይም በመስጊድ ዉስጥ ተወልደዉ በመልካም ሥነ ምግባር ያደጉ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያልተለያቸዉ፤ ከራሳቸዉ በላይ ለአገራቸዉና ለህዝባቸዉ የሚያስቡና የሚቆረቆሩ ወርቅዬና ብርቅዬ ልጆች ነበሩ፤ ከወንዱም ከሴቱም። በቤተክርስቲያን አስተዳደር ላይ የነበረዉ ቅሬታ ቢኖር በጭፍን ነገሥታትን፤ መሪዎችንና መኳንንትን ብቻ እያወደሱ የተጨቆነዉን ወገን በመዘንጋታቸዉ ነበር፤ አሁንም ነዉ። ስለዚህ ታሪክ የሚገመገመዉ በወቅቱ በነበረዉ ንቃተ ሕሊና እና በተወሰደዉ የትግል እንቅስቃሴ እንጂ በዛሬ መነጽር መሆን የለበትም ብዬ አምናለሁ። ያለፈዉን እንደታሪክ እያየን፤ ከመልካም ጎኖቹ መልካም ትምህርቶች እየቀሰምን ዛሬ የተሻለዉን ወይንም ቢያንስ እኩል አስተዋጽኦ ከፍሎ አገርን ከጥፋት ማዳን እንጂ  ያለፈዉን ሁሉ እኩል እየኮነኑ ቁጭ ብሎ ማላዘንን እግዚአብሔር አይወደዉም፤ ለወገንም ለታሪክም አይበጅም። ትላንትን ለዚያዉም በተንሸዋረረ መነፅር እያዩ የትዉልዱን አባላት  እንዳሉ ለመኮነን መሞከር ከማህበረሰብ ሣይንስም አንፃር ትልቅ ስህተት ይሆናል። የዚያ ትዉልድ ተማሪዎች እኮ በኢትዮጵያ ምድር ተወልደዉ፤ ኢትዮጵያዉያን/ት ሆነዉ ኖረዉ፤ ኢትዮጵያ አለባት ብለዉ ላዩትና ላመኑበት ችግር፤ መፍትሄ ይሆናል ብለዉ ባመኑበትን አቋም ፀንተዉ ኢትዮጵያዊ/ት እንደሆኑ ነዉ የሕይወት ዋጋ የከፈሉት!  ሙሉውን ጽሁፍ ያንብቡ …