ወያኔ የሰላማዊ ትግል አስተባባሪዎችን በሽብርተኛነት ከሰሰ፣ የህዝብን ትግል አቅጣጫ ለማስቀየርም ባለሥልጣኖቹን አሳሰረ

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ (ጥር 06 ቀን 2009 ዓ.ም.) – ንግስት ይርጋና ሌሎች አምስት ተባባሪዎች በሽብረተኛነት ተከሰሱ  – የሕዝብን ድጋፍ ለማግኘት ወያኔ ባለስልጣኖችን መወንጀልና ማሰሩን ቀጥሏል – በኢትዮጵያ የሥራ አጡ ቁጥር ከፍተኛ ነው።

በጎንደር ሕዝባዊ አመጽ ወቅት ከፍተኛ የማስተባበር ስራ ስትካሄድ የነበረችው ንግስት ይርጋ እና ሌሎች አምስት ተባባሪዎች የፀረ ሽብር አዋጅ ቁ 3 ቁ 4 እና ቁ 16ን ተላልፈዋል በማለት በሽብረተኛንት ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑ ታውቋል። አፋኙ የወያኔ የጸጥታ ኃይል ላለፉት ጥቂት ወራት እነዚህን ዜጎች አስሮ በምርመራ ሲያሰቃያቸው የነበረ ሲሆን በመጨረሻ የሀሰት ክስ የመሰረተባቸው መሆኑ ተገልጿል። ፍርድ ቤቱ ጉዳያቸውን ለማየት ለ ጥር 10 2009 ቀጠሮ የሰጠ መሆኑንም ከተገኘው ዜና ማወቅ ተችሏል።

በሞት አፋፍ ያለው የወያኔ አገዛዝ ከሕዝቡ ተዕሚነነት አግኝቶ ህይወቱን ለማትረፍ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል የተባሉትን ባለስልጣኖች ከስራ ማባረርና ማስሩን የቀጠለ መሆኑ ታውቋል። ባለፉት ጥቂት ቀናት የመንግስት ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የተባሉ ግለሰቦች ከየቦታው ተይዘው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ሲታወቅ ባለፉት ሁለት ቀናት ደግሞ የቴሌኮሙኒኬሽን መስርያ ቤት የሪሶርሲንግ እና ፋሲሊቲ ክፍል አቶ አብርሃም ጓዴንና እና የንግድ ባንክ የመገናኚያ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል በማለት በቁጥትር ስር ያዋለ መሆኑን ተገልጿል። በተለያዩ ቦታዎች ሙስና ውስጥ ተዘፍቀዋል የተባሉት ለዓይነት እየተመረጡ በቁጥጥር ስር ውለዋል ቢባሉም የወያኔ ቁንጮ ባለስልጣናትና የእነሱ ተባባሪዎች በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ መዝበረው ከሀገር ማውጣታቸው በገሀድ እየታየ እርምጃ ያልተወሰደባቸው መሆኑ ይታወቃል። የወያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው በቅርቡ ለፓርላማ በሰጠው መግለጫ የከፍተኛ አመራር አባላቱ ተጠያቂ ያልሆኑት ማስረጃ ስለሌለ ነው ብሎ ማሾፉ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የሥራ አጡ በተለይም የወጣት ሥራ አጥ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁት ዜጎች እየተናገሩ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ትክክለኛ የስራ አጥ ቁጥር ለማወቅ ባይቻልም ስራ ለመስራት ከሚችለው ውስጥ ከ25 እስከ 40 ከመቶ የሚሆነው ወጣት ስራ አጥ መሆኑ ይገመታል። አንዳንዶቹ ህይወታቸውን እየሸጡ ወደ ወደ ውጭ የሚወጡ ሌሎቹም በተለይ ህጻናት ሴቶች በወያኔ ደላሎች አማካይነት ወደ አረብ አገር የሚሸጡ ቢሆንም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ወጣት ከፍተኛ ትምህርት ያጠናቀቀውም ጭምር አለስራ እየተንከራተተ መሆኑ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ተብሏል። ሕዝባዊ አመጹን ተከትሎ የወያኔ አገዛዝ ስራ አጥነትን ለማጥፋት በጀት የመደበ መሆኑን ቢገልጽም የተያዘው በጀት በአንድ በኩል ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ተግባራዊ ቢሆን እንኳ ችግሩን ሙሉ በሙሉ እንደማይቀርፍ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ያዳምጡ