በጎጃም ዳንግላ ዜጎችን የገደለና ያስገደለው ተገደለ፣ የወያኔ ሃይሎችም በባህርዳርና በቦረናም ዜጎችን ገደሉ፣ ኢትዮጵያዊያን ወደሃገር ቤት የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ ቀንሷል …

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ጥር 09 ቀን 2009 ዓ.ም.):
በጎጃም ክፍለ ሀገር በዳንግላ ዜጎችን የገደለና ያስገደለ ፖሊስና ነጋዴ ተገደለ – የወያኔ የጸጥታ ኃይሎች በባህር ዳር ዜጎችን መግደል ቀጥለዋል – በቦረና አካባቢ የወያኔ ልዩ ፖሊስ አባላት ግድያ አካሄዱ – ውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያን በባንክ በኩል የሚላከው የውጭ ምንዛሬ መቀነሱ ተነገረ – ባለፈው ሳምንት በሜዲትራኒያን ባህር በሰጠመችው ጀልባ ላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንዳለበት ታወቀ – ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ዓመት በድርቅ ልትጠቃ መሆኑን ተመድ ገለጸ – ግብጽና ደቡብ ሱዳን በወያኔ ላይ ተጽእኖ ለማድረግ ተስማሙ።

ሰኞ ጥር 8 ቀን 2009 ዓ.ም በጎጃም ክፍለ ሀገር ዳንግላ ከተማ የ03 ቀበሌ ነዋሪና ፖሊስም ነጋዴም የነበረ ግለሰብ ባልታወቁ ሰዎች የተገደለ መሆኑ ተነግሯል። ከጥቂት ወራት በፊት ሕዝባዊ እንቅስቃሴው በአካባቢው ተቀጣጥሎ በነበረበት ወቅት ከንግድ ቤቱ በራፍ ላይ የነበረውን የዳሽን ቢራ አርማ እንዲያወርድ ቢጠየቅ ፈቃደኛ ካለመሆኑም በላይ አንድ ሰው ገድሎ ወደ ወደ ባህር ዳር ሸሽቶ የነበረ መሆኑ ይታወቃል። ግለሰቡ በፈጠረው ግርግርም በርካታ ቤቶች የተቃጠሉ መሆናቸውና ንጹሃን ዜጎችም በፖሊሦች መገደላቸውም አይዘነጋም። ሁኔታው ሲረጋጋ ግለሰቡ ከሸሸበት ቦታ በመመለስ ከ70 እስከ መቶ የሚቆጠሩ ወጣቶች ያሳሰረ ሲሆን በእስር ቤት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውም ታውቋል። በግለሰቡ ድርጊት ያዘኑና በሁኔታው ብሶት ያለባቸው ዜጎች እርምጃ ወስደውበታል።

በተያያዘ ዜና በባህር ዳር ማዕከሉን ግራንድ ሆቴል ላይ ያደረገው የወያኔው ኮማንድ ፖስት የግድያ ዘመቻውን የቀጠለ መሆኑ ታውቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ምሽት ላይ እስማኤል አህመድ የተባለው ዜጋ ቤቱ ደጃፍ ላይ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ በወያኔ የጸጥታ ኃይሎች መገደሉ አብዛኛውን የባህር ዳር ነዋሪ ያሳዘናና እና ያስደነገጠ መሆኑ ይታወቃል። የዚህ የአረመኔ ቡድን የግፍ አርምጃ ቀጥሎ የወያኔ የጸጥታ ኃይል አባላት ሰኛ ጥር 8 ቀን ምሽት ላይ በቀበሌ 14 ጋጃ መስክ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ አንድ ጣውላ ቤት የሚሰራን ወጣት በጥይት ደብድበው ገድለውታል። በተመሳሳይ ጊዜም ሌላ ጠላ ቤት የምትሰራ ሴት በካራ ወግተው የሄዱ መሆናቸውን ከአካባቢው ካገኘነው ዜና ማወቅ ችለናል።

ባለፈው ሳምንት ለአምስት ተከታታይ ቀናት የወያኔ ልዩ ፖሊስ ኃይሎች በቦረና አካባቢ ባካሄዱት ወረራ 50 ሰላማዊ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከወያኔ ልዩ ፖሊስ በኩል 57 ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል። ከተገደሉት ልዩ ፖሊሶች መካከል 18 ቱ የወያኔ የመከላከያ ጦር መታወቂያ እንዳላቸው ተረጋግጧል።

ውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በባንክ በኩል ወደ አገር የሚላከው የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱ ተነገረ። ባለፉት አመታት ለአስራ ስድስት ሚሊዮን ተኩል ኢትዮጵያን ለያንዳንዱ 120 ዶላር በአመት ቢያንስ አምስት ጊዜ ሲላክ የቆየ መሆኑን የጠቆመው የዜና ምንጭ ባለፉት ስድስት ወራት የተላከው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አመላክቷል። በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ውስጥ የሚልኩት ገንዘብ ለመቀነሱ በአገሪቱ ውስጥ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ እንደዋና ምክንያት ሲጠቀስ በጥቁር ገበያ ያለው የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ከባንኩ ክፍያ በጣም መብለጡም ከምክንያቶቹ ውስጥ አንደኛው ነው ተብሏል። በአሁኑ ወቅት የወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ችግር ያጋጠመው ሲሆን የወያኔ አባሎች የዘረፉትን ገንዘብ ወደ በውጭ ምንዛሬ ከአገር ውጭ ለማስወጣት በሚያደርጉት እሽቅድምድም የአንድ ዶላር ዋጋ ወደ 30 ብር እየተጠጋ መሆኑ ይነገራል።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ጥር 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በሜዲትራኒያን ባህር ስደተኞችን የያዘች አንዲት ጀልባ ባህር ውስጥ በመስጠሟ በውስጧ የነበሩት በርካታ ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ተነግሯል። በጀልባዋ ላይ ከነበሩት 180 የሚሆኑ ስደተኞች መካከል እስካሁን ድረስ አራት ሰዎች መሞታቸው እና ሌሎች አራት ሰዎች ተርፈው ትራፓን ከተባለው በጣሊያን ሲሲሊ ወደብ የተወሰዱ መሆናችው ታውቋል። በህይወት የተረፉት ስደተኞች ለባለስልጣኖች ባደረጉት ገለጻ በጀልባዋ ላይ ከነበሩት 180 ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ የመጡ ዜጎች መሆናቸውን ገልጸዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ መሰረት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 180 ሺ ስደተኞች የሜዲትራኒያን ባህር አቋርጠው ጣሊያን የደረሱ መሆኑ የተመዘገበ ሲሆን ወደ 5000 የሚገመቱ የሞት አደጋ እንዳጋጠማችው ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ዓመት በድርቅና በረሃ እየተጠቃች ነው በማለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞ ጥር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ከናይሮቢ በሰጠው መገልጫ ገልጿል። ቀደም ብሎ እንደተገለጸው በዚህ ዓመት 5.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በረሃብና በድርቅ የሚጠቁ መሆናቸውን በማንሳት የ900 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደሚያስፈልግም ድርጅቱ ገልጿል። በሶማሊያ የተባበሩት መንግስት ድርጅት የእርዳታ አስተባባሪ የሆኑትም 3.9 ሚሊዮን የሱማሌ ዜጎች በድርቁ እንደሚጠቁ ገልጸው ለሶማሊያ ብቻ 864 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደሚያስፈግልግም ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያን ያጠቃው ድርቅ ከአምሳ ዓመት ወዲህ ከፍተኛው መሆኑ ሲገልጽ ባለፈው ዓመት ብቻ ለ18 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን 1.7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት እርዳታ ተሰጥቷቸዋል ተብሏል። በተጨማሪም የዓለም የምግብ ፕሮግራም ማክሰኞ ዕለት ከሮማ በሰጠው መግለጫ በደቡብ እና በደቡም ምስራቅ እየተከሰተ ያለው ድርቅና ረሃብ 5.6 የሚሆኑ ዜጎችን እንደሚያጠቃ ገልጹ በድርቁ ምክንያት ለሚደርሱ የከብት እልቂት የዘር እህል እጥረት የ20 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ጠይቋል።

ጥር 2 ቀን የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ግብጽን የጎበኙ መሆናችው የሚታወቅ ሲሆን ከግብጹ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር ባደረጉት ንግግር የአባይ ግድብን ለማስቆም ሁለቱ መንግስታት በአንድ ላይ ለመስራት የተስማሙ መሆኑን ኒያሚልፒዲያ የተባለ የደቡብ ሱዳን የድረገጽ ጋዜጣ እሁድ ጥር 7 ቀን ባወጣው ዕትሙ ገልጿል። በዚህ በድብቅ በተደረገው ስምምነት የኡጋንዳው ሙሰቪኒ ተባባሪ ናችው የተባለ ሲሆን ለማከናውን የታቀዱት የጋር እርምጃዎች የተለያዩ ናችው ተብሏል። ከሚወሰዱት እርምጃዎች መካከል የታጠቁና ያልታጠቁ ተቃዋሚዎችን መርዳት፤ ሕዝባዊ አመጾችን መተባበር፤ የአባይ ግድብን አስመልክቶ በዲፕሎማሲ መድረክ የወያኔ አገዛዝ እንዲገለል ማድረግ፤የሚሉ የሚገኙባቸው ሲሆን ደቡብ ሱዳን በዚህ በኩል ሙሉ በሙሉ እንድትተባበርና ግብጽም በአጸፋ ለደቡብ ሱዳን የመሳሪያና የገንዘብ እርዳታ እንዲያደርግ መስማማታቸውን ይገልጻል። የወያኔ አገዛዝ የሪክ ማቻርን ጦር መጠለያ በመስጠት ሲያጠናክረው ቆይቷል በማለት የደቡብ ሱዳን መንግስት ባለስልጣኖች በተለያዩ ጊዜያት ያነሱት በመሆኑ የአሁኑ ስምምነት አያስገርምም የሚሉ በርካታ ናችው። ስምምነቱን አስመልክቶ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣኖች ተጠየቀው በመካድም ሆነ በማመን መልስ ያልሰጡ ሲሆን አንድ የሳልቫኬር አማካሪና በአስተዳደር ስራ ላይ ሹም የሆኑ ሚስተር አብርሃም ቾል የተባሉ ሰው ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያ ስትል ጥቅሟን አሳልፋ አትሰጥም በማለት ተናግረዋል።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ያዳምጡ