ወያኔ የሀገሪቱን የውጭ ዕዳ በእጥፍ አሳደገው፣ የቱሪስቶች መቀነስም ጭስ አልባውን የምጣኔ ሃብት ዘርፍ ክፉኛ እየጎዳው ነው፣ ንግሥት ይርጋና ሌሎች ሰላማዊ ዜጎች …

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ጥር 23 ቀን 2009 ዓ.ም) – ባለፉት አምስት ዓመታት የአገሪቱ የውጭ ዕዳ በእጥፍ አደገ ተባለ – የአገር ጎብኝዎች መቀነስ የቱሪስቱን ዘርፍ ክፉኛ የጎዳው መሆኑ ተነገረ – ንግሥት ይርጋና ሌሎች ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀረቡ- የአፍሪካ ኅብረት የሞሮኮን የአባልነት ጥያቄ ተቀበለ

ባለፉት አምስት ዓመታት የአገሪቱ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ በእጥፍ ያደገ መሆኑን ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች ገለጹ። በ2004 ዓ.ም. የበጀት ዓመት 1.4 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የአገሪቱ የውጭ ዕዳ በ2007 ዓ.ም. ወደ 6.4 ቢሊዮን ዶላር ያደገ ሲሆን በ2008 ዓም ደግሞ 3.3. ቢሊዮን ዶላር የነበረ መሆኑን ምንጮቹ ይጠቅሳሉ። አገሪቱ ከምትችለው በላይ እዳ ውስጥ ከገባች ዋናውን ብድር ከመክፈል በተጨማሪ በየአመቱ ለወለድ ክፍያ ለሌሎች የባንክ አገልጎቶች የምትከፍለው ገንዘብ በጣም ከፍተኛ ስለሚሆን በኢኮኖሚው እድገትና በመጭ ትውልድ የኑሮ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል ተብሏል። በተያያዘ ዜና ሰሞኑን የወያኔው የንግድ ሚኒስቴር ለፓርላማው ባቀረበው ዘገባ ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ የተላከው የሸቀጥ መጠን እያሽቆለቆለ የሄደ መሆኑንና ከታቀደው በግማሽ የቀነሰ መሆኑ ተጠቅሷል። በዚህ ዓመት ባጠቃላይ 349 ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኝ የፋብሪካ ውጤት ወደ ውጭ ይላካል ተብሎ ታቅዶ የነበረ ሲሆን የተገኘው 198.5 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ ተገልጿል። ወደ ውጭ የሚላኩት የጥጥ የቆዳ የስጋና ሌሎች ምርቶች መጠን በከፍተኛ ደረጃ መቀነሳቸውም ተስተውሏል።

በሕዝባዊ አመጹ ወያኔ ተግባራዊ ባደረገው አፋኝ የአስቸኳይ አዋጅ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የአገር ጎብኝዎች ቁጥር እጅግ በመቀነሱ ምክንያት በዚህ ዘርፍ የሚገኘው የንግድና የሥራ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ እየተዳከመ መሆኑን ሁኔታውን የሚከታተሉ ወገኖች ገልጸዋል። በየቦታው የሚገኙ የቅርሳ ቅርስ ሱቆች ገበያቸው በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ ሲሆን አገር ጎብኝዎችን የሚያስተናግዱ ሆቴሎችና የምግብና የመዝናኚያ ቦታዎች በገበያቸው መቀነስ ምክንያት ሠራተኞችን ያባረሩ መሆናቸውና የባንክ እዳቸውን መክፈል እንዳቃጣቸው እየተናገሩ ነው። ከቱሪስት ጋር የተያያዘው የኢኮኖሚ መስክ ከ900 ሺ እስከ ሚሊዮን ለሚደርሱ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል የሰጠ መሆኑ በየጊዜው የተነገረ ሲሆን የአገር ጎብኝዎች መቀነስ ብዙዎችን ስጋት ላይ ጥሏቸዋል። ከጠቅላላ አገራዊ ገቢ (ጂዲፒ) 10 ከመቶ ድርሻ አለው የሚባለው ይኸው የቱሪዝም የኢኮኖሚ ዘርፍ መዳከሙ በኢኮሚው ላይ የሚያደርሰው ጫና ከፍተኛ እንደሚሆን የሚያከራክር አይደለም፡፡ ሕዝባዊ አመጹና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢኮኖሚው ላይ ምንም ጉዳት እንዳላመጣ የወያኔ ባለስልጣኖች ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየውን ጨምሮ በተለያየ ጊዜ ይናገሩ እንጅ ችግሩ ከፍተኛና አሳሳቢ መሆኑን የሚናገሩ ወገኖች በዚህና በሌሎች የኢኮኖሚ መስኮች የተከሰቱትን ችግሮች ለማስወገድ የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ መፍጠርን ይጠይቃል ይላሉ። ይህም ደግሞ የአንድ ቡድንን አምባገነን አገዛዝን ለአንዴም ለሁሌም ማስወገድና ሕዝቡን የመብት ባለቤት ማድረግን የሚጠይቅ መሆኑን በተጨማሪ ይገልጻሉ።

ንግሥት ይርጋና ሌሎች ተከሳሾች በዛሬው ቀን ፍርድ ቤት ቀርበው ለተከሰሱበት ክስ የመጀመሪያ የመከላከያ ማስርጃ አቅርበዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ አቃቤ ህጉ ያለውን የመከራከርያ መልስ እንዲያቀርብ ለየካቲት 7 ቀን የተቀጠረ መሆኑ ታውቋል። በተያያዘ ዜና የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ የነበረውና በቅርቡ ከወያኔ የማጎሪያ ጣቢያ የተፈታው ይድነቃችው ከበደ የሀሰት ወሬ በማውራት ክስ የተመሰረተበት መሆኑ ታውቋል። በቅሊንጦ እስር ቤት በነበረበት ወቅት “መንግሥት እስረኞችን በእሳት አቃጥሎ እናንት ለምን ዝም ብላችሁ ታያላችሁ፤ አትጮሁም ወይ? አታለቅሱም ወይ? እኛም መታገል አለብን” በማለት የሀሰት ወሬን በማውራት ለማነሳሳት ሞክሯል በሚል ተከሷል። በቀረበው ክስ መሰረት የወያኔ አገዛዝ ዜጎችን ለማሰቃየት እስከ ምን ድረስ እንደሚሄድና ምን ያህል ዝቅ እንዳለ ያሳያል ተብሏል።

የአፍሪካ ህብረት የሞሮኮን የአባልነት ጥያቄ ተቀብሎ በድጋሚ አባል ያደረጋት መሆኑ ተነግሯል። ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያ፣ ዚምባብዌ እና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሞሮኮ በአፍሪካ ህብረት ውስጥ በድጋሚ አባል ልትሆን የምትችለው የምዕራብ ሳህራ ግዛት ህልውናን ከተቀበለች ብቻ ነው የሚል መከራከሪያ ቢያቀርቡም ተቀባይነት ስላላገኙ ሞሮኮ በድጋሚ አባል መሆን ችላለች። የሞሮኮው ንጉሥ መሀመድ በስበብሰባው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን ሞሮኮ በአፍሪካ ህብረት ውስጥ ለመግባት የፈለገችው ድርጅቱን ለመክፈል ሳይሆን ለመጥቀም ነው ብለዋል፡፡

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ያዳምጡ