የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዴልሂ አውሮፕላን ጣቢያ በድንገት ተገዶ አረፈ

የወያኔ ቡድን ኮንትራት የሚሰጧቸው ኩባንያዎች በርካታ ገንዘብ መዝረፋቸው እየተጋለጠ – የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዴሊሂ አውሮፕላን ጣቢያ በድንገት ተገዶ አረፈ – የወያኔ ጥልቅ ተሃድሶ ወደ ፍርድ ቤት በመዛመቱ ዜጎች እየተቸገሩ መሆናቸው ተነገረ – በደቡብ አፍሪካ ጸረ ስደተኛው ሰልፍ ቀጥሏል።

የበረራው ቁጥር ኢቲ 8806 የሆነውና ከሙምባይ ወደ ካትማንዱ ሲበር የነብረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በዛሬው ቀን በህንድ ዴሊሂ አውሮፕላን ማረፊያ በአስቸኳይ ተገዶ አርፏል። አውሮፕላን ውስጥ የነበሩት 245 መንገደኞችና 10 የአውሮፕላኑ ሰራተኞች ምንም ጉዳት ያልደረሰባቸው ሲሆን ለአውሮፕላኑም ተገዶ ማረፍ የቴክኒክ ጉድለት ነው የሚል ምክንያት ተሰጥቷል።

የወያኔ ቡድን ባለስልጣኖች ለተለያዩ የልማት ግምባታ በኮንትራክት ከሚሰጧቸው ከተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር የጥቅም ክፍፍል ያላቸው መሆኑ በተደጋጋሚ የተገለጠ ሲሆን የሚዘረፈው የመንግስት ገንዘብ መጠን ምን ያህል ግዙፍ መሆኑን ተጋልጠው እጅ ከፍንጅ ከተያዙ ኩባንያዎች ሁኔታ መረዳት ይቻላል ተብሏል። ትድሃር ኮንስትራክሽን የሚባለው ኩባንያ ለአዲስ አበባ የመንገዶች ባለስልጣን መመለስ የነበረበትን 137 ሚሊዮን ብር ሳይመልስ መቅረቱ በሂሳብ አጣሪዎች የተጋለጠ መሆኑን የወያኔ የዜና ማሰረጫ ዘግቦታል። ኩባንያው በመንግስት ክፍያ የተደረገባችውን መኪናዎችና ሌሎች ለመንገድ ስራ የሚያገልግሉ ተሽከርካሪዎችን ከቦታው በመውሰድ የሰወረ ሲሆን እንዲሁም ሌሎች ለመንግስት መሰጠት ያለበትን ክፍያ ያላጠናቀቀ መሆኑ ተገልጿል።

የወያኔ አገዛዝ በየቦታው እያካሄደ ያለው ጥልቅ ተሃድሶ ወደ ፍርድ ቤቶችም በመዛመቱ ባለጉዳዮች እየተጉላሉ መሆናችውን አንዳንድ ምንጮች ገለጹ። ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ ውስጥ በአንዳንዳንድ ቦታ ዳኞች በችሎት አዳራሾቻቸው ውስጥ ቀኑን ሙሉ እንዲሰበሰቡና ጥልቅ ተሃድሶ እንዲወስዱ በመደረጉና ለመታየት ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበሩ የክስ ጉዳዮች በመሰረዛቸው በርካታ ባለጉዳዮች መጉላላታቸውና ከፍተኛ ችግር የደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል። መታየት የነበረባቸው ጉዳዮች ከአንድ ወር በላይ ቀጠሮ በመስጠት እንዲዛወሩ በመደረጉ ፍርድ የሚያስፈልጋቸው ክሶች ካለመጠን እንዲከማቹ ተድርጓል ተብሏል። በአሁኑ ወቅት የወያኔ ስልጠና እየተካሄደ ያለው በተወሰኑ ፍርድ ቤቶች ሲሆን ሁሉም በተራ እንደሚደርሳቸው ይነገራል። ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ ዳኞች የወያኔ አባላትና አገልጋዮች ከመሆናቸውም በላይ በመመሪያ የሚሰሩ በመሆናቸው ህዝብ እንዲጉላላ ከማድረግ በስተቀር ተሃድሶው የሚፈይደው ነገር የለም የሚሉ ብዙ ናችው።

አርብ የካቲት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ጸረ ስደተኛ የሆነው ሰልፍ በደቡብ አፍሪካ ዋና ከተማ በፕሪቶሪያ ቀጥሎ የዋለ ሲሆን ፖሊስ በአስለቃሽ ጋዝና በውሃ ግፊት ሰልፉን ለመበተን ጥሯል። ለሁለት ቀናት በተደረገው ስልፍ ከ 130 በላይ ሰዎች መታሰራቸው ተነግሯል። የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ሌሎች ህዝባዊ ተቋማት መንግስት እንዲህ ዓይነቱን የጥላቻ ሰልፍ መፍቀድ አልነበረበትም በማለት ወቀሳቸውን ያሰሙ ሲሆን ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ አድርገዋል። የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከአፍሪካ አገሮች ወደ አውሮፓ ከሚሰደዱት ይልቅ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚገቡት በቁጥር የሚበልጡ መሆናቸውን ገልጸው አብዛኞቹ ስደተኞች ሰላማዊና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛአ አስተዋጾ በማድረግ ላይ ያሉ ስለሆነ ሁሉንም ስደተኛ አደንዛዥ እጽ የሚሸጥ ወይም ህገ ወጥ የሰው ልጅ አስተላላፊ ብሎ መሰየም አይቻልም ብለዋል። ከዚህ በፊት በደቡብ አፍሪካ በተደጋጋሚ በርካታ በርካታ ስደተቾም መገደላቸውና አካላዊ ጉዳት የደረሰባችው ሲሆን ከ፤እነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያውያን ሶማሊዎች ይገኙባቸዋል።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ያዳምጡ