የወያኔ ባለሥልጣኖች ሆቴል ግንባታ፣ በአዲስ አበባ ቆሻሻ ክምር ተንዶ ሰዎች አለቁ …

ፍኖተ ዴሞክራሲ ሬዲዮ (መጋቢት 05 ቀን 2009 ዓ.ም. ) – የወያኔ ባለሥልጣኖች የታላላቅ ሆቴሎች ባለቤቶች መሆናቸው ተጋለጠ – ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰ የቆሻሻ ክምር መደርመስ የሞቱት ሰዎች ቁጥር እያደገ መሄዱ ታወቀ – ባለፈው ዓመት የሳኡዲ መንግሥት ወደ ዘጠና ሺ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ከአገሩ አባሯል – ጋዜጠኛ አናኒያ ሶሪ ተፈታ።

የወያኔ ባለስልጣኖች በጀርባ የተለያዩ የንግድና የኢንዱስትሪ ተቋሞች ባሌበቶች መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እየተስፉፉ በመሄድ ላይ የሚገኙትን ታላላቅ ሆቴሎች እየተቆጣጠሩ መሆናቸውን ኢንዲያን ኦሽን ኒውስ ሌተር የተባለው ሳምንታዊ መጽሔት አጋልጧል። ኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል በሚል ስም በካዛንችስ የተገነባው ሆቴል ባለቤት ገምሹ በየነ የሚባል ቢሆንም በጀርባ በኩል በሸርክና ሆቴሉን የሚያካሂደው አባ ዱላ ገመዳ መሆኑን ጠቅሷል። በቅርቡ 130 ሺ ዶላር ወጭ ሆነበት በአያት ሪል ስቴት ተይዞ የነበረ 1500 ካሬ ሜትር ቦታ ለኤሊሊ ኢንተርሽናል በማን አለብኝነት የተሰጠ ሲሆን የአያት ባለቤት አያሌው ተሰማ ቦታውን ለማስመለስ በፍርድ ቤት ያልተሳካለት ከመሆኑ በላይ እስከናካቴውም ያጭበረበርከው የታክስ ዕዳ አለብህ በሚል ክስ ወደ እስር ቤት የተወረወረ መሆኑ ይታወቃል። ገምሹ በየነ ከአባዱላ ጋር በመሆን በባግያ ሃይቅና በሌሎች ቦታዎች ሆቴሎችን ለመስራት እቅድ ይዞ ይገኛል። በቅርቡ 9 ሚሊዮን ዶላር ወጥቶበት በቦሌ አጠገብ የተሰራው አዚማን የተባለው ሆቴል ስሙ በአንድ በቀድሞ የኢህአዴግ አባል ቢሆንም የአብዛኛው የአክሲዮን ባለቤት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መሆኑን ጋዘጣው ጠቁሟል። በጎንደርም በ3 ሚሊዮን ዶላር የተሰራው ላንድማርክ የተባለው ሆቴል ደግሞ በጀርመርንና በአሜሪካ ሲኖር የነበረው ነጋ አዲሱ በይፋ ባሌቤት ነው ቢባልም በረከት ስምኦን ከፍ ያለ ድርሻ እንዳለው ይነገራል። የበረከት ሚስት አሰፉ ፋንቴ እና ወንድሟ መዝሙር ፋንቴም በባህር ዳር የሚገኘው የራህኔ ሆቴል ባለቤቶች ናቸው ተብሏል።

ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በደረሰው የቆሻሻ ክምር መደርመስ ምክንያት በጠቅላላው የሞቱት ሰዎች ቁጥር እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን እስከዛሬ 72 አስከሬኖች የተገኙ መሆናቸውን አንዳንድ ምንጮች ገለጸዋል። ቁጥሩ በየቀኑ እየጨመረ እንደሚሄድም ተገምቷል። የሟቾቹ ዘመዶች በተድረመሰው ክምር የተቀበሩትን ዜጎች ለማውጣት የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣኖች ያደረጉት ጥረት አነሰተኛ መሆኑን ገልጸው አብዛኛውን ሥራ ራሳቸው በእጃቸው ጭምር በመቆፈር ያከናውኑት መሆናቸውን ገልጸዋል። በአገዛዙ አማካይነት በፍለጋው ላይ የተሰማሩት ሰዎች እያካሄዱ ያሉት ሥራ ለገምተኛ ነው በሚል የሟቾቹ ቤተሰቦችን ንዴትና ብስጭት እያሳዩ በመሆናቸው አገዛዙ በቦታው ላይ የፖሊስ ኃይል ማሰማራቱም ታውቋል። አስከሬናቸው የተገኘው ዜጎች በትናንትናው እና በዛሬው ዕለት የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈጽሞላቸዋል። የቆሻሻ ክምሩ አደገኛ መሆኑን በተደጋጋሚ ለባለስልጣኖች የተናገሩ መሆናቸውን የሚገልጹ ዜጎች አገዛዙ ምን ዓይነት እርምጃ ያልወሰደ መሆኑን ተናገረዋል። የቆሻሻ ክምሩን ከሚችለው በላይ በጥቅም ላይ እንዲውል በማድረጉና ዜጎች ለደህነነታቸው አደገኛ በሆነ አካባቢ እንዲኖሩ በማድረጉ አገዛዙ ከተጠያቂነት አያመልጥም በማለት የሰብአዊ መብት ተከርካራ የሆነው ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ አውጥቷል።

ባለፈው ዓመት የሳኡዲ መንግስት 89 800 ኢትዮጵያውያንን ከአገሩ ያባረረ መሆኑን ይፋ ባደረገው ዘገባ ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪም 2897 ኢትዮጵያውያን በወንጀል የተከሰሱ መሆናቸውን ጠቅሷል። ለኢትዮጵያን መብት ተከራካሪ መሆን የነበረበት ሪያድ የሚገኘው የወያኔው አገዛዝ ቆንስላ ባሰራጨው ደብዳቤ ኢትዮጵያውያን አርፈው እንዲቀመጡ ጥሪ አስተላልፏል። የወያኔ አገዛዝ በሕዝብ ላይ በሚያደርሰው በደል በመማረርና በኑሮ ሁኔታ ችግር አገራቸውን ጥለው ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚሰደዱ ኢትዮጵያን ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ በጣም እየጨመረ መሄዱ የሚታወቅ ሲሆን በተለይ በአረብ አገሮች የሚደርስባቸው ኢሰብአዊ የሆነ በደልና ግፍ በየጊዜው መገለጹ ይታወቃል። ኢትዮጵያውያን ከመሰደድ የሚገደዱበትን ሁኔታ ለማስቀረትና የሚደርስባቸውን በደልና ግፍ ለማስቆም የሚቻለው አገዛዙ ሲወገድ ብቻ ነው የሚሉ በርካታ ናቸው።

አናኒያ ሶሪ የተባለው ጋዜጠኛ በትናንትናው ዕለት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ተፈቷል። አናኒያ የተያዘው ህዳር 8 ቀን 2009 ዓም. ሲሆን ላለፉት አራት ወራት አንድም ክስ ሳይመሰርትበት ቆይቷል። በዚህ ዓመት አለምንም ጥፋት ተይዘው ክስ ሳይመሰርትባቸው በእስር ቤት ተሰቃይተው ከወጡት ጋዜጠኞች መክካከል ከስዩም ተሸሞ እና ከበፈቃዱ ኃይሉ ቀጥሎ አናኒያ ሶስተኛ መሆኑ ነው።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ያንብቡ