በኢትዮጵያ የተቅማጥ በሽታ እየተስፋፋ ነው

  • ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ  አንድነት ድምጽ  (መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም.) – የጋምቤላው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ፍርድ ቤት ቀረበ – በስዊድን ዜጎች ተዘጋጅቶ በይፋ የተሰራጨው ዶክመንተሪ ፊልም ትኩረት እያገኘ መሆኑ ታወቀ – ወያኔ በርካታ ጋዜጠኞችን ማሰሩ ተጋለጠ – በኢትዮጵያ የተቅማጥ በሽታ እየተስፋፋ መሆኑ ተመድ አጋለጠ  – በአዲስ አበባ 85 ከመቶ የሚሆነው ሕዝብ የመጠጥ ውሃ አያገኝም ተባለ – የወያኔ አገዛዝ ከሶማሊያ ወታደሮቹን በድንገት አስወጣ።

የጋምቤላው የሰባዊ መብት ተማጓችና የአካባቢ ድህንነት ጠበቃ አሞት አጓ ፍርድ ቤት መቅረቡ ተነገረ። ወያኔ ለትርፍ ሲል የጋምቤላን መሬትና ደን ለባዕዳን መሸጡና አካባቢውን መጉዳቱ የሚታወቅ ነው ያሉ ዘጋቢዎች የጋምቤላ ባለስልጣኖች ክ269 ተኮናታሪዎች ምንም አልሰሩበትም በሚል መሬት መንጠቃቸውንም ዘግብዋል። በጋምቤላ መሬት ግዢ ላይ በስፋት ተሰማርተው የቆዩት ከውጭ ሀገር የመጡና የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውም የሚታወቅ ነው ተብሏል ። በመላ ኢትዮጵያ ከ 2 ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ከመሬቱ መፈናቀሉን ጫና ሰጥተው የገለጹ ክፍሎች ከሺ ያላነሱ ተጨፈጨፉ በኋላ ወያኔ ጋምቤላን ለበለጥ ጥፋት መዳረጉን አጋልጠዋል። ይህ በዚህ እንዳለ በጋምቤላ በዲማ ወረዳ በእርሻ የተሰማራ ባለህብት ልጅ የሆነው አማኑ ኢታፋ ከጫካ በመጡ ታጣቂዎችም መገደሉም ተዘግቧል።

በስዊድን ዜጎች ተዘጋጅቶ ባለፉት ጥቂት ቀናት በይፋ የተሰራጨውና በኢትዮጵያ የተካሄደውን የመሬት ንጥቂያ የሚያጋልጠው ዶኩመንተሪ ፊልም ሰፊ ትኩረት እያገኘ መሆኑ ተነገረ። ዶኩመንተሪ ፊልሙ በኢትዮጵያው ውስጥ የተካሄደው የመሬት ንጥቂያ በዜጎች ላይ ያስከተለውን ረሃብ፤ መፈናቀልና ስደት ከማጋለጡም በላይ የአለም ባንክን በቀጥታ ተጠያቂ ያደርጋል። ፊልሙን ያቀነባበሩት ስዊድናዊ ባደረጉት ገለጻ በአዳጊ አገሮች መሬትን መንጠቅ የተጀመረው ከአስራ አመት በፊት መሆኑን አስረድተው በአዲስ አበባ አውሮፕላን ጣቢያ በአንድ በኩል ከረጅዎች የተሰጠ የእርዳታ እህል ከአውሮፕላን ላይ ሲራገፍ በአዩበት ዓይን በሌላ በኩል በውጭ ከበርቴዎች በተነጠቁ መሬቶች ላይ የተመረቱ የሩዝ ምርቶች ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ ለመላክ በአውሮፕላን ላይ ሲጫኑ ማየታቸው ያሳዘናቸው መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የመሬት ንጥቂያው የተካሄደው ያለሕዝቡ ፍላጎትና ይሁንታ መሆኑና ካሳ ሳይከፈል የተካሄደ ንጥቂያ መሆኑ ዶኩመንተር ፊልሙ ከመጠቆሙ በላይ የሼክ አላሙዲ ንብረት የሆነውን የሳኡዲ ስታር የሩዝ እርሻን እንደማስረጃ ያቀርባል። የዓለም ባንክ ሁኔታውን በማመቻቸትና ለነጣቂዎቹ ብድር በመስጠት በኩል የመሬት ንጥቂያው ተባባሪ መሆኑንም ያጋልጣል።

ዘለዓለም ወርቅ አገኘሁ የተባለ ጋዜጠኛና ዘጋቢ (ብሎገር) ለእስር ከተዳረገ ሶስት ዓመት ሊሆነው ነው ብለው ያስታወሱ ክፍሎች ወያኔ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አመካኝቶ በርካታ ጋዜጠኞችን ማሰሩን አጋልጠዋል። አዋጁ ብዙ ሺዎችን ለእስር ቢዳርግም የፈለገውን ግብ ሊያገኝ አለመቻሉን የአዋጁን ዕድሜ በአራት ወር በመቀጠል ወያኔ አምኗል። አዋጁ ደህንነትና መረጋጋት የሚሉትን የሚመለከት ነው ቢሉም ስለ መቀጠሉ መግለጫው ራሱን መከላከያ ሚኒስቴር ነኝ ክሚለው የወያኔ ቡችላ መቅረቡ አነጋጋሪ መሆኑም ተጠቁሟል። መከላከያ ሰራዊት ሀገሪቷን ከውጭ ጥቃት ጠባቂ እንጂ በሀገር ውስጥ ሕዝብን አፋኝ ሊሆን አይገባም ብለው የጠቆሙት ክፍሎች ብረት አንስተው የሚታገሉትን ዜጎች ሊያሸንፍ አለመቻሉንም ጠቁመዋል። በተያያዘ ዜና የጠላይ ሚኒስቴሩን የስራ ድርሻ እነ ሳሞራ ዩኒስ እየወሰዱት ነው በተባለው መሰረት ሳሞራ የውጭ ሀገሮችን አምባሳደሮች ተቀባይ ሆኖ ታይቷል። በወያኔ ሁኔታ ግራ የተጋቡትና ስጋት የዋጣቸው የአሜሪካ የጦርና የስለላ ተቋሞች ወያኔ ተቅዋሚ የተባሉትን ደልሎ ሊያግባባና የጋለውን ሁኔታ ሊያበርድ የማይችል ከሆነው ጄኔራሎቹ ስልጣን እንዲይዙ መገፋፋታቸው የማይቀር ነው ብለዋል። ይህ አቋም ለኤርትራም ተይዟል የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

የተባበሩት መንግስታት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ጉዳይ ተቋም በቅርቡ ባወጣው ዘገባ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ከ 3000 በላይ ዜጎች በተላላፊ የተቅማጥ በሽታ እንዲሚሰቃዩና ከነዚሁ ውስጥ ቢያስንስ ስምንት ሰዎች እንደሞቱ ገልጿል። ዘገባው በተጨማሪም ከ 465 ሺ ሰዎች በላይ በሚያሳክክ በሽታ የሚሰቃዩ መሆናቸውንና እርዳታ እንዳልደረሰቻው አውስቷል።

በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው በሚል የሚዋሽለት የወያኔ ኤኮኖሚ ዕድገት ልብ ወለድ መሆኑን ያለው ረሃብ፤ ኪሳራና የተስፋፋ ድህነት ያጋልጣል ያሉ ክፍሎች በአዲስ አበባ ራሱ 85 በመቶ በላይ ሕዝብ የሚጠጣው ውሃ አያገኝም ከማለታቸው ባሻገር የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው እንዲሉ በጠቅላላ በሀገሪቷም ቢሆን ወደ 70 በመቶ ሕዝብ በንጹህ ውሃ እጥረት የሚሰቃይ መሆኑን አጋልጠዋል። በርካታ ግድቦችም ተሰርተው ግልጋሎት መስጠት ጀምረዋል ቢባልም የመብራት ሀይል እጥረት ከፍተኛና የምርት ስምሪትንም እያደናቀፈ መሆኑ ሊታወቅ ከቻለም ጊዜ አልፏል ተብሏል። ወያኔ በቅርቡ ለታንዛኒያ መብራት ሀይል ሊሸጥ መነሳቱም ሲዘገብ የግልገል ግቤ 3 ስራ ተጠናቆ ሳያልቅ የግልገል ግቤ 4ን ኮንትራት ለተለመደው ለሳሊኒ ኩባንያ ሰጥቶ ስራ መጀምሩም ተገልጿል። በዚህም በዚያም ግን የወያኔ የተሓድሶ እቅድና ምኞት መክሸፉን ታዛቢዎች አስምረውበት አቅርበዋል።

የወያኔ አገዛዝ ወታደሮቹን ኤልቡር ከተባለችው የሶማሊያ ከተማ በድንገት በማስወጣቱ ምክንያት በጥቂት ጊዜ ውስጥ አልሸባብ ከተማዋን የተቆጣጠራት መሆኑ ታውቋል። ወያኔ ወታደሮችን በድንገት ያስወጣበት ምክንያት በውል ያልታወቀ ቢሆንም በአገር ውስጥ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት እንደሆነ ብዙዎቹ ግምታቸውን ይሰጣሉ። የአልሸባብ ቃል አቀባይ ከተማው በአልሸባብ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መውደቋን አረጋግጧል።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ያዳምጡ