የወያኔ አገዛዝ ለአማላጆች የሚከፍለው ወጭ ከፍተኛ ነው

ከፍኖተ ሬዲዮ (ሚያዚያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም.) – ለሎቢ ከፍተኛ ወጭ ከሚያወጡ የአፍሪካ ገዥዎች መካከል የወያኔ አገዛዝ ከፍተኛ ነው ተባለ – በቅርቡ የወጣው የአፍሪካ ሀብት ሪፖርት በኢትዮጵያ የሚሊዮነሮች ብዛት 3100 የደረሰ መሆኑን ገለጸ – የተመድ የሰብአዊ መብት ተቋም ኃላፊ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ነው – የወያኔው ልዩ ፖሊሲ በወሰን አካባቢ በሶማሌ ዜጎች ላይ በደል ፈጸመ::

ለሎቢ (ለአማላጅ) ኩባንያዎች ከፍተኛ ገቢ ከሚያወጡ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ከመጀመሪያዋ ተርታ መሆኗን አንድ ጥናት ገለጸ። የወያኔ አገዛዝ በዓመት አንድ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺ ዶላር በአሜሪካን አገር ለሚገኙ የሎቢ (የአማላጅ) ኩባንያዎች ይከፍላል የተባለ ሲሆን ይኽም ግብጽ ከምትከፍለው ጋር ተመጣጣኝ በመሆን ከአፍሪካ ከፍተኛው ነው ተብሏል። የወያኔ አገዛዝ ለምዕራብ አገሮች ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ለወያኔ አምባገነን አገዛዝ የሚሰጠው ድጋፍ እንዲቀጥል ለአማላጆች (ለሎቢስቶች) የሚከፍለው ገንዘብ የኢትዮጵያ ሕዝብን አንጡራ ሀብት እየጎዳ ነው ተብሏል።

በቅርቡ የወጣው የአፍሪካ ሀብት ሪፖርት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሚሊየነሮች ብዛት 3100 የደረሰ መሆኑን ጠቅሶ በአፍሪካ ውስጥ ሚሊዮነር በብዛት ከሚኖሩባቸው 10 የአፍሪካ አገሮች መካከል አንዱ አንድርጎ አስቀምጧታል። በርካታ ሀብታም ነጮች ባሉባት በደቡብ አፍሪካ 40 400 ሚሊየነር ግለሰቦች ያሉ መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን ኬኒያም 9400 ሚሊየኖርች ይኖሩባታል ተብሏል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሚሊየኖሮች ብዛት ከፍተኛ እድገት አስመዝግባለች የተባለችው ኢትዮጵያ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2006 እስከ 20126 ባለው ጊዜ የሚሊየኖሩቹ ቁጥር ውስጥ በ 219 ከመቶ አድጓል ተብሏል። አብዛኞቹ ሚሊዮነሮች ከአንድ አካባቢ የመጡት የወያኔ አባሎች መሆናቸው የሚገመት ሲሆን አማካይ የነፍስ ወከብ ገቢው በአመት ከአንድ ሺ ዶላር ብቻ ነው በሚባልበትና እንዲሁም ከ30 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በቀን 1 ዶላር በማግኘት ከድህነት በታች ባለ ሁኔታ በሚኖርበት አገር ውስጥ ይህን ያህል ሚሊየነር መኖሩና ቁጥሩም ከፍተኛ እድገት እያገኘ መሄዱ አስገራሚ ነው ተብሏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኃላፊ ከሚያዝያ 24 ቀን 2009 እስከ ሚያዚያ 26 ቀን ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙና ከወያኔ ባለስልጣኖች ጋር ተገናኝተው ስለሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳይ እንደሚነጋገሩ ተገልጿል። የተመድ የሰብአዊ መብት ኃላፊ በምን በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩ አስቀድሞ የተገለጸ ነገር ባይኖርም በሕዝባዊ አመጽ ወቅት በወያኔ የአግአዚ ጦርና በፌዴራል ፖሊስ የጸጥታ ኃይሎች በግፍ ስለተገደሉት ዜጎች ጉዳይ ዓለማቀፋዊ ነጻና ገለልተኛ ተቋም ያጥናው የሚለውን የተመድና የአውሮፓው ኅብረት ጥያቄን ያነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። የተመድ የሰብዓዊ መብት ኃላፊ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣኖች ጋር የሚነጋገሩ መሆናቸውም ተገልጿል።

የወያኔው ልዮ ፖሊስ በሶማሊያ ወሰን አካባቢ ሰፍረው የነበሩትን የሶማሊያ ተወላጆች ከፍተኛ ግፍ የፈጸመባቸው መሆኑን የዜና ምንጮች አጋልጠዋል። የግድያ ወንጀሎችን ከመፈጸማቸው በተጨማሪ ሴቶችን አስገድደው ስብእናቸውን የመድፈር ወንጀል ፈጽመዋል ተብሏል። የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣኖች ስለጉዳዩ የሰጡት የእምነት የክህደት ቃል ባይኖርም የአካባቢው ነዋሪዎች ግን በደል እንደደረሰባቸው ዘርዝረው ተናግረዋል። የኬኒያ መንግስትም ጌዶ በተባለ የሶማሌ ግዛት መንደሮች በአውሮፕላን በመደብደብ ጉዳት ያደረሰ መሆኑም ተገልጿል። የኬኒያ ወታደራዊ ባለስልጣኖች ድርጊቱ መፈጸሙን ቢክዱም የአይን እማኞች ግን ለቦምቡ ድብደባ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ የነበረው የጌታቸው ሽፈራው ጉዳይ በዛሬው ቀን ብይን ያገኛል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ብይን ሳይሰጠው ለሌላ ጊዜ የተላለፈ መሆኑ ታውቋል። ለመከላከያ የሰጠው ቃል አልተገለበጠም በሚል ምክንያት ዳኞቹ ለግንቦት 16 ቀን ቀጠሮ የሰጡ መሆኑ ታውቋል።

ለዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ያዳምጡ