ህዝባዊ አመጽ ዳግመኛ

(የፍኖተ ዴሞክራሲ ዜናና ኃተታ) – ነዋሪዎችን ያነጋገረ አንድ የውጭ አገር ጋዘጠኛ ሕዝባዊ አመጽ ዳግመኛ ሊከሰት እንደሚችል ዘገበ – የበቆሎ ምርት ጨራሽ የሆነውን የተምች ትል ለመቆጣጠር አለመቻሉ አሳሳቢ ሆኗል – ኬኒያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ታሰሩ – አልሸባብ በሶማሊያ ፑንትላንድ ግዛት በአፍርካ ህብረት ጦር ሰፈር ላይ ጥቃት አካሂዶ ጉዳት አደረሰ።

ኤ.ኤፍ.ፒ የተባለው የፈረንሳይ የዜና ወኪል ጋዜጠኛ የአምቦ ወጣቶችንና ሌሌች ነዋሪዎችን አነጋገሮ ባጠናከረው ዘገባ አምቦ ውስጥ ሌላ ሕዝባዊ አመጽ ሊከሰት እንደሚችል ዘግቧል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በርካታ ወጣቶች በመታሰራቸው ምክንያት ተጀምሮ የነበረው የአመጽ እንቅስቃሴ ለጊዜው ቢቋረጥም በነዋሪው ላይ ያለው ንዴትና ብሶት ከፍተኛ በመሆኑ በማናቸውም ጊዜ አመጽ ሊነሳ የሚችል መሆኑን ይጠቁማል ብሏል። ጋዜጠኛ ጨምሮ እንደዘገበው ምንም እንኳ ባሁኑ ወቅት ብዙዎቹ ወጣቶች በፍርሃት ውስጥ ቢሆኑም አልፎ አልፎ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መኖሩንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ ከፍተኛ ሕዝባዊ አመጽ ሊገነፍል እንደሚችል የገለጹለት መሆኑን ጠቁሟል። ባሁኑ ወቅት ተሰብስቦ መነጋገር እንደማይቻል፤ በአንድ ላይ መሄድ እንደሚያሳስር፤ አገዛዙ በዩነቨርስቲዎችና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች አገዛዙ ሰላዮችን አሰርጎ ማስገባቱንና በጥቆማ የሚያስር መሆኑን፤ የታስሩ ወጣቶች ጓደኞቻቸውን እንዲጠቁሙ የሚያስገድዷቸው መሆኑን፤ በየቤቱ የተቃውዋሚ ራዲዮኖችና የተሌቪዥን ጣቢያዎች ይተላለፉበታል የተባሉ የሳተላይት ዲሾችን የጸጥታ ኃይሎች ጣሪያ ላይ ወጥተው እንደሚፈተሹና እነዚህን ጣቢያዎች ሲያዳምጥ የተገኘ እስከ 50 ሺ ብር እንደሚቀጣ፤ ዘርዝረው የነገሩት መሆኑን ዘግቧል። በነዋሪው ሕዝብ ልብ ውስጡ እየተባላላ ያለው ብሶት እንደተዳፈነ እሳት ነው በማለት ነዋሪዎቹ የተናገሩትን ጠቅሶ አገዛዙ ሁሉን አረጋግቻለሁ ቢልም አመጽ ሊፈነዳ እንደሚችል ጠቁሟል።

የወያኔ የእርሻ ሚኒስቴር ባለሥልጣኖች ና የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ሰራተኞች ረቡዕ ግንቦት 30 ቀን በሰጡት መግለጫ የበቆሎ ምርት ጨራሽ የሆነው የተምች ትል በስፋት እየተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል። ተምቹ እስካሁን በ 52 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የበቀለውን የበቆለ ምርት የጨረሰ ሲሆን በጋምቤላ፤ በኦሮሞና በደቡብ አካባቢዎች ባሉ 144 ወረዳዎች ውስጥ ባጭር ጊዜ ውስጥ የተስፋፋ መሆኑ ተጠቅሷል። ሞቃትና ርጥብ የሆነው የአየር ንብረት ለትሉ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን እንድ የተምች መንጋ በንፋስ ኃይል እየተረዳ ባጭር ጊዜ ውስጥ እስከ 500 ኪሎሜትር ድርስ ሊስፋፋ እንደሚችል ተጠቁሟል። በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ወደ አፋር፤ አማራ፤ ቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ትግራይ አካባቢዎች ሊዛመት እንድሚችልም ተገልጿል። ባለስልጣኖቹ የተምቹ አደጋ ለረዥም ጊዜ ሊቆይ የሚችል ክስተት ነው ማለታችው መፍትሄው ቀላል እንዳልሆኑ ይጠቁማል ተብሏል።

ኬኒያ ውስጥ ካዮሌ በሚባለው ቦታ በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ገብታችኋል የተባሉ 40 ኢትዮጵያውያንን በእስር ላይ መሆናችውን ዘ ስታር የተባለው የኬኒያ ጋዜጣ ዘግቧል። ወጣቶቹ ከ 10 እስከ 25 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ያሉ ሲሆን በአስተርጓሚ ተጠይቀው በሰጡት መልስ ወደ ኬኒያ የገቡት በአስተላላፊዎች መሪነት መሆኑንና ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚሄዱ ተናገረዋል። ሰኞ ዕለት ወደ ኬኒያ የገቡትና በአሁኑ ወቅት በካዮሌ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙት ወጣቶች በቅርቡ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ መሆናቸውን ጠቁሟል።

ፑንትላንድ በተባለው የሶማሊያ ግዛት ከምትገኘው የቦሶሶ ከተማ ጥቂት ኪሎሚትር ርቆ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት የጦር ካምፕ ላይ በዛሬው ዕለት አልሸባብ ጥቃት ሰንዝሮ 61 ወታድሮችን መግደሉንና 16 መኪናዎችን መማረኩን ገልጿል። ከሶስት ሰዓት ውጊያ በኋላ የአልሸባብ ኃይሎች አፈግፍገዋል። ስለደረሰው ጉዳት የሶስተኛ ወገን ማረጋገጫ ማግኘት ባይቻልም የፑንትላንድ አልሸባብ አደረስኩ ያለውን ጉዳት አስተባሏል። በጉዳዩ ለመነጋገር ተሰብስበው እንደንበር ይታወቃል። በተያያዘ ዜና በሶማሊያ ጆሃር በሚባለው ከተማ ውስጥ መንገድ ላይ በተቀበረ ፈንጅ ጉዳት የደረሰበት አንድ ወታደራዊ መኪና ከጥቅም ውጭ የዋለ ሲሆን በላዩ ላይ የነበሩ ሶስት ወታደሮች ወዲያውኑ ሲሞቱ ሌሎች ሶስት የቆሰለ መሆኑ ታውቋል።

ለዝርዝር ዜና ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮን ያዳምጡ