የወያኔ ደም የማፋሰስ ተንኮል . . . በመተሀራ የስኳር መቀበር . . . የሀሰተኛ መዲሃኒት ሽያጭ መስፋፋት

ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ (ፍካሬ ዜና ታህሣሥ 08 ቀን 2010 ዓ.ም.) – ወያኔ የዜጎችን ደም የማፋሰሱን ዘመቻ መቀጠሉ ተነገረ – በየዩኒቨርሲቲዎች የተቆሰቆሰው ግጭት እየሰፋ መሄዱ ተሰማ – ንፁህ ውሀ ማግኘት እንደ በረከት እየሆነ ነው – በመተሀራ የስኳር መቀበር ጉዳይ እያነጋገረ ነው ተባለ – የሀሰተኛ መድኒቶች ስርጭት እየተስፋፋ መሆኑ ተሰማ – የዓለማ የገንዘብ ድርጅት የወያኔን የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ መንቀፉ ታወቀ – በውጪ ምንዛሪ እጥረት የተለያዩ ክፍያዎችን መፈጽም አለመቻሉ ተሰማ – የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በገንዘብ እጥረት የመዘጋት አደጋ እያንዣበባቸው መሆኑ ተነገረ፡፡

ወያኔ የዜጎችን ደም የማፋሰሱን ዘመቻ መቀጠሉ ተነገረ

ከዚህ ቀደም በምስራቅ ሐረርጌ በተከሰተው ግጭት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የኦሮሞ ገበሬዎች መፈናቀላቸውና በመቶዎች የሚቆጠሩ መገደላቸውን በተለያዩ ጊዜያት መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ ባለን መረጃ መሰረት እስካሁን በርካታ ህፃናት ከወላጆቻቸው ጋር ማገናኘት ባለመቻሉ ህፃናቱ ቀን ከሌሊት እያለቀሱ መሆናቸውን መረዳት ችለናል፡፡ በቅርቡ ይኸው አደጋ በድጋሚ መከሰቱ የታወቀ ሲሆን ግጭቱ እየደረሰ ያለው ወያኔ ባደራጀውና ባስታጠቀው የሶማሌ ልዩ ኃይል በሚባለው በመሆኑ በበርካታ አካባቢዎች ወያኔ ሲወገዝ መሰንበቱን ተረድተናል፡፡ የሶማሌ ልዩ ኃይል ከሚባለው በተጨማሪ አጋዚ የተባለው የወያኔ አረመኔ ጦር በዚህ ባሳፍነው ሳምንት በምስራቅ ሐረርጌ፣ በጨለንቆ ከአስራ አምስት በላይ የሚሆኑ ሰዎችን መጨፍጨፉ በስፋት እየተነገረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በማዕራብ ሐረርጌ ሀዊ ጉዲና በተባለ የገጠር መንደር፣ የሶማሌ ልዩ ኃይል የተባለው የወያኔ ነፍሰ- ገዳይ፣ ከሰማንያ በላይ የገበሬ ቤቶችን ማቃጠሉ የታወቀ ሲሆን ከስድስት በላይ የሚሆኑ ሰዎችም መገደላቸው ተሰምቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ የወያኔ የጭብል ቡድን የሆነው ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ የኦሮሞ ፕሬዚዳንትና እባቡ ስብሀት ነጋ መጋጨታቸው ተሰምቷል፡፡ ይህንን የሕዝብ ጭፍጨፋ በመቃወም በአምቦ በተካሄደ
ሕዝባዊ አመጽ ከሁለት በላይ የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡ ይህ ተቃውሞ በወለጋ፣ በአርሲ፣ በምዕራብ ሸዋ በብዙ ቦታዎች መካሄዱን መረዳ ተችሏል፡፡

በየዩኒቨርሲቲዎች የተቆሰቆሰው ግጭት እየሰፋ መሄዱ ተሰማ

በየዩኒቨርሲቲዎች የተጀመረው ተቃውሞ እየቀጠለ ሲሆን በዚህ ምክንያት በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት መቋረጡን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ይህ የተማሪዎች ተቃውሞ በአጠቃላይ ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ካለችበት አጠቃላይ ሁኔታ ጋር ተያያዥነት እንዳለው ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡ በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች የሚታዩ የተማሪዎች አመጾች በወያኔ የሚመራውን የትግራይ ምራጮች ዘረኛ አገዛዝን በመቃወም መሆኑን መረዳ ተችሏል፡፡ በየዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ሰላም የሚያደፈርሱት አንዳንድ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች እንደሆኑ የሚያስረዱ ተማሪዎች እንደሚሉት እነዚህ ተማሪዎች፣ ሌሎች ተማሪዎችን እየተከታተሉ የሚያስደበድቡና የሚያሳስሩ በመሆናቸው አስቀድሞ በአነዚህ ላይ እርምጃ መውሰድ የሚል አቋም መያዙ ከሚደርሱን ዘገባዎች ተረድተናል፡፡ የፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚያስረዱት ይህ ሁኔታ በዚህ ዘርን መሰረት አድርጎ ከዘለቀ የሚያስከትለው ጦስ ወደ እርስ በእርስ እልቂት ይጓዛል የሚል ነው፡፡

ንፁህ ውሀ ማግኘት እንደ በረከት እየሆነ ነው

ንፁህ ውሀ ማግኘት እንደ ቅንጦት የሚታይ ከሆነ ከሁለት አስርት አመታት በላይ መቆጠራቸውን ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡ በገጠር በተለያዩ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች የተገነቡት የውሀ ጉድጓዶች ትኩረት ሰጥቶ የሚያሳድስ ባለቤት በማጣታቸው በርካቶቹ ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ያስረዳሉ፡፡ በከተሞች አዲስ አበባን ጨምሮ ንፁህ ውሀ ማግኘት ለአብዛኛው ከተሜ የሰማይን ያህል ሰቅቆታል ቢባል ማጋነን አይሆንም ይባላል፡፡ በአዲስ አበባ በየአመቱ ለውሀ ማስፋፊያ የሚመደበው በቢሊዮን የሚቆጠር ብር የውሀ ሽታ ሆኖ እየቀረ ባለበት ከሠላሳ ከመቶ በላይ የሚሆነው የአዲስ አበባ ሕዝብ በጋሪ እየተጓጓዘ የሚመጣን ውሀ ለመጠቀም ተገዷል:: የዚህ ውሀ ዋጋም እጅግ በጣም ውድ እንደሆነ ተጠቃሚዎች በምሬት ሲገልጹ ይደመጣል፡፡ በመስመር ውሀ ከሚያገኙትም አብዛኛው መስመር ከመኖሪያ ቤቶችና ከህንፃዎች ከሚወጣ ቆሻሻ ፍሳሽ ጋር የውሀ ቧንቧዎች እየታሰሩ እጅግ ለጤና ጎጂ የሆነ ውሀ እየታደለው ለተለያዩ በሽታዎች በርካታ ሰዎች እንደተጋለጡ ከሚደርሱን ዘገባዎች መረዳ ተችሏል፡፡

በመተሀራ የስኳር መቀበር ጉዳይ እያነጋገረ ነው ተባለ

ከሀገር ውጪ በሁለት መርከብ ተጓጉዞ ከገባው ስኳር ውስጥ ሦስት ሺ ሰባት መቶ ሰባ ሰባት ኩንታል ስኳር በመርከብ ሲጓጓዝ በመመረዙ እንዲወገድ መደረጉ ሲነገር መጠኑ በይፋ ይልተጠቀሰው ቀሪው ስኳር እንዴት ከመመረዝ እንደተረፈ አለመብራራቱ የጉዳዩን ወስብስብነት አጋልጧል ተብሏል፡፡ ይህ ስኳር በመጀመሪያ እንዲቃጠል ታስቦ በመተሀራ አካባቢ የወያኔ ሹመኞች በመታገዱ ከአፈር ጋር እየተቀላቀለ እንዲቀበር መደረጉ ቢነገርም ይህ ለመሆኑ ግን ጉዳዩን ያጣራው የዋናው ኦዲተር ምንም መረጃ አለማኘቱን አትቷል፡፡ የመተሀራ ስኳር ፋብሪካ መስፋፊያም በገንዘብ እጥረት ሳበያ መስፋፊያው መጠናቀቅ ባለመቻሉ ፋብሪካው ከአቅሙ በታች እያመረተ ነው ተብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ የስኳር ፋብሪካዎች በአጠቃላይ ሀገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ በመዳረጋቸው በአሁኑ ወቅት ለሠራተኞቻቸው እንኳ ደሞዝ መክፈል እንደተሳናቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ተቀበረ የተባለው ስኳር በቁንጮ ወያኔዎች በእነ ዓባይ ፀሀይና በሳሞራ ዩኑስ የተዘረፈ ለመሆኑ እንደማያጠራጥር ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡

የሀሰተኛ መድኒቶች ስርጭት እየተስፋፋ መሆኑ ተሰማ

ከዚህ ቀደም እንደተዘገበው በውጪ ምንዛሪ እጦት ለህይወት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መድሀኒቶች በአሁኑ ወቅት ከገበያ ጠፍተዋል፡፡ ይህን ተንተርሶ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ መድሀኒቶች፣ በመድሀኒት ቤቶች እየተሸጡ በህሙማ ላይ የጤና ቀውስ እያስከተሉ መሆናቸው እየታወቀ በወያኔ በኩል የተወሰደ እርምጃ አለመኖሩ እንዲህ ባለው የውምብድና ተግባር ሊሰማሩ የሚችሉት ወያኔዎቹ እራሳቸው እንደሆኑ ብዙዎች በቁጭት ሲያስረዱ ይደመጣሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከቻይናና ከህንድ ጥራታቸው በእጅጉ የወረደ፣ እንዲሁም ከመድሀኒትነት ይልቅ መርዛምነታቸው የተረጋገጡ ይይስሙላ መድሀኒቶችም በገበያ ወስጥ እንደሞሉ የመድሀኒት ባለሙያዎችና ህሙማን በምሬት የስረዳሉ፡፡

የዓለማ የገንዘብ ድርጅት የወያኔን የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ መንቀፉ ታወቀ

የዓለሙ የገንዘብ ድርጅት ኃላፊ ፈረንሳዊቷ ክርስቲን ላጋርድ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ወያኔ ከደረሰበት የውጪ ምንዛሪ ችግር ሊወጣ የሚችለው ለግሉ ዘርፍ የተዘጉ የንግድ ሥራዎች ሲፈቅድ መሆኑን አስረግጠው መናገራቸው ታውቋል፡፡ ወያኔ ከሰሀራ በታች ከሚገኙ ሀገራት ብቸኛው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶችን አፍኖ የያዘ ቡድን በመሆኑ በኢንተርኔት ዘርፍ በውድድር ሊመጣ የሚገባውን ለውጥና እድገት ገድቦ መያዙ በየጊዜው ነቀፌታ እየተሰነዘረበት እንደሆነ የሚታወቅ ነው ተብሏል፡፡ ከዚሁጋር በተያያዘም ወያኔ የውጪ እዳውን መክፈል ባለመቻሉ እዳው እየተከመረ በመሄዱ ለዚህ የእዳ ክፍያ የሚሆን የፖሊሲ ቅየሳ እንደሚያስፈልግ ሴትየዋ አበክረው መናገራቸው ታውቋል::

በውጪ ምንዛሪ እጥረት የተለያዩ ክፍያዎችን መፈጽም አለመቻሉ ተሰማ

የውጪ ምንዛሪ ባዶ መሆን በወቅቱ መፈጸም የሚገባቸው ክፍያዎች ሳይፈጸሙ እጅግ በመዘግየታቸው ወያኔ ከዚህም ከዚያም ተቀስፎ መያዙ እየተነገረ ነው፡፡ ነዳጅ አቅራቢ፣ ቪቱል ኦይል የተባለ ኩባንያ ከ 2015 እስከ 2017 ናፍጣ፣ ቤንዚንና ድፍድፍ ዘይት አቅራቢ ሲሆን ያቀረበበት ሂሳብ 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሊከፈለው ባለመቻሉ የኮንትራት ውሎን ለማደስ ፈቃደኛ እንዳልሆነና ወያኔ እዳውን ከተገቢ ጥቅሙ ጋር እንዲከፍለው ከውትወታ አልፎ በህግ ወደ መጠየቅ ሊጓዝ እንደሚችል ማስጠንቀቁ ተሰምቷል፡፡ በተመሳሳይም ፔትሮ ቻይና የተባለ ኩባንያም ነዳጅ እያቀረበ ላለበት አንድ መቶ ሰባ ሚሊዮን ዶላር ሳይከፈለው እስካሁን ሲንከባለል እንደመጣ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ የቻይና ኩባንያ ውል በዚህ በያዝነው በፈረንጆቹ ወር መጨረሻ እንደሚያከትም ሲታወቅ ኩባንያው ውሉን እንደማያድስ ውስጥ አዋቂዎች ግምታቸውን እየሰጡ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ በአዲስ አበባ የትኬት ሽያጭ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን በረራ ድርጅቶች ትኬቶቻቸውን በብር የሸጡትን ወደ ውጪ ምንዛሪ ለመቀየር አለመቻላቸው ሥራቸውን አስቸጋሪ እያደረገባቸው መሆኑን አማረው በመግለጽ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በገንዘብ እጥረት የመዘጋት አደጋ እያንዣበባቸው መሆኑ ተነገረ

ወያኔ የትምህርት ጥራቱን እመቀ እመቃት በመክተት የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና አስረኛ ክፍል ማድረጉ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ተገቢውን ነጥብ ያላገኙ ተማሪዎች የሙያ ስልጠና እንዲውስዱ ይደረጋል፡፡የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ በጀታቸው በተለያዩ እርከን በሚገኙ የወያኔ ሹመኞችና አገልጋዮች እንደሚዘረፍ ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ዘንድሮ በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ወያኔ በገንዘብ እጥረት አጣብቂኝ ውስጥ በመግባቱ የእነዚህ የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት እጣ ጨለማ መሆኑ ይነገራል፡፡ ተቋማቱን ከመዝጋት በሚል የውጪ ኩባያዎች ከወያኔ የሙያ ማሰልጠኛ ድርጅት ጋር በሽርክና እንዲሠሩ ጥሪ መቅረቡ የታወቀ ሲሆን ብዙዎች ጉዳዩን የይስሙላ ተውኔት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በሙያ ስልጠና ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በተግባር መሰልጠን ሲገባቸው በንድፈ-ሀሳብ ብቻ ተወስነው እንዲጨርሱ መወሰኑም ታውቋል፡፡

ለዝርዝር ዜና ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ያዳምጡ