ከግባችን ለመድረስ ትግላችን ተጠናክሮ ይቀጥል

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) መግለጫ  –  የኢትዮጵያ ሕዝብ ለ27 ዓመታት በዘረኛና ፀረ ሕዝብ አገዛዝ ሲደማ፣ ሲታሰርና ሲሰቃይ፣ ሲገደል መቆየቱ ሁሉም ዜጋ የሚያውቀው አሰቃቂ እውነታ ነው። ሕዝባችንም ወያኔ ሥልጣን ከጨበጠ ጀምሮ ብቅ ጥልቅ ባለ መልኩም ቢሆን አስከፊውን አገዛዝ ለማስወገድ ትግል ሲያካሂድና አያሌ መስዋዕትነትን ሲከፍል ቆይቷል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሲገደሉ፤ ከ50ሺ ያላነሱ ዜጎች ደግሞ ግብረ ስየል ተፈጽሞባቸው በየጉድጓዱና በየእስር ቤቱ ተጥለው ሲማቅቁ መቆየታቸው ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ተፋፍሞ በመካሄድ ላይ ያለውን ትግል ለማፈንና ለማቀዝቀዝ ወያኔ የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አፋኝ አዋጅ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ አውጇል።ድሮም ቢሆን እኛ የምናውቀው ወያኔ በቁጥጥሩ ስር አውሎ የሚያሰቃያቸውን የፖለቲካ እስረኞች ሁሉ አለአንዳች ቅድመ ሁኔታ የሚፈታ ወይም ለድርድርና ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር ክፍት የሆነውን ሳይሆን ዘረኛውን፣ አረመኔና አፋኙን፤ የአስቸኳይ ገዜ አዋጅ የሚያዥጎደጉደውን ነው። ወያኔን ያደቆነው ሰይጣንና የሰፈረበት ጂን ሀገርና ሕዝብን አጥፊ ነው።

በዚህም በዚያም የወያኔ ጥረት አደናግሮም ሆኖ ፍጅትን አካሂዶ የሕዝብን ትግል ማፈንና ማስቆም ነው። በዚህም ሰይጣናዊ ተልዕኮው የሚተባበሩትንና መጋዣ የሚሆኑለትን ከየመቃብራቸው አስነስቶ አሰማርቷል። ድርድር ብለው የሚፈራገጡትን ክህደቱዎች ያጤኗል! ወያኔ አዲሱን የጥቃት አዋጅ ሲያውጅም የሽግግር መንግሥት ይመሰረታል ብላችሁ አታስቡ፤ አትቃዡም ሲል በግልጽ ነግሮናል። ወልዲያ ባለ አፋችን አማሬሳ ለማለት ተገደናልና የሕዝብ ኅብረትና የጋራ የትግል መንፈስ በትግሉም፣ በአድማውም በግልጽ እየታየ በመሆኑ ሕዝብን ሊከፋፍሉ የተነሱት ዘረኞችና ጠባቦች ሁሉ ዓላማቸው ውድቅ ሆኖ ይገኛል። ሕዝባችን ባካሄደው ትግል በዘር ለይቶ ማንንም ያላጠቃ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በወያኔ ላይም እየደረሰና እየተፋፋመ መቀጠል ያለበትን ሁለገብ ጥቃት እንደ ጸረ-ትግሬ ጥቃት ለማቅረብ የሚጥረውን የወያኔ አገዛዝ ሆነ በባዕድ ሀገር ያሉ የትግራይ የምሁሮችና ተቋሞችን ሕዝቡን ለአደጋ አታጋልጡት የምንላቸው ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዝብ በመሠረቱ እንዲህ ዓይነት – አንዱን ዘር ነጥሎ የማጥቃት – ባህልም የለውምና የሌለውን ባህል መለጠፉ ትክክል አይደለም። ሥራ ማቆም አድማ፣ የሙት ከተማ አድማ፣ የጋራ አድማ፤ የወያኔው ድርጅት ንብረት የሆኑትን ለይቶ ማውደም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወያኔን ማጋለጥ፤ የወያኔ ቡችላዎችና የባንዳ አራሙቻዎችን ሁሉ ከጥቅም ውጪ ለማድረግ ትግላችንን ማጧጧፍ ግዴታችን ሆኖ ይገኛል። ወያኔ አደብ ገዝቶ፤ በይሉኝታና ንስሐ ስሜት ተጸጽቶ የሚታረም አይደለም። ወያኔ እስረኛ ልንፈታ ነው የሚል መግለጫ በሰጠበት ወቅት ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ሊፈቱ ይችላሉ በሚል ራሳቸው ተሞኝተው ሌላውን ሊያሞኙ የሞከሩትን ሁሉ አብዛኛውን እንደማይፈታ ነግረናቸዋል። እንዲያውም ተጨማሪ እየገደለና እያፈሰም ነው ከማለታችንም በላይ የአፈና እርምጃ/አዋጅ እንዳሰበም መጠቆማችን ይታወቃል። ወያኔ የተወሰኑ እስረኞችን የለቀቀ መሆኑን ቢገልጽም ለረጅም ጊዜ አስሮ የሚያሰቃያቸውን በርካታ የኢሕአፓን አባላት፤ የሙስሊም ታጋዮችን፤ የዋልድባ ቀሳውስትን፤ ከባህር ዳርና ጎንደር፣ አምቦ …ወዘተ የታፈሱ ወጣቶችን አልፈታም። ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ የሚለውን ሕዝባዊ መፈክር ዘንግተው የተወሰኑት ስለተፈቱ ብቻ በደስታ መዝናናት አግባባነት የለውም።

የከፈልነው ከፍተኛ መስዋዕትነት ወያኔ ሥልጣኑን ጨብጦ ባለበት ሁኔታ ለውጥ ተደረገ በሚል አስመሳይ ማደናገሪያ እንደገና የወያኔን አስከፊ አገዛዝ ለማስቀጠል አይደለም። የታገልነው ለሕዝባዊ መንግሥት ነው – ሕዝብ የሥልጣን ምንጭ እንዲሆን ነው ! የታገልነው የወያኔን የአገዛዝ ሥርዓት አስወግደን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመተካት ነው እንጅ ያንኑ አፋኝና ጨቋኝ ሥርዓት ለማደስ አይደለም። የሰማዕትን ደም ገና ከወዲሁ ቦታ አሳጥቶ የወያኔን አገዛዝ ለማስቀጠል ከወያኔ ጋር መሞዳሞድ ያስወቅሳል ፤ ያስወግዛል። በደማቸውም ላይ መቀለድ ይሆናልና መቸም ልንቀበለው የምንችል አይደለም። ወያኔ 27 ዓመታት ሙሉ በግፍ ሲገዛንና በገፍ ሲጨርሰን ዕርቅና ሰላም ያሉት፤ ጥሪ ያደረጉለት በርካታ ወገኖች ነበሩ። ለሰላም ጉባኤ ወደ አዲስ አበባ የመጡትን ከማሰር ጀምሮ ወኔ ካላችሁ ድፈሩና ታገሉን፤ ጦርነት እንሰራባችኋለን፤ … ወዘተ በሚል ሲታበይብንና ሲደነፋብን ከርሟል ። የሕዝብን ምርጫ ሰርቆ ፓርላማ በሚለው አንድ እንኳን ተቃዋሚ እንዳይኖርም አድርጓል። ሲያስተላለፍ የቆየው መልዕክት አንድና አንድ ብቻ ነው–በግድ ካልሆነ ሥልጣን እንደማይለቅ፤ የሕዝብን መብትና ፍላጎት እንደማያከብር፤ አምባገነነቱን እንደሚቀጥል፤ ጸረ ሕዝብነቱን አቅፎ እንደሚገኝ፤ አፈና እንደሚፈጽምብን ነው። በሕጋዊ መንገድ በሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ላይ ከአረመኔው ደርግ አገዛዝ ጊዜ ያልተለየና ለአፍም የሚቀፍ ግብረ ስየል ፈጽሟል። በሕዝብ አመጽ እስኪገደድ ድረስ፣ ”አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለም ወንጀለኛ ብቻ እንጂ” ብሎ ሺዎችን አፍኖ ሲያሰቃይ መቆየቱንም የምናውቀው ነው። ለውሸቱ ለከት፤ ለግፉ ገደብ ሳይኖረው የ27 ዓመታት መከራና ሥቃይ ጭኖብን የከረመ ኃይል ነው። በመሆኑም ወያኔ ይወገድ ሥርዓቱ ይውደም ወቅታዊ መፈክር ሆኖ እስካሁንም አለ። የመፈክሩን ወቅታዊነትም ጠባቂ ወያኔ ራሱ በአስከፊና ዘረኛ አቅዋሙና ድርጊቱ መሆኑ ግልጽ ነው። የወያኔ አገዛዝ ካልተወገደ ኢትዮጵያ ክብሯን፣ መብቷንና ብልጽግናዋን ከቶም አታገኝም።

ስለዚህም ትግሉ መቀጠሉ ፍትሃዊና አስፈላጊም ነው። ግባችን ሕዝባዊ መንግሥትና ዴሞክራሲን ማስፈን ነውና ከዚያ አልደረስንም። ትግላችን ከወያኔ ተደራድሮና ወያኔን በያዘው መልክ ሆነ በአዲስ ጭምብል ማስቀጠል አይደለምና የምናቋርጠው አይደለም፤ አይሆንምም። ትግላችን ከግቡ ሳይደርስ እጅ ሊሰጡ የተዘጋጁ ኃይሎች አያሌ ናቸው። በቅድሚያ ወያኔ የግፍና የዘረኛ ሥርዓቱን መቀጠል ይፈልጋልና በኃይልም ሆነ በማወናበድ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። አዛዦቹ የሆኑት ባዕዳንም ከውድቀት ሊያድኑት እየተሯሯጡ ናቸው። ከወያኔ ጋር አብረን ተቃቅፈን እንስራ ባዮች በአሁኑ ጊዜ መብዛታቸው፤ ክህደቱዎች ከጉድጓዶቻቸው ወጥተው ”አለና !” ሲሉ መሰማታቸው፤ በሀቀኛ ጸረ-ወያኔ ድርጅቶች ላይ ጥቃት መብዛቱ አለምክንያት አይደለም። እነዚህን ሁሉ መቋቋም ማቸነፍ ይጠበቅብናል። በሕዝብ መሃል የተፈጠረውን ሕብረት ማጠንከር መንከባከብ ግዳጃችን ነው። ቀጥሎም ወይም ከዚሁ በተያያዘ ደግሞ የሀቀኛ ሀገር ወዳዶችን ጸረ-ወያኔ ህብረት ከወዲሁ መመስረት መቻል አለብን። ለወያኔ እጅ ለመንሳት የሚመሰረት ኅብረት – ያውም ሚዛን በማይደፉ ቡድኖች — ለሀገርም ለሕዝብም ጠቃሚ ባለመሆኑ በዚህ ቧልት ገብቶ ለመተብተብ ጊዜውም ሁኔታውም የሚፈቅድልን አይደለም። የትግል መፈክሮቻችን የተለወጡ አይደሉም፤ አራት ነጥብ።

ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ!

pdf_print