የደነቆሩ ዘረኞች፤ መደዴ ፖለቲከኞችና ቢጠቅሙ ትዝታዎች

ከሀማ ቱማ –

“እትብቱ ተቆርጦ ካረፈበት ምድር፣
የሰው ልጅ ካልኖረ ከራሱ ህዝብ ጋር፣
ምን መቅኖ ያገኛል ያገር ልጅነቱ፣
በተዛባ ዕድሜ ከራቀ ከእናቱ።”

ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው)

በነሓሴ 1961 ዓ.ም. አንድ ዲሲ 3 አይሮጵላን ሰባት ሆነን ጠልፈን ወደ ሱዳን ስንገባ “በቅርቡ ወደ ሀገራችን እንመለሳለን” የሚል ጽኑ እምነት ነበረን።  ጊዜ አልፎ ነቃፊዎችና አዋራጆች ሲፈሉ አንድ የፈረንጆቹ ሰላይ የነበር ግለሰብ እኛን ያቀለለ መስሎት የጠለፉት አይሮጵላን እኮ ዕንቁላል ሚጫንበት ነው ብሎ ተችቶ አስቆን ነበር።  ይህን ውዳቂ ግለሰብ ደርግ ጊዜውን ጠብቆ ሰደድን ሰርገህ ልትገባ ሞከርክ ብሎ ገሎታል።   ቁም ነገሩ ግን የአጼው ስርዓት ማክተሚያው መሆኑን ማወቃችንና  ነጻ በሆነች ኢትዮጵያ ለመኖር ተስፋ ማድረጋችን ነው።  ግን አልሆነም።  ወደ ኢትዮጵያ ምድር ተመልሰን በትግራይም፤ ጎንደርም፤ ጎጃምም ልንታገል ብንችልም ለውጥ መጥቶ በሀገራችን ልንኖር አልቻልንም።  አለፈለት ቢባልም ቢሾፍበትም የሀገራችን ወጣትም ዛሬ ለአስከፊ ስደት ተዳርጎ በቦሳሶ፤ የመን፤ ሊቢያ፤ ጣሊያን ድንበር ላምፓዱሳ በአሰቃቂ ሁኔታ እያለቀ ነው።  ለዚህም ነው የገሞራው ቀጣይ ግጥምም ሲያጅበን እስከዛሬ የቀጠለው፤

“ክንፍ የለኝ ሆኜ እንጂ ክንፍማ ቢኖረኝ፣
መች ያስችለኝ ነበር እኔ አንቺን ሳልጎበኝ?
መች ያስችለኝ ነበር እስከዛሬ ድረስ፣
ያች ውድ ሀገሬን ሳላይና ሳልደርስ!”

ገሞራውም ለሀገሩ ሳይበቃ በባዕድ ሀገር  ሞቶ በኢትዮጵያ ግን ሳይፈልግ ሊቀበር ሆኗል።  ሌላ ራሱን የቻለ ታሪክ።

በአጭሩ ያሰብነው ዓላማ አልሆን ብሎ ቢዘገይም ቃል ኪዳናችንን ሳንክድ እነሆ እስከዛሬ በትግል ላይ አለን።  አለን ባመጽ ለማለት በሙሉ አፍና ድፍረት የምንነሳውም በአያሌ ድለላ ሳንሸነፍ፤ ችግርና መከራ ሳይፈታን ትግል መቀጠል በመቻላችን ነው። ያን ጀግናና ታጋይ ትውልድ፤  ከልቡ ለሀገሩና ወገኑ ቆሞ ለጋ ሕይወቱን የገበረውን ሁሉ ዛሬም የሚያወግዙትን የሰው አሳማዎች መስማት መገደዳችን ደግሞ ያስቆጨናል።  ለቀጣይ ትግላችንም ነዳጅ ሆኖ ስናይና ዛሬም ወጣቱ አይ ተስፋ ቆርጧል፤ በዲቪና አላሙዲ ተሸንፏል ሲባል ለውድ ሀገሩ መስዋዕት ሊሆን ተነስቶ ሲተካን መደሰታችን ደግሞ አልቀረም።   ሆኖም፤

“አለን በአመጽ አዲስ ሥርዓት እስኪታነጽ፣
የሰማዕት ደም ፍትህን አግኝቶ እስኪታበስ”

ማለታችንን ግን አላቆምንም።

ዛሬ ይህን ማንሳት ግዴታ የሆነው የደረስንበት የታሪክ ወቅት ዳግም እንደገና በሀገርም ውስጥ ሆነ በደጅ ክንፍ አልባ መብት አልባ በሀገራችን ባዕድ ተፈናቃይ ስደተኛ እንዳንሆን ነው።  ለሶስት አራት ዓመታት የሕዝባችን ትግል ተፋፍሞ ወያኔን ሊያስወግድ አምርሮ እየገፋ ነው።   በዚያው ልክ ደግሞ ወያኔና ጭፍሮቹ ይህን ትግል ሊያደናቅፉ በመዋደቅ ላይ ናቸው።   ማን ያቸንፋል ግብግቡ በደም ታጅቦ፤ በወገን ደም ታጅቦ በመካሄድ ላይ ነው።  ጎርፉ ሲመጣ የመዘጋ ዓይጥ ከየጉድጓዱ ብቅ ይላልና የምናውቃቸው ሆኑ አዳዲስ ዓይጦች ጥርሳቸውን አግጠው ብቅ ብለውብናል።  ፈሪ ተለይ ነጋሪት ተጎሽሞ፣ ማን ሀገር ወዳድ አርበኛ፣ ማንስ ቡከን አስመሳይ ታጋይ መሆኑም እየታየ ነው።  ግና ሕዝብ በቃ ብሎ ተነስቷልና የወሳኝ ለውጥ ጊዜ በየተሬው ፈንጥቆ አለሁ እያለን ነው።

”በገዛ ቤታችን ባይተዋሮች ሆነን፣
ኑሮ ተባለና ይኽው እንኖራለን፣
ይህን ሁሉ መዓት ባናት ተሸክመን።”

ሲል ገሞራው ያማረረውን ህዝብ ይህማ ሰለቸን በቃን ብሎ በማመጹ የወያኔ የውድቀትና መቀበሪያ ቀን መጣሁ ተቀበሉኝ እያለን ነው።  አቤት ልንል ስንነሳ ግን ጋሬጣው እየጣለን ድላችንን ስንቀማ ቆይተናል።

ያኔ በዚያ ጎህ ባልቀደደበት ዘመን ለትግል ስኬት አስፈላጊ የሆነውን ድርጅት ምስረታ አዲስም ከባድም ሙከራ ነበር።   ወደ ውጭ ሀገር አይሮጵላን ጠልፈን ልንሄድ ስናቅድ አይሮጵላን ላይ ወጥቶ የሚያውቅም ውጭ ሀገርንም ያዩ አንድ ወይም ሁለት  ነበሩ።  መውጣት አስፈላጊ ሆኖ የተገኘው አንድም የተማሪውንና የህዝባችንን ትግል ለማስተጋባት ሲሆን በዋናውና ሌላው መንገዱ ደግሞ በውጭ ለትጥቅ ትግል ተደራጅቶ ለመመለስ በሚል ነበር።  ከእኛ ቀጥለው ሌሎች በወለጋ በኩል ወደ ሱዳን ወጥተው፤ ኢሕአፓም ሆነው፤ ተመልሰው ታግለው የተሰዉም ቆየት ብለውም የተዉንም ነበሩ።  እነ ዋለልኝ፤ ጌታቸው፤ ማርታና ሊሎችም የጠለፋ ሙከራ አድርገው መረጃው በደረሰው ጨካኝ መንግስት ተገድለዋል፤ የገዳዮቹም ማንነት ምስጢር እንዳልሆነ ይታወቃል።  ሕይወታቸውን ገብረዋልም።  የእኛን እርምጃ በተመለከተ ብዙ ተብሏል–አብዛኛው ሀሰት ነው።  አንድ ለፎ የማያወቀውን ሲጽፍ ከምዕራብ ጀርመንና አልጄሪያ ኤምባሲ ተመሳጥረው ያደረጉት ነው ብሏል።  የሁለቱ ሀገሮች ጎራ ተጻራሪ እንደነበርም አላሳሰበውም።  ሌላው የተቃዋሚ ድርጅት መሪ ነኝ ባይ ቱሪናፋ ደግሞ ጠለፋውን ያካሄዱት ከእኛ አስፈቅደው ነው ሲል ቀጥፏል።   የሀገራችንን አይሮጵላን (ከሱዳን ወደ አዲስ አበባ ተመልሷል ለነገሩ) ሰርቀው ሀገር ጎዱ ያሉን ነበሩ።  በካርቱም ኮበር እስር  ያሉ ኢትዮጵያዊ ሌቦች ግን ከሰረቁ አይቀር አይሮጵላን መስረቅ ነው እንጂ፤ትምህርት አገኘን ብለውም አድንቀውናል። ያተረፍነው ለስድስት ወር በቡሪ ፖሊስ አካዳሚ እስርና ከሱዳን ወደ አልጄሪያ መባረር ቢሆንም ላቀድነው በር ከፍቶልናል። የአጼው መንግስት መልሱልን ሲበዛም፤ካልተመለሱም ለስብሰባ ካርቱም አንመጣም የሚል አቅዋም ሲነገርም ሱዳን ወደ ቻይና፤ መስኮብ፤ምሥራቅ ጀርመን ሊልከን ቢያማርጠንም ሁሉም ጋ አንሄድም፤ግባችን በሱዳን ወይም አካባቢው ቆይተን መደራጀትና ትጥቅ ትግል መጀመር ነበርና በጊዜው ተራማጅ የነበሩት የሱዳን መኮንኖች ገዢዎች  (ኋላ በኒሜሪ የተገደሉ) ሊመልሱን ባይፈቅዱም በፓሊስ አጅበው ወደ አልጄሪያ ሰደውናል።   አልጄርያ የቃል አብዮተኛ የተግባር አምባገነናዊ አገዛዝ፤ ዘረኛ ዜጎችም የበዙባት።   መጥፎ ስደት።   ያም ሆኖ የታሰበውን ድርጅት ለመመስረት በአስከፊ ችግር አልፈን በሚያኮሩ ወጣቶች — በሀገር ውስጥም በደጅም — ትብብር እውን ልናደርገውም ችለናል።  በጋራ ጥረትና ልፋት።  ይህ የራሱን ትረካና ዝርዝር ይጠብቅ እንበልና ዋናው ቁም ነገሩ ግን ለሀገር ተብሎ ከተነሱና ከቆረጡ ብዙ ማከናወን መቻሉ ነው። እኛም ሆን አብረውን የተሰለፉት የነበራቸው ርዕዮት ቢኖራቸው፤  እምነታቸው፤  ትግላቸውና ሰልፋቸው ለኢትዮጵያን ለድሃው ጭቁን ሕዝቧ ነበር።   በሃይማኖትና ዘር ሳንከፋፈል ልንሰለፍ የቻልነውም በጋራ የምንወዳትና ልንሞትላት ዝግጁ የሆንላት ኢትዮጵያ ስለነበረችን ብቻ ነው ። የሀገር ተምቾች ዛሬ ያን ትውልድ በሀገር አጥፊነት ሊከሱ ሲውገረገሩ (ያውም ብዙ መቶ ሺ ለጋ ሕይወትን አጥፍተው) በጉድ ይሰማ ጆሮ የምናልፈው ብቻ ሳይሆን ያን የጀመርንባቸውን ትግል እንድንቀጥልባቸው ሞራልና ግፊት ሰጥቶናልና ጸንተን እንታገላቸዋለን።  በክልል ተበልቶ እርስ በርስ ሊናከስ ተነስቶ የነበረውም ለአንዲት ሀገር ኢትዮጵያ የተሰዋነውን ከቶም መቼም ሊወቅሰን የሚችል አይደለም።

ያኔ ለትግል የተነሳውን ሁሉ በልዩ ልዩ ምክንያት የሚያወግዙ ያኔም ነበሩ ዛሬም በአሰቃቂ ደረጃ ፈልተዋል።  የሚተቹን ጥፋታችን ባልሆኑ ጉዳዮችና ክስተቶች ነው።   እኛ አመጽ አመጽ ብለን አልተወለድንም።  ወደ ዓመጽ የገፋን የነበረው አድሃሪ የአጼ ስርዓት ነው።  እነ በላይ ዘለቀን የሰቀለውና ምድረ ባንዳን የሾመው።   አጼው የነመንግስቱና ገርማሜ ንዋይን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በአሜሪካ ድጋፍ አክሽፈው ከዚህ ሙከራ ግን ትምህርትን ቀስመው ለውኝ ለማምጣት ፈቀደኛ ቢሆኑ ኖሩ የእሳቸውም የስርዓታቸውም መጨረሻ የተለየ ይሆን ነበር። ዛሬም ለምሳሌ ወያኔ በግፉና በዘረኝነት በመቀጠሉ ሕዝብ እምቢኝ ብሎ ሊያመጣበት ለሚችለው አሰቃቂ ዕልቂት ተጠያቂ ራሱ ነው።   ጥፋቱ የወያኔ ነው።   የየካቲት አብዮትን የጠራ የአጼው ስርዓት በመሆኑ የዜጋ ግዳጃቸውን ሊወጡ በተገደዱ ተራማጆችና ወጣቶች ላይ ውግዘት መከመሩ ፋይዳ ቢስና ከታሪክ ሂደትም የተጣላ ይሆናል።   እንዳልካቸው መኮንንም የጥገና ለውጥ ሊያሰፍን ሲሞክር ሠራተኛው ሕዝብ በጠቅላላ ስራ ማቆም አድማ “ይቅርታ ጊዜ አልፏልና ወግድ” ያለውም አለምክንያት አልነበረም።   ከዚህ ተያይዞም ሊነሳ የሚገባው ደግሞ ያለን የነበረን  ፍርደ ገምድልነትና ጭቆና የለም ማለቱ ችግርን የሚፈታ ሳይሆን የሚያባብስ መሆኑ ነው።  ስርዓት የፊውዳል ስርዓት ነበር የሚለውን ሊክዱ የከጀሉ የታሪክ ላፒሶች ብቅ ማለታቸውንም በአሁኑ ጊዜ እየታዘብን ነው። ጪሰኝነት፤ ገባርነት፤ምርትን ለባላባቶች ማስረከብ(በፍትሓ ብሄር ሕግ የሰፈረ) ና በድህነት መማቀቅ መቸ ታይቶ ሊሉ የተነሱትን መቸም ታውረዋል ብንል የለሆሳስ ንግግር ይሆናል።  ሀቁ ሌላ ነውና።  የአርሶ አደሩ ዓይን ያወጣ የመበዝበዝና መሰቃየት ሁኔታ ለአርሶ አደር አመጾች መፈንዳት በደቡብም በጎጃምም ምክንያት ከመሆኑ ባሻገር መሬት ለአራሹን አብዮታዊ መፈክርም አድርጎታል።   ጸሓይ የሞቀው ሕዝብ ሁሉ የሚያውቀው ሀቅ ነው።  ብሔራዊ ከበርቴ የሚባል መደብ ሊከሰት ታግዶ አቀባባይና ቅጥረኛ ከበርቴዎች ተፈልፍለው ሠርቶ አደሩንም ሕዝብ መብት ነፍገው ሲበዘብዙና ሲያስበዘብዙ እንደነበርም የሚረሳ አይደለም።  የደቡብ ጢሰኛ አርሶ አደር ላይ በሀይማኖትም በብሄረሰብም ደረጃ ጭቆና እንደነበረበት የማይካድ ሆኖ ሳለ ዛሬ ዓይናቸውን ጨፍነው ይህን ሀቅ የሚክዱት ደግሞ ዛሬ በዚህ መስክ ላለው ችግር ከፍተኛ አስተዋጾ አድራጊና አሁንም ችግር ፈጣሪ ሆነው ይፈረጃሉ።   እነዚህ ሃሳዊዎች የሰለጠኑና ያወቁ መስሏቸው ኢትዮጵያዊውን የእኔ ብጤ ልጅ ዋለልኝን ሊያወግዙ ቢጥሩም ዋለልኝ ለዩኒቨርስቲ ትምህርት ሳይበቃ ያኔ ደራሳ ይባሉ በነበሩት፤ በሜጫ ቱለማ፤ በኦጋዴን፤ ጭቆና ይወገድልን ትግሎች ብቅ ብለው በአፈናም በግድያም እንደተጠቁ የምናውቀው ነው።   እነ መንግሥቱና ገርማሜ ንዋይ ወዘተ ሲሰቀሉ፤ እነ ማሞ መዘምር ሲገደሉ፤ የተማሪዎቹ ሚና ምን ነበር? ማነውስ ግድያውን የፈጸመው? የኤርትራ ነጻ አውጪ ግንባር የትጥቅ ትግል በ 1960 ሲጀምር ዛሬ የሚወገዙት ተማሪዎች ሁሉ ነቅተው መሬት ለአራሹ ብሎ ለመሰለፍም ብዙዎቹ አልደረሱም ነበር።   ጭቆና ነበረ፤ አሁንም አለ።  በሀይማኖት የነበረው ልዩነት እንዲወገድ ክርስቲያኑም ሳይቀር ሙስሊሞችን አጅቦ በየካቲት 66 ታግሏል።  የሌለን ጭቆና አለ ብሎ ተሰልፎ ሕይወቱን የሚገብር ያበደ ሰው አልነበረም/የለምም።  ሙስሊም ዜጎች ወያኔን ይኸው ለ 5 ዓመታት ወጥረው የሚታገሉትና መስዋዕትነትንም የሚከፍሉት፤ ለቀጣይ ኢትዮጵያዊ ትግል አርአያ የሆኑት በወያኔም የሀይማኖት ጭቆና ስለሰፈነ ነው።  የአሰቦት ፍጅት፤ የአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ፤ የአደባባይ ኢየሱስ (ጎንደር) ግድያዎችን ማስታወስም ይበቃል።  የባህታዊ ፍቅደ ሥላሴን መገደል፤ የሙስሊም ምዕመናን መሪዎች መሰዋትና ወደ ቂሊንጦ ዝዋይ መጋዝ፤ የዋልድባ ቀሳውስት ላይ ግድያና ስየል መፈጸሙ።   ይህ ሁሉ የለም አልነበረም ሀሰት ነው የሚለን ወያኔ ብቻ ከነጭፍሮቹ ነው።   አሁንም ቢሆን መብቴ ተረገጠ የሚለውን ሕዝብ ማዳመጥና ፍትህና እኩልነትና ለማስፈን በጋራ መታገሉ እንጂ ጭቆና የለም ብሎ መካዱ ለኢትዮጵያ አይበጃትም።

የመከራችን ሌሊት ሊያልቅ ሲቀርብ የደነቆሩ ዘረኞችና መደዴ ፖለቲከኞች ለባሰ ጥፋት ሊዳርጉን ደፋ ቀና ማለታቸውን ቀጥለዋል።  የሰሞኑ የክህደት ልምዱ የአባይ ጸሃዬ ተዘጋጅተዋል ተዘጋጅተናልና እንጨራረስ ንግግር የሚያስታውሰኝ ካለ የሚፈታ ከተማ አዋጅ ቢነግሩበት አይሰማን ነው።  አባይ ጸሃዬ በወያኔ ታሪኩ — ጠንቅቀን በምናውቀው — ልክ እንደ መለስ ጓድ ያላቸውን ሳይቀር የመክዳትና የፈሪነት ታሪክ ነው።   የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሀዲዎችና ፈርጣጮች ለገንጣዮች አጋልጠው እንዳስጠቋት ብናውቅም ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያቸንፍበት አቅምም ሁኔታም የለም — ሕዝብ ተባብሮ በወያኔ ላይ እስከተነሳ ድረስ።   ወያኔ ሀይል ያለውም ይተናል።   የመገንጠል ቅዠቱም ቅዠት ይሆንበታል እንጂ አይጠቅመውም።  ዕልቂት ይሁን ከተባለም ማን እንደሚያልቅ በዘረኝነት ላልታወረው ሁሉ ግልጽ ነው።  የማይድን በሽተኛ የሆነው ወያኔ እንደ አጼ ልብነ ድንግል ጦር አምጡ ብሎ ቢማጸን የሚታደገው ደጋማ ወይም ባዕድ የሚያገኝ አይሆንም።   የርዋንዳ ዓይነት እልቂትን ጋብዞ ታሪካችንን ሊያቆሽሽ ቢጥርም የሚሳካለት አይሆንም።   እንዳይሳካለት ግን በወያኔ ወጥመድ ውስጥ ነጋ ጠባ ዘው የሚሉትን መደዴዎች መምከር የግድ ነው።  ቢመከሩ ቢመከሩ አልሰማ ያሉና ትግሉን እያንደፋረሱ አላዋቂ ሳሚዎች መበርከታቸው የሚካድ አይደለም። በነዚህና በወያኔ ቅጥረኞች፤ የባዕዳን ተቀጣሪዎችና የለየላቸው የስልጣን ጥመኞች መሀል ልዩነት አለ።   ከሀዲና ቅጥረኞቹን ለመምከርም– በጊዜ ከሕዝብ ይቅርታ ጠይቁ ውጪ–ጊዜ አናጠፋም።   ደግመን ደጋግመን አሳስበናቸዋል።   የወያኔ አባሎችና ተለጣፊዎች ሳይቀር ከወንጀሉ ጎራ ከወጣችሁና ወደ ሕዝብ ፊታችሁን በደግና በሀቅ ካዞራችሁ መገናኛ ቦታ አናጣም ስንል ቆይተናል።   አሁንም አላቋረጥንም።   ፍትህን ማወቅ ማየት ያቃተውን ጠቅላይ ሚኒስቴር ተብዬ በአስመሳይ ወይም በከተሜዎች አነጋገር ፎርጅድ ኦሮሞ (ወርቅነህ ገበየሁ ለምሳሌ ሆነ ሌላ) ለመተካት መከጀል ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም ነው።   ቀደም ብሎም እንደነ በረከት ዓይነቶቹ አስመሳይ አማሮች ተለጣፊ ቡድናቸውን ይዘው የት እንደደረሱ  አይተናል።   እስረኛ ፈታን ባሉ ማዕግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ መግደልም ማሰርም ጮሌነት ሳይሆን በራስ ላይ ጥፋትን ማውረድ ነው።   ዋናው ትኩረታችን ያወቁ መስሏቸው የሕዝብን ጎራ እንደ ደንባራ በሬ የሚያተረማምሱትን ይመለከታል።   ተቃዋሚ ነን ብሎ በዚያው የወያኔን አቅዋምና ፍላጎት አስተጋቢ መሆን (በወልቃይት ጠገዴ ጉዳይም ሆነ በድርድር ) ያስጠይቃል።   የሕዝብን የሙት ከተማና ሌሎችንም አድማዎች ተጻሮ  ወይም ለመከፋፈል ሲንደፋደፉ መገኘት ስህተተኛ ያደርጋል።   ጉድ ይሰማ ጆሮ እነ ኢሕአፓንም ጸረ አማራ ብሎ ለመክሰስ መፍጨርጨር (ያውም ከሳሾቹ በወጣቶች ላይ ወንጀልና ሽብር በማክሄድ የሚከሰሱ ሆነው) ከመደዴነትም በላይ ተራ ቀጣፊ መሆን ነው።   ወያኔና ጭፍሮቹ ነገ ጠባ ሊያጃጅሉን ልንፈቅድላቸውም ከቶም አይገባም።   ወርውረው ቢስቱት ያልጎዱት ይመስለዋል የተባለውን ሞኝ ሆነን ሁሌም ለወያኔ ሰለባ መሆናችን መቆም አለበት።

በተለምዶ አነጋገር ዕርቅ ያልፈለገን ገበሬ ንጉሥ አያስታርቀውም ይባላል። ዕርቅና ስምምነት ሲጠይቅ የነበረው ሕዝብ ከእንግዲህ በቃኝ ብሎ ባለበት ዕርቅ ብለው የሚዳክሩትንም ከመደዴ ፖለቲከኞች እንጨምራቸዋለን።

ገሞራውን ያስታውሰኛል፤

“አጥፍቸው ልጠፋ ከነቃም ሊያጠፋኝ፣
ደሙን ተዋህጄ ጉልጥምቱን ልል ሙጥኝ፣
በክስተቴ ገዘፍኩ ለመኖር ካልበጡኝ፣
ብልጡማ አያስጠጋም ምናልባት ሞኝ ባገኝ ….”

ደርግ ሊወድቅ ሰሞን አንዳንድ ሞኞች በቀቢጸ ተስፋ ተውጠው ለምንስ ኢሳያስ በአዲስ አበባ መሪ አይሆንም ብለው ሲጠይቁ ተደምጠው ነበር።   ኢሳያስም ባልደረባዎቹም አንዳንዶቻቸው ውልደታቸው ከወደ አድዋ ትግራይ ቢሆንም ለዓመታት ግንጠላ–ኤርትራ ብለው ታግለው ከመ ቅጽበት አንድ ጠዋት ኢትዮጵያዊ ሊሆኑ አይችሉም፤ አይታሰባቸውም፤ ቢከጅሉም ተከታዮቹ እሺም አይሏቸው።   ወያኔዎች በትግራይ የበላይነት የሚያምኑ፤ ጸረ አማራ ጸረ ኢትዮጵያ በመሆን የሸበቱ፤ ዘመን ያሳለፉ ናቸውና–የደነቆሩ ዘረኞች ናቸውናም–ዛሬ ሊለወጡ መጠበቅ ይወድቅልኛል በሚል በሬን እንደተከተለችው ዕንቁራሪት ከመሆን አያልፍም።   አይሆንም፤ አይከሰተም።   ያንኑ ዘረኝነታቸውን እስከ መጨረሻው በጎስቋላ በቅሎም ላይ ሆነ በከርካሳ ባሊላ ሊነዱ ነው ምኞታቸው።  የዘንድሮ ሞኞች ደግሞ ወያኔ አደብ ገዝቶ ከሕዝብ ሰምሮ ላለውና ለመጪው ቀውሱ መፍትሔ ሲፈልግ ይታያቸዋል። በጎ ገጽታ አሳየን ባሉ መንግስት በግድያው ሲቀጥልና አዋጅ ሲያዥጎደጉድም፤ የሽግግር መንግስት አይታሰብም ሲልም ሊማሩ ሊነቁ ያልቻሉ አሉ። በዚህ በዚያ ተስባስበው ጥራን እንጂ ጌታው ሊሉት ተዘጋጅተዋል።   በወያኔ ብሶ ሊጠራቸውም ሊሰማቸውም ከቶ ዝግጁ አልሆነም።  እስየው ብንል የሚፈረድብን አይሆንም።  በቅድሚት አጻውቶ፤ ብድሕሪት ዝመቶ –ከፊት አጫውተው፤  ከኋላው ዝረፈው–ወያኔዎች በሚገባ የሚያውቁት ተረት   ሆኖ ቆይቷል።  የማይሆንን ነገር ይሆናል ብሎ መታከቱ የሀገርን ጉዳይ የሚመለከት ከሆነ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው።  የይቻላል ይሆናል ሜዳ እንደ ፎገራ ሊሆን ቢችልም ሀቁ ሲከር ደግሞ ሽሮ ሜዳንም አያክልም ማለት እንችላለን።   ለዚህ ነው ወያኔ የአፈና አዋጅ ሲያውጅ ይኸው የምናውቀው ወያኔ ይህ ነው ብለን ስንቆይ ግን አደብ ገዛሁ፤ ሕዝብን አዳመጥኩ ሲል ምንድነው ይህ ጉድ፤ የምናውቀው የደደቢቱ ዘረኛውና አውሬው ወያኔ አይደለም ብለን የተናገርነው።  ተመክሮ አስተማሪ ነውና፤  ወያኔን ክምስረታው ጀምሮ በቅርብም፤ በሩቅም፤ በውስጡም፤ ካዩትም ከሰማነውም ሁሉ የምናወቀው ነንና። ለኢትዮጵያ ስለቆምን ከነአጋሮቹ ወግቶን ደም ተቃብተናልና። የጓዶቻችንና ብዙዎችን ደብዛ እስካሁንም አጥፍቷልና። ስለ ወያኔ ምንም ቅዠትና ድንግርግር የለንም።  መጥፋቱ ብቻ ነው መፍትሄያችን።  የግብረ ስየልን ክብረ ጭካኔ ጥሶ ያለፈው ወያኔ ይዟቸው ኢሰብዓዊ ስቃይን የተቀበሉ እስረኞችን ተመክሮ ማጤኑ ራሱ የወያኔን ጭራቅነትና ፋሺስትነት ገልጾ የሚያሰየን ነውና።

የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ልብስ እንጂ ድሪቶን አይፈልግም። ሳልቫጅ መሪዎችን አይፈልግም። በተግባር አይተናቸው ምንም ጥቅም ሊሰጡ ሳይችሉ ቆይተውና አልፎም ሀገርን ጎድተው የከረሙትን እንደገና ወደ ሥልጣን ቦታ ልናመጣቸው መታሰብ የለበትም። ውራጅ እንዲለብስ ሕዝባችን አልተፈረደበትም። ትላንት የት ነበሩ ስንል በደም ሲጨማለቁና ሀገርን ሲያስለቅሱ እንደነበሩ እያስታወስን እንደገና ግዙን ጨፍሩብን ልንላቸው አይገባንም። የቀይ ሽብር ወንጀለኞችን፤ ነፍሰ ገዳይ ወያኔዎችን፤ ሰብዕናቸውን መርካቶ የሚያወጡ ከሀዲዎችን ልናዳምጥም ሆነ መድረክ ልንሰጣቸው መታሰብም የለበት።  ለዚህም ነው ወያኔ እገሌን አንስቼ በእገሌ ልተካ ነኝና ትግሉን አብርዱልኝ ሲል ወግድ የምንለው።   እሳት ካየው ምን ለየው?

ገሞራውን እንደገና ልጥቀስ፤

“ጎርፍን ተገን አርጎ ዕቡይ ዋናተኛ፤
ጨዋ መስሎ ገብቶ ውስጠ ተንኮለኛ፤
እችላለሁ ብሎ ያሻጋሪ አታላይ፤
አርክሶ አጣላ ከኑሮ ሊያለያይ፣
ይህ ዓይነቱስ ታንኪር ደባ አይደለም ወይ?
በወርሃ -ማዕዶት የበቀለ እንጉዳይ!”

ሕዝብ ለፍርድ ሲመኛቸው፤ ታሪክ ለትቢያ ሲያጫቸው ተመልሶ በሥልጣን ቦታ ላይ ቁጭ እንዲሉ መፍቀድ የለብንም።  እገሌ እውነም የአመራር ችሎታ አለው፤ 27 ዓመት  ከወንጀል አውድማ ከርሞ ባለፈው ሰሞን  ወያኔን ወቀሰ፤ ደመቀ አቢይ ሆኖ ለሕዝብ ቆመ ወዘተ የሚባለው ሁሉ አሳፋሪ ነው። የዘወትር ጅሎች ናቸው ያሰኛል። ይህ ደግሞ ሀገር፣ ትግላችን የሚጠይቀው አቅዋም አይደለም። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ምሁሮች ሚና–በተለይም በውጭ ሀገር ያሉት–አጠያያቂ ከሆነ ቆይቷል ማለት እንችላለን። ሁሉም አለማለታችን ግልጽ ነው። ሕዝብን በመከፋፈል ርኩስ ዘመቻ ላይ ያሉ፤ ጸረ ወያኔን ማዕቀብ ለማደናቀፍ የሚጥሩ፤ ለባዕዳን ያደሩ፤ ሀገር ወዳድ ድርጅቶችና ሰማዕትን የሚዘልፉ፤ በአጠቃላይ ለወያኔ ያደሩትን ማለታችን መሆኑ ግልጽ መሆን አለበት።  በሀገራችን ኢትዮጵያ የረጅም የነጻነት ትግል ጉዞ ወጣቶች ምሁሮች ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፤አሁንም እንዳላቸው እያሳዩ ነው።   ሙሶሊኒና ግራዚያኒ የሀገራችንን ምሁሮች ፈጅተዋል።  ወጣት አርበኞች ራሳቸውን ጥቁር አንበሳ ብለውም ለለውጥም ለሀገር ነጻነትም ተሰውተዋል። የተራማጅ ተማሪዎችን ዴሞክራሲያዊ ትግልና የከፈሉትንም መስዋዕትነት ከየካቲት 66 አያይዞም መጥቀስ የሚቻል ነው። ደርግ የሚሉት ጭራቅ በሕዝብ ላይ ሲመጣም ወጣቶች በኢሕአፓ ጎን ተሰልፈው ለሽብርም ለነጻ እርምጃም ተዳርገዋል፤በትጥቅ ትግልም ከፍተኛ መስዋዕትነትን ከፍለው አኩሪ ታሪክን አስመዝግበዋል። ወያኔ ለስልጣን ሲበቃ፤ጸረ ኢትዮጵያዊው ቡትሮስ ጋሊ አዲስ አበባ ሲመጣ ወዘተ የሀገርን ጥቅም አስቀድመው ወጣቶች ደማቸውን በትግሉ አፍሰዋል፤ኢአግ ሲመሰረትም ጫካ ገብተው ወያኔን ተፋልመዋል፤ ወዘተ። ወያኔን ከአምስት አመት ጀምሮ በሙስሊሙ የመብት ትግል፤ ሆነ በጎንደር፤ ጎጃም፤ ወሎ፤ ሐርርጌ፤ ጂማ፤ ወልዲያ፤ አምቦ፤ ወለጋ ወዘተ ወጣቶች ትግሉን አፋፍመው ቀጥለው ወያኔን አንገዳግደው ወደ ውድቀቱ መርተው፤ አቅል አሳጥተውት፤ እንደ እብድ ውሻ እንዲጮህ አድርገውት ሊሸኙትም ተዘጋጅተዋል። አኩርተውናል ብንል ማጋነን አይሆንም።

ከዚህ ላይ የጎደለና በአሁኑ ጊዜም በጣም አሳሳቢ ሆኖ የምናገኘው አንድ ክስተት ደግሞ በአብዛኛው የትግራይ ወጣቶችና ምሁሮች፤ ንዑስ ከበርቴዎች በዚህ ሀገር አድን ሰልፍና ተቃውሞ ላይ አለመገኘታቸው ነው። ገና ከጠዋቱ በበኩላችን የትግራይ ሕዝብ የጭቆናውው ተረፍ መርፍ (ትርፍራፊ) በማግኘት የሕዝብ ጠላት ሆኗል ይል የነበረውን ፍረጃ አንቀበለውም ብለን በገሃድ ቆመናል። በተያያዘም ወያኔ ሻዕቢያ ብሎ ዜጎችን በዕብሪትና ኢፍትሓዊ መንገድ ከሀገር ሊያባርር ሲነሳ ተቃውመነዋል።  በትግራይ ሕዝብን በወያኔ መሃል ልዩነት መኖሩን ጫና በመስጠታችን እናንተማ ያው ትግሬዎች ስለሆናችሁ ነው ተብለንም ነበር።  የትግራይ ምሁሮች በአብላጫው የወያኔ ትምክህትና ዘረኛነት ሰለባ ሆነው ከሌላው ኢትዮጵያዊ ተነጥለው ሲቆሙ፤ በዘር ቆጠራ ሲሰማሩ፤ ተጨፍነው ሕዝብን ሲያስቀይሙና የትግራይንም ሕዝብ ለአደጋ ሲያጋልጡ ይህ አቅዋምና አካሄድ ወደ ጥፋት እንደሚወስዳቸውም ደጋግመን አሳስበናል።  እንበለውና “ክሱና ዘለፋው” ግን ከመርሃችን ፈቀቅ አላረገንም፤ አቅዋምም አላስቀየረንም።  ወያኔ ሶማሌውን በኦሮሞው ላይ በማስነሳትም ምን ያህል ደም እያፋሰሰ መሆኑንም አይተናል።   በዚህ ረገድ ጽንፈኛነትን–የማንንም ብሄረሰብ ቢሆን–የሚያራግቡትን ኢትዮጵያን ትጎዳላችሁና አቁሙ እንላቸዋለን።   ጽንፈኛነትን በጽንፈኛነት፤ ዘረኝነትና በሌላ ዘረኝነት ልንተካ መነሳቱ ለኢትዮጵያ ጉዳት እንጂ ስርየትን አያመጣም።   ለዚህም ነው በሕዝብ መሀል ክፍፍልና ጥላቻን ሊያስፋፉ የሚጥሩት ወያኔዎችና ሌሌች ጭፍሮቻቸውም ጸረ ኢትዮጵያ ናቸው የምንለው።  አማራው ከኢትዮጵያ ይገንጠል የሚል ሽንካላ ጥሪን ያስደመጡ የመቀሌ ውላጅና ምልምል አስመሳይ አማራዎችንም አልሰማንም?

በተያያዘም የወያኔን መሰሪና ጭካኔ የተሞላበት ስልት ሁሉ ማየት እንገደዳለን። ወያኔ ገነ ከጠዋቱ በሰርጎ ገብ ሥራ ሙሉ እምነት የነበረው ነውና–ይህንንም ከአለቃው ከሻዕቢያ የተማረው ነው –የሕዝብን ትግል ለማፈን ስለላና አደናጋሪ ፕሮፓጋንዳን በማሰራጨት ብዙ ጉዳት አድርሷል። ይህን ማድረጉ ወይም መሞከሩ በራሱ አስወቃሽ ላይሆን ቢችልም (ራሱን መጠበቅ አለበትና)  የሚሞኝለት ሰው ማግኘቱ ግን ነው ችግሩ። የአንድ ብሔር ድርጅት ዋና መሪ ለምሳሌ የወያኔ ደህንነት የወር ደሞዝ ተከፋይ ተቀጣሪ ነበሩ። ጊዜ ያለፈበትን ቅጥረኛን አስሮ የመልቀቅና ወደ ሕዝብ ጎራ፤ ወደ ድርጅት ማስጠጋትን ወያኔ እየሞከረው ከአንዴም ሁለቴ ሳይሆን ከዚያም በላይ ተሳክቶለታል። ልደቱ የተባለውን ለምሳሌ በሰላይነት ቀጥረው ወደ ኢሕአፓ ሊያስገቡት ብለው ሲያቅታቸው ወደ ቅንጅት በኢዴፓ ስም ከተው ጉዳት ማድረሳቸውን በቅርቡ አንድ የወያኔ ደህንነት አባል የነበር ነግሮናል። በጊዜው ይህን ሰው ተጠንቀቁ ብንል ቀንታችሁበት ነው ብለው ያወገዙንና ወያኔውን ያወደሱ ጥቂቶች አልነበሩም። ግለሰቡ ለይስሙላ ለወር ታሰረና ማንዴላ የሚል ቅጽል በወያኔ ገፋፊነት ተሰጥቶት ጉዳት አደረሰ።   ጉዮ የተባለ የቦረና ተወላጅ የወያኔ ተቀጣሪ ሆኖ ግን ታስሮ ተፈታ በሚል ሽፋን ናይሮቢ መጥቶ ጃተኔ አሊን (በኩረጽዮንን) ተጠግቶ በሆቴሉ ሁለት የወያኔ ነፍሰ ገዳዮችን አምጥቶ አስገድሎታል።   ሌላው ደግሞ ታስሮ ተፈቶ በሚል ናይሮቢ እነ ዲማ ነገዎን ተጠግቶ በድንበር ያለን የስልጠና ሰፈር ሳይቀር ካየ በኋላ ወደ ወያኔ ከድቶ ጦር አምጥቶ ሰፈሩን አስደምስሷል። ዛሬም በዚህ ዓይነት በየድርጅቱ የተሰማሩትን አጥፊዎች ማንነት ለሚመለክታቸው ድርጅቶች ብንጠቁምም ጆሮ ዳባ ብለው እንዳሉ የሚታወቅ ነው።  የጠላትን ጥቃት ለመከላከል እጅ አጥፎ ከመጠበቅ ይልቅ ጠላትን ሰርጎ ገብቶ ተንኮሉን ማወቅና ማክሸፍ ስምሪት ራሱን የቻለና በደርግ ጊዜም በድርጅት ደረጃ በስራ ላይ የዋለ ነው። ጽንፈኞች የሚያደርሱት ጉዳት ግልጽ ሆኖ ሳለ ጽንፈኝነትን ወያኔ ራሱ እንደሚያበረታታ የምናውቀው ሲሆን ሌሎች ደግሞ በይፋ አማራን እረዱ ለሚሉት ወፈፌዎች ሁሉ መድረክ ሲስጡ ቆይተዋል።  ካምፓላ ዩጋንዳ በነበርኳብቻው ዓመታት የወያኔ የኬንያ እምባሲ የጸጥታ ሀላፊ የነበር ግለሰብ (አሁን በውጭ ጉዳዩ ሚኒስቴር አዲስ አበባ ይሰራል ) በካምፓላ የነበረን አንድ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት የኢሕአፓ ንብረት ነው ብሎ በመጠርጠሩ በምግብ ቤቱ በአሳላፊነት ይሰራ የነበረን ወጣት ስደተኛ ልጅ መልምሎ እንዲሰልለን በቀጠረበት ጊዜ በመኪና ከከተማ ውጭ እየወሰደ የሰጠው ስልጠና ትዝ ይለኛል።  ልጁ ልቀጠር ወይ ብሎ ሲጠይቀን አዎንታዊ መልስ ሰጥተን የወያኔንም ክፍያ ለስደት ኑሮው እንዲያውለው ነግረነው የወያኔ ወሬ አቀባይ ሆኖ ቢያንስ ለዓመት ሰርቶ ነበር። ወደ ስልጠናው ስመለስ ወያኔው የነገረው፤

1) እነማንን መሰለል እንዳለበትና ከውጭ ሀገር ወደ ምግብ ቤቱ የሚመጡትን ስም ማወቅ፤

2) ድርጅቶች ሆኑ ቡድኖች ገንዘብ አዋጣ ሲሉት (እኔ በኋላ እተካልሀለሁና ) በሚገባ አዋጣ፤

3) ጸረ ወያኔ ብቻ ሳትሆን በአቅዋምህ ጸረ ትግሬ ሁሉ ሆነህ መገኘት አለብህ፤ ወዘተ የሚል ነው።

ጽንፈኞች የሚቀፉኝ ለዚህ ነው ብል አንዱም ምክንያት ነው።  ነገሮችን በሃይል ወጥረው ሚንደገደጉ ብዙውን ጊዜ ተልእኮ እንዳላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተግ ተግ ያሉትን የአማራን ኦሮሞ ጽንፈኞች ሚና ማጤኑ ይበቃናል። ከእኛም በላይ ጸረ ትግሬ ለአሳር እያሉ ፤አማራና ክርስቲያኑን መጨረስ ነው ሲሉና ከወያኒና ተለጣፊዎቹም ጋር መተቃቀፍን ሲሰብኩ እየተደመጡ ነው።  ዋና ስራቸው ግን ሀገር ወዳድ ድርጅቶችን ማራከስና ሕዝብን እርስ በርስ ማጋጨት ሆኖ ይገኛል።  በሌላ በኩል ወደ ራሳችን ተመክሮም ስንመለስ ኢሕአፓን ጣኦት ወይ ታቦት ያደረጉት ወደ ቀቢጸ ተስፋው ለመግባትና ለመጨቅየትም የመጀመሪያዎቹ ነበሩ ማለት እንችላለን።

የኢትዮጵያ ወርቅ ልጅ ገሞራው ሲተች የጻፍው ወደሚቀጥለው ይወስደኛል፤

“ለውጥ አለ ይሉናል ሰማን እንጂ አላየን፤
ባላገር እኛ እንጂ እንዳለነው አለን፣
ሙቀጫና ወፍጮ ቁናና እንስራ እያላገጡብን።”

ኤኮኖሜው አደገ ተመነደገ ይላሉ–ልፈፋቸውንም የዓለም ባንክና የአሜሪካው መሳሪያ አይ ኤም ኤፍ  ያስተጋባሉ። ወያኔ የምዕራቦቹ መናጆ ነውና ያዳንቁታል። የአንድ ሀገር ኤኮኖሚ አደገ ተመነደገ ሊባል የሚችለው የሕዝብን ድህነት እየቀረፈ ብዙሃኑን ለብልጽግና ሲያደርስ ነው። ሀገር በተጨባጭ ለሕዝብ በሚጠቅም ይዘት ሲያድግ ነው። መብራት አልባ፤ ውሃ አልባ ግም ሕንጻ ሲሰራ አይደለም። ቀለበት መንገድ ሰራን በሚል መመጻደቅ ሲሰፍንም አይደለም። የሀገራችን ብርቅዬ ልጆች መንገድ አዳሪ ሆነው የከተማ ባቡር ሰራሁ በማለት አይደለም። ለም መሬታችን ለባዕዳን ሲሸጥ ሲሰጥ አይደለም። ለተራበ አንጀት ጥይት ሚሰጥበት ሀገር መሆን አይደለም። የተወሰኑ የትግራይ ተወላጅ አዜቦች የሚሊዮን ዶላሮች ባለሀብቶች ሲሆኑ ማየት አይደለም። የስቃይና የድህነት ኑሮ ዕጣ ክፍላችን ሆኖ ሲያጀብን ቆይቷል እንጂ ለውጮቹ የሚታየው ዕድገት ብልጽግና ለኛ እንደተሰወረ አለ። ላም አለኝ በሰማይ። የእኛን ችግር የምናውቀው እኛ ብቻ ነን። ወደ ሀቅና ታሪክ መለስ ብለን ስንቃኝ ደግሞ የነበረውና የሚወሸከተው ከነበረው ተቃራኒ ሆኖ እናገኘዋለን። ወያኔ ሆነ የፖለቲካ መደዴዎችና የታሪክ በራዦች የሚያቀርቡት ዓይን አውጣ ቅጥፈት ሆኖ በገሃድ ይታያል። ፋሺስቱ መንግስቱ ንግገር ብሎ በሰፊው በአሃዝ ሲያደነቁረን የሚታመን ቢሆን ኖሮ ሀገራችን በዴሞክራሲም በብልፅግናም ተጥለቅልቃ ነበር። ሟቹ መለስ ኢትዮጵያ ብሎ መጥራት ቢተናነቀውም በሁሉም አቅጣጫ ዓይኑን በጨው አጥቦ መዋሸቱ ቅንጣትም አልከበደውም ነበር።  የኢኮኖሚ ዕድገት ሳይሆን ጣራን የበጠሰ የኑሮ ውድነት ሰፍኖብን እንደከረመ ገፈት ቀማሹ ሕዝብ ያውቃልና የፈረንጅ የተጭበረበረ አሃዝ አያደናግረውም።   ችግርሩን የሚያውቀው ሕዝብ  ይኸው አሁን ድህነቱና ስቃዩ፤መብት አልባነትና በገዛ ሀገሬ ተገዢ ተጨቋኝ መሆኑ ሰለቸኝ ብሎ ተነስቶ ታሪክን መጻፍ ማጻፍ ተያይዟል።  የነ አዜብ ድሃ ነን፤ሀገሪቷን አልዘረፍንም የምጸት ሳቅ አሳቀው እንጂ አላሳሳተውም ። ሀገራችንን ስናስመልስ ሀብታችንም ተመላሽ መሆኑ አይቀርምና ትኩረታችን ወያኔን አስወግዶ ሀገርን ማስከበር፤ ማስመለስ ላይ መሆኑ አስፈላጊ ነው።

ይህም የጋራ ትግላችን፤ ሕዝብ ተያይዞት ያለው ትግል በጀመረው ሀዲድ ላይ መጓዙን ይጠይቃል። አሁንም በዘር በክልል ትግሉን ከፋፍለው የግል ና ውሱን ጥቅማቸውን ሊያሟሉ የሚጥሩ አሉ።  የጋራውን በተከፋፈለ ለመተካት፤ ኢትዮጵያ ያለውን ወደ ጎጥና ብሄረሰብ ደርጃ ለማውረድ፤ህብረት የተባለውን የድርጅትና ቡድን ፉክቻ እንዲተካው ለማድረግ።  ገና ከደይኑ አልወጣንምና፤ጠርጣራ ሆኖ መቆምን ግድ ይላልና መዘናጋትን አሽቀንጥረን መጣል ማስወገድ አለብን።   ወያኔ ለዕርቅ ሲለመን አሻፈረኝ ብሎ ለዓመታት አላግጧል፤ አሁንም አልተቀየረም።   ከባልሽ ታረቂ ቢሏት ልመና መሰላት እንደተባለው ነው።   ወያኔን ሰላምና እርቅ ሲሉት የተፈራ መስሎት አበየብን።   ለውይይት ከውጭ የመጡትንም አስሮ ከርቸሌ አወረደ።   ይህንን አጢኖ በጉንጭ አልፋ ድርድር ለመድከም ከመንደርደር ይልቅ ጸረ ወያኔን ትግል ማፋፋም አስፈላጊ መሆኑን በተደጋጋሚ ተገልጿል።   እርቅ ደም ያደርቅ ይል የነበረው ሁሉ እርሙን ማውጣት ተገዷል።   ከግባችን ለመድረስ ህብረት ያስፈልገናል፤ ይህን ጥረት የሚያደናቅፉትንም ማግለል ማቸነፍ ይጠበቅብናል።   ህብረት አስፈላጊነቱ ወያኔን ለመጣል ብቻ ሳይሆን ከወያኔ ውድቀት በኋላምም ህዝብን ወሳኝ የሚያደርግ የሽግግር ሂደትን እውን ለማድረግም ነው።   አንድ ድርጅት የሚፈነጭበት ሳይሆን እንደ 1983ኡ፣ ሁሉም ሀገር ወዳድ ድርጅቶች ተሰባስበው የሚመክሩበትና ዋናውን ውሳኔ ለሕዝብ የሚተዉበት።   ከዚህ የተለየ ሽግግር ሊታየን አይገባም። አሊያማ ወያኔ ያጠመደብን የብጥብጥ ፈንጂ ሁላችንንም ለጥፋት ይዳርገናል።

ህብረት ወያኔን ለማስወገድ።   ህብረት ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ሽግግር።   ወሳኙ ዛሬም ቢሆን ነገ ሕዝብ ብቻ ነው።

ገሞራው ኃይሉ እንዳለው፤

“ወጋ ወጋ አድርጎ እዚያም እዚህ ምድር፣
የኔም ሆነ ያንቺ ግዴታ እኮ ነበር!
ማንም የጣለውን እንደገና ማጠር።”

ወያኔን እናውድም !!