የአካለ ስንኩል አሽከር ተጎንብሶ ይራመዳል

በፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምፅ ራዲዮ  በመጋቢት 20 ቀን  2010  ዓም  የተላለፈ  ሐተታ
logo
አንድ  የድኩማን አሽከር የሆነ ሰው፤  ተጎንብሶ መራመዱን  የተመለከቱ  ሌሎች ሰዎች ፤ ይኽንን ርምጃ ምን እንዳስመረጠው  ቢጠይቁት፤ “ጌቶቸን ቀና ብየ ለማየት ነው።”  ብሎ መለሰላቸው ይባላል።  አካለ ስንኩል  ከመሆን   ይበልጥ የሚታዘንለት፤ የአዕምሮ ድኩማን ሰው እንደሆነ፤ የሥነ አዕምሮ ጠበብት ይስማሙበታል።  ከጌታው የአካል ስንኩለንት ይልቅ፤ የእርሱ  የአዕመሮ ደካማነት  በእጅጉ ያሳዝናል። ይኽ ሰው፤ ለመኖር ሲል አጎንብሶ በመሄዱ ሰብዕናውን ተዝብት ውስጥ ጥሎታል።  የአዕምሮ ደካማነት፤ እንደ አካለ ህመምተኛነት  በቀላሉ ፈውስ  የማይገኝለት ይሆን ይሆናል፡፡    ተፈውሷል ሊባለለት ቢሞከርም እንኳ፤  በተሟላ መልኩም ሆነ በአስተማማኝ ደረጃ  ሙሉ ጤንነቱ ለመመለሱ ማረጋገጫ መስጠት አይቻልም። ምናልባት ጊዜና ቦታ እየጠበቀ የወፈፍተኛነት ባኅርዩን ማንፀባረቁን አይተውም ይሆናል። በሀገር ጥላቻ ልክፍት የተበከለም እንዲሁ ነው።  ብከለቱ ለሀገር ለወገን ሳይተርፍ መወገድ አለበት።  በጊዜ ካልተወገደ ደግሞ ከመቆየቱ  ብዛት፤ የገገነውን ከይሲ ጠላት በኋላ ማስወገድ ቀላል አይሆንም።

ዛሬ ሀገራችንን የሚገዟት ወያኔዎቹና አገልጋዮቻቸው  በዘር በሽታ የተበከሉ በመሆናቸው፤ ኢትዮጵያን፤ በጥላቻ ዐይን ከማየት  በስተቀር፤ በጎ ባኅርይ ሊይሳዩ አይችሉም።  በዚህ ምክንያት አላስፈላጊ  ጦርነት ውስጥ ገብተዋል።  አሸከሮቻቸው ሳይቀሩ አጎንብሰው እንዲሄዱ የተገደዱበት ምክንያት፤  የራሳቸው ኅሊና ተገዥ ለመሆን ባለመቻላቸው ነው።  የራስ ኅሊና ተገዥ ሳይኮን፤ ሀገርን ያኽል ግዙፍ ነገር መግዛት የሚቻል አይሆንም። የራስ ኅሊና ተገዥነትን  ማረጋጋጥ  መቻል ፤ የሀገር መሪ ለመሆን ከሚያስችሉ ባህርያት አንዱ ነው።

የወቅቱ ባለሥልጣናት ነን የሚሉ ግለሰቦች፤ ቀና ብሎ መመልከት የሚያስችላቸው ሰብዕና ስለጎደላቸው ፤ ከሕዝብ ጋር እሳትና ገለባ ሆነዋል።   እሳትና ጭድ አጥፊና ጠፊ እንጅ፤ ተስማምቶ መኖር አይቻላቸውም። ዛሬ  የኢትዮጵያ ሕዝብ  ትግል  እሳት፤  ወያኔዎቹ  ጭድ ሆነው በመጥፋት ሂደት ላይ ይገኛሉ። ወያኔ ካልጠፋ ሀገር ሠላም  አታገኝም።  የሀገርን ጥፋት ለማስቀረት የሚቻለው፤  ሀገር፤  አስተዋይ ህሊና ያላቸውን መሪዎች ማፍራት ስትጀምር ነው።

ለችግራችን መፍተሄዎች  ሊገኙላቸው ከላስቻሉን ምክንያቶች አንዱ፤ የችግሩ መፍተሄዎች ናቸው ተብለው የሚቀርቡት
ዘዴወች  ሁሉ መፍተሄ ለማስገኘት ብቃት ስለሌላቸው ነው።  በዚኽ የተነሳ፤ ከወያኔ ጋር በመሆን መፍተሄ እንፈልግ
ወደሚል  አመለካከት እየተሄደ ነው። ይኽ ደግሞ፤ “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል። ” እንደተባለው፤ መፍትሄን አይወልድም።

መፍትሄ ባለማግኘታችን፤ “ምላጭ ቢያብጥ፤ በምን ይበጡ?   ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡ? ”   በሚል እንቆቅልሽ ውስጥ ገብታ  የምትገኝ  ሀገር  ነዋሪዎች ሆነን  ቀርተናል።  ህመምተኛው፤ ታማሚው ብቻ ሳይሆን፤ መዳህኒቱም  ጭምር እራሱ  ህመምተኛ ከሆነ፤ ማን ፈዋሽ? ማንስ ተፈዋሽ? ሊሆን ይችላል? ምላጩ ካበጠ፤ ማን ይበጠዋል!  ዉሀው ካነቅስ፤  በምን ይዋጣል!  የችግሩን  መፍቻ  ያመጣል  የተባለው መሳሪያ፤ ራሱ ችግር ላይ ከወደቀ፤  የራሱን ችግር ለመፍታት ቁመና ስለማይኖረው፤ የሌላውን ችግር የፍታል ተብሎ አይታሰብም፡፡   የሀገራችን ወቅታዊው ሁኔታ ይኽንን ክስተት  የሚያንፀባርቅ ሆኗል።

“ለማኝ ሲያጣ ተሳድቦ እንደሚሄድ “ሁሉ”    የወቅቱ ገዥዎችም ሥልጣናቸውን ሲያጡ የሀገሪቱን  ሀብትና ንብረት
አወዳድመው ከመሄድ በስተቀር ሌላ ምርጫ አይታያቸውም።  የሀገሪቱ መሠረታዊ ችግር ፈጣሪዎች መሆናቸው እየታወቀ ፤
ከወያኔዎቹ ጋር መደራደር መፍተሄ ያመጣል ብለው የሚመኙ ቡድኖች መኖራቸውን ሲገነዘብ፤  የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሩን
ችግር ሊፈታ የሚችለው እርሱ እራሱ ብቻ መሆኑን ካመነበት ውሎ አድሯል።

ወያኔዎቹ፤ አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ብቻ የሚያስቡ እንደመሆናቸው፤  “ኢትዮጵያ የአንድ መቶ ዐመት ዕድሜ ያላት
ሀገር ነች” የሚለውን ለማጣጣም  በሚመስል መልኩ፤ ዛሬ፤ አንድ መቶ የፖለቲካ ድርጅቶች የተኮለኮሉባት ሀገር ሆናለች።
መደራጀት በራሱ ክፋት ነው ለማለት የማያስችለው፤ ኅብረትሰብ፤ በፈለገው መልክ መደራጀቱ የዴሞክራሲ መብቱ ስለሆነ ነው። ቢሆንም፤ ከብዛት ጥራት ካልተገኘ፤ “የዝምብ መጥራቀም ወስከንቢያን አይከፍትም።” ወደሚለው ይትብሃል ሕዝቡ እንዲሄድ ይገደዳል።  ጥራት ኖሮት፤ በጥራት የሚያምን ድርጅት ካለ፤ ቢኖር፤ በጥራት የታጀበ ጥራት ያለው መፍትሄ ማምጣት የሚቸግረው አይሆንም ነበር። እስካሁን ድረስ ግን ጥራት ያለው ሥራ መከናወኑን ለመገንዝብ  የኢትዮጵያ ሕዝብ አልታደለም።

ምናልባት፤ “የወጥ ሰሪዎች  መብዛት ፤ የምግቡን ጣዕም ደረጃ ዝቅ ከማደርጉም በተጨማሪ፤ የአሳላፊዎች ብዛት ድግሱን ለማበላሸት የራሱ አስተዋፃኦ  ይኖረዋል እንደሚባለው ሁሉ፤ ለአንድ ሀገር ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች  ከሚገባው በላይ  መብዛት፤ በሀገራችን ፖለቲካ  አግማስ  ላይ  ያን ያኅል አሉታዊ  አስተዋጽኦ  አይኖረውም ማለት አይቻልም።  የወቅቱን  ሀገራዊ ፖለቲካ ሁኔታ በቅርብ ለሚከታተል አስተዋይ ተመልካች፤ ሦስት ፍትጊያዎች እርስ በእርሳቸው እየተራኮቱ  እንደሆኑ መገንዘብ  አይቸግረውም። እነርሱም፤

1ኛ.  ሀ.  ኢሕአዴግ በተሰኘው ስብስብ የተኮለኮሉት   ሦስት ተጠማጅ ድርጅቶች፤ ከወያኔ ባርነት ነፃ ለመውጣት የሚያደርጉት ያልተመጣጠነም ቢሆን፤ ትግል እያደርጉ መምጣታቸው ነው። ወክለነዋል የሚሉትን ሕዝብ ከወያኔ አገዛዝ ለማውጣት እንችላለን ብለው  ይመኛሉ።  መፍጨራጨው  ባልከፋም ነበር። ነገር ግን እራሳቸው ነፃ ሳይወጡ ብሄራቸውን ነፃ ማውጣት ስለማይሆንላቸው፤ መጀመሪያ ከወያኔ ባርነት ራሳቸውን ነፃ ያውጡና፤ ወደ ሕዝቡ ትግል እንዲቀላቀሉ  መወሰን አለባቸው። ራሱን ነፃ ያላወጣ ሌላውን ነፃ ሊያወጣ አይችልም።

ለ.  የወያኔ/ ሕወኃት  መሪዎች፤ የሕዝቡን ዐመፅ በአግባቡ ለመቋቋም አቅምና ቁመና ስለአነሳቸው፤ በኃይል ብቻ እንመልሰዋልን በሚሉት ቡድኖችና ሌላ መፍትሄ ይፈለግለት ብለው  በሚፍጨረጨሩት መካከል የሚደረገው ትግል፤ በአርምሞ  የሚታይ   ክስተት  አይደለም።

የሕዝቡ ትግል እያየለ በመጣ ቁጥር በወያኔዎቹ ጓዳ ምስቅልቅሉና ውጥንቅጡ እየተበረከተ መሄዱ አይቀሬ ነው።      የሁለቱ ጽንፈኞች ፍትጊያ  ያተኮረው፤ ያው ዞሮዞሮ በሥልጣናቸው የመቆየቱ ጉዳይ ነው። ማነኛቸውም ቢሆኑ፤ ስለ ሀገሪቱና
ሕዝቧ ጉዳይ የተለየ እሳቤ ሊኖራቸው አይችሉም። የትኛው ቡድን የበላይነት እንደሚይዝ  ግን በእርግጠኘነት መናገር
አይቻልም።

ሕዝባዊው ዐመፅ እየበረታ በመጣ ቁጥር፤ ከላይ  የተጠቀሱት ቡድኖች ሀገራዊ ትግሉን ለመቋቋም ከማይችሉበት ደረጃ
መድረሳቸው አይቀሬ ነው። በተደጋጋሚ የሚያውጁት አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ፤  የቱን ያኅል ቢርመሰመስም ፤ በሥልጣን
ለመቆየት ዋስትና የሚሰጣቸው አይሆንም። ለሕዝባዊው ትግል መንበርከካቸው ግን አያጠራጥርም።  መደምደሚያቸው
ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

2ኛ.    ዋነኛውና ወሳኙ ትግል፤ በመላው ሕዝብ በመካሄድ ላይ ያለው ሀገራዊ ዐመጽ ሆኗል ። ይኽ ዐመፅ ወሳኝ ነው።
በሀገሪቱ የወደፊት እድል የሚያመጣው መሠረታዊ ለውጥ ስትራተጃዊ ነው። የመቶ ሚሊዮን ዜጋና የሀገሪቱን ሁለንተናዊ
ሕይወትና ጥቅም በአውንታዊ መልኩ ለመወሰን  ብቸኛ ዐቅም ይኖረዋል።

ይኽ ስለተባለ  ግን ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ነው  ማለት አይደለም። ብዙ የሚጠበቁና ያልተጠበቁ መሰናክሎች
እንደሚገጥሙ ሁሉም በትኩረት ሊመለከተውና  ሊከታተለውም ይገባል ። የሀገራችን ጉዳይ ውስብስብነትና ውጥንቅጥነት ፤
በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም።  ያገባኛል የሚለው ባለድርሻ  ሁሉ ሙሉ ተሳትፎ ሊያደርግ ይጠበቅበታል።   የሁሉም
ግብኣት መካተት ወሳኝነት አለው። አግላይና ነጣይ ፖለቲካ  ለወደፊቱ የሀገራችን  መፃዒ  ዕድል አሉታዊ ሚና
እንዳይኖረው፤ ካሁኑኑ ብርቱ ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል።  ውሃ በቀጠነ እያኮረፉ በሀገራዊው ትግል ላይ  ሳንካ ሊፈጥሩ
የሚሞክሩት ፀረ አንድነት ኃይሎች ፤  ሀገራዊ ትግሉን  ለማሰናከል ምክንያት እንዳያገኙ  ማድረግ ተገቢ ነው።

ይኽ ሁሉ እንዳለ ሆኖ፤ የውጭ ኃይሎች  በኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ጉዳይ ጣልቃ የመግባታቸው ጉዳይ በአርምሞ
የሚታይ  ጉዳይ አይደለም።  ምንም ጊዜ  ቢሆን .ሀገራችን ከምዕራባውያኑ ጣልቃ ገብነት ነፃ ላትሆን ትችላለች ብሎ ማሰብ፤
ጠቃሚ ነው።  ለሀገር ስትራተጂያዊ ጥቅም የሚያስብ ሁሉ፤ የውጭ ጣልቃ መግባት ዐደገኛነትንና የሚያስከትለውንም
ጠንቅ፤ ሁል ጊዜ ጠንቅቆ ማወቅ ይገባዋል ።

ምዕራባውያኑ በአስራ ዘጠኝ  መቶ  ሰማኒያ አንድ /1981 ዐመተ ምህረት ሎንዶን  ውስጥ በሀገራችን ላይ የከፋቱትን  የአጋንንት በረት ዛሬ መዝጋት ተስኗቸዋል።  ያ ሎንዶን ላይ የሰደዱት  ዐውሬ  ይኽው ዛሬ  ሀገርችንን እያደማት ይገኛል። በመሆኑም፤ ሀገራችን፤ ነፃነቷንና ማንነቷን ደፍሮ  ያስደፈራትን ባለጋራ ለማስወገድ የሞት -ሽረት ትግል በማድረግ ላይ ትገኛለች ።

አመፀኛውን  ሥርዓት በአመጽ ማሰገድ ስለአለባትም ነው ሕዝቧ ከአጽናፍ እስከ አፅናፍ የተባበረ  ዐመፅ ማድረጉን ብቸኛ
አማራጭ አድርጎ የተነሳው።  የተባበረው ሀገራዊ ትግል፤ በስቸኳይ  ዐዋጅ  ሊገታ እንደማይችል የተረጋገጠ ሀቅ ሆኗል።
ሠፊዋን ሀገርና ታላቅ ሕዝቧን  እንዲህ  በቀላል መግዛት እንዳማይቻል ወያኔዎቹ አሁን ገብቷቸዋል። ያ ማለት ግን
ወድደው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ወስነዋል ማለት አይደለም። ወገባቸው እንጅ ጭቅላታቸው ገና ስለአልተመታ፤
መፍጨርጨራቸው አይቀርም። በመጨረሻው ሰዓት፤ በተባበረው ሕዝባዊ ዐመፅ መወገዳቸው ስለማይቀር፤ የተጀመረው
ሕዝባዊ  ዐመፅ ተጠናክሮ ከመቀጠል ሌላ አማራጭ የለም።

ከወያኔ ጋር መደራደር ይሻላል  የሚባለው  አርሲ-ኩርሲ ፤ ትጥቅ አስፈችና አቅጣቻ አሳሳች መሆኑን ተግንዝቦ  ሀገራዊ
ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠል አማራጭ የለውም። ሕዝባዊው ዐመፅ በሚካሄድበት ወቅት ግን የሚከተሉት  መሠረታዊና ዘላቂ
የሆኑት ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው  ይገባል። እነርሱም፡

1ኛ. ሀገራዊው ትግል አንድነቱን አጠንክሮ መቀጠል አለበት። የአንድነቱ-ሀገራዊው ትግል፤ አሸናፊነት ለነገዋ ኢትዮጵያ  ሀገራዊ አንድነት መሠረት ጣይ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

2ኛ.  ትግሉ ያነጣጠረው፤ ወያኔን  በማስወገድ ላይ በመሆኑ የወያኔ የበላይነት እስኪወገድ ድረስ በጽናት መቀጠል አለበት።

3ኛ   ሀ.  የትግራይን ሰፊ ህዝብ ከወያኔ ለይቶ ማየት የሁሉም ዜጋ ተግባር ነው። አጥፊውን ከንጹሁ መለየት ከታሪክ ፍርድ ነፃ ያዋጣል።

ለ.  መላው የትግራይ ሕዝብ  ከቀሪው ወገኑ  የኢትዮጵያ ሕዝብ  ዐመፅ  ጎን ተሰልፎ ፤ ሀገራዊ ትግሉን አብሮ   በማካሄድ
ድርሻውን መወጣት ይገባዋል።

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!