ቆንጆ የሁሉም ናት

አሥራደው (ከፈረንሳይ)

 

አንደኛው  አግኝቶ፣  ውዴ  ፍቅሬ  ሲላት፣

ሌላው  በማጣቱጧት  ማታ  ሲመኛት፣

የውበት  ዕድምተኞች፣  እያዩ  ሲያደንቋት፣

ያላየው  እያየ፣  ውበቷን  ሲጎመዥ፣

ምኞቱን  ለማስመር፣  ዐይኑ  ሲንቀዠቀዥ፣

የሰማው ላልሰማ፣ ዝናዋን ሲረጨው፣

በውበት ረሃብ፣  ምራቁን ሲያስውጠው፣


ያገኛት ሲጨፍር፣  ልቡ ጮቤ ሲረግጥ፣

በውበቷ ነዶ፣  በውበቷ ሲቀልጥ፣

በምኞት ጧት ማታ፣ ያጣት ሲቁነጠነጥ፣

አካሉ ሲፈላ፣ ጨጓራው ሲመለጥ፣

በድንገት ያያትም፣ አድናቆት ሲቸራት፣

መች ያለ ምክንያት፣ ቆንጆ አርጎ ፈጠራት ?!

ነው እንጂ እንዲያደንቃት፣

ሁሉም እንዲመኛት ::

የራሱን ተፈጥሮ፣ የራሱን ማንነት፣

እንዲችል ለማየት፣

በቆንጆዋ ውበት።

ከጥንቱ ሲፈጥራት፤

አረጋት መስታወት፤

ለራስ መመልከቻ፣ እኔስ ማነኝነት ::

 

ስለዚህ !

የሚታይ ተፈጥሮ፣ የሚናፈቅ ውበት፣

እንዴት ተደብቆ፣ ይቀራል ከማጀት ?!

ወቶ ባደባባይ፣ መታየት አለበት፤

መደነቅ አለበት !!

እናም !

ቆንጆ የሁሉም ናት !

ማነው የስስታም፣ ያንድ ሰው ያረጋት ??!!

ለመላው ሴት ልጆች መታሰቢያ ትሁንልኝ ታኅሳስ 10 ቀን 2002 .. (19 /12/2009)

ከስንኟ ቋጣሪ ሃሳብ መወራወር ለሚሹ asradew@live.fr ያገኙታል ::