በፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ: ኢትዮጵያ፤ እንደማነኛውም ሀገር፤ የራሷ መጥፎም ሆነ መልካም ታሪክ ነበራት/ አላት። የጥቃትና የድል፤ የጥጋብና ረሀብ፤ የስፋትና የመጨራመት፤ የመከራና ሀሴት ዘመናት ሁሉ ተፈራርቀውባታል። የተለያዩ ሥርዓተ- ማኅበራትንና ገዥዎችን ሁሉ አሳልፋለች። ድንበሯ ያልተደፈረ፤ ታሪኳ የተከበረ፤ ሉዓላዊነቷ ያልተገሰሰ፤ የንግድ መናሃርያዋ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ የተዘረጋ፤ ኃያል ሀገር ነበረች። የጦርና የንግድ መርከቦቿም በውቅያኖሶችና ታላላቅ ወደቦች ይንሳፈፉ ነበር። ያ ሁሉ ዛሬ፤ ነበር ሆኖ አልፏል! “የነበር ሲያወሩት ይመስላል ያልነበር፤ የኢትዮጵያ ጠረፍ ውቅያኖስ ነበር!” እያሉ መናገር፤ የዕለት -ተዕለት ቁዘማ ሆኖ ቀርቷል! ታሪካዊና ነባራዊ ሀቆች ግን እነኝኽ ናቸው!
ዜጎቿም በነኝህ ተፈራራቂ ሥርዓተ- ማኅበራትና ስልተ-ምርቶች ሂደት ተጉዘዋል። ያም ሁሉ ሆኖ እስካሁን ደረስ፤ የራሳቸው ዕድል ባለቤቶችና ወሳኞች አልሆኑም። በዚህ በያዝነው 21ኛው ክፍለ-ዘመን እንኳ፤ የዴሞክራሲ ጭላንጭልን ሊጎናጸፉ አልቻሉም። የነፃነትና ፍትኅ-ርትዕ ዕጦት አሉባቸው። የጉስቁልና ኑሮ የህይውታቸው መቆያ፤ ረሀብና ስደት፤ የማንነታቸው መለያ መሆኑን ድፍን ዓለም አውቆላቸዋል። እነርሱ ግን ወዴት እንደሚሄዱ ብቻ ሳይሆን፤ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እንኳን የተገነዘቡት አይመስልም። ሙሉውን ሀተታ ያንብቡ