ተገኜ ሞገስ የቂጣው መቀስ: ግላዊ አጭር የጓድ ትውስታ


ኢያሱ ዓለማየሁ – ጓድ ተገኝ ስንለው “ኝ” ን አጥብቅልኝ ማለት ብቻ ሳይሆን ራሱን “ተገኜ ሞገስ የቂጣው መቀስ” እያለ ያስቀን የነበረውን ጓዳችንን ባለፈው ሳምንት ሞት በድንገት ነጥቆናል፡፡ ያኔ ያኔ ወደ ካርቱም ሱዳን ሲመጣ ገዳሪፍ ወይም ሜዳ ስለነበርኩ አልተገናኘንም፡፡ በካይሮ ግብጽ እንዳለ ግን አውቅ ነበር፡፡ የትግል ስምሪታችን ቦታዎች የተለያዩ ሆነው በአንድ ድርጅት ስር ብንሰለፍም በአካል የተገናኘነው ቆይቶ ነው፡፡ ጓድ ተገኜ እዩኝ እውቁኝ የማያበዛ በመሆኑ በመጀመሪያ የነበረኝ ግምት የማይስቅ የማይጫወት ቆምጫጫ ምናልባትም ደባሪ ሰው ነው የሚል ነበር፡፡ ተገኜ ግን ተጫዋች ብቻ ሳይሆን በራሱም ላይ የሚስቅ፤ የቂጣው መቀስ የሚል ሆኖ አገኘሁት፡፡ በበኩሌ ራሳቸውን አግዝፈውና ዙፋን ሰጥተው ከሁሉ በላይ ነን የሚሉ ከጥንትም ያሙኛል፡፡ ዶክተር፤ ኢንጂኔር፤ ፕሮፌሰር ወዘተ ታፔላን ለጥፈው ከሁሉም በላይ ልሂቅ አዋቂ ነን ብለው የሚኮፈሱት ላይ በፊትም ዛሬም ያለኝ ድምዳሜ አሉታዊ ነው፡፡ ፖለቲካ ዘቅጦ ዘቅጦ እነማን ፖለቲከኞች ተብለው እንዳሉ ስናይ ብናፍር አይፈረድብንም፡፡ በራሱ ላይ መሳቅ የማይችልና ተደብሮ የሚደብር ካባ ለባሽ የሆነ በትግሉ መስክ ዘለቄታ አይኖረውም የሚል ድምድሜ ይስማማኛል፡፡ ተገኜ ሁላችንንም “አባዬ”ና ሴት ጓዶችንም “ማሚት” ማለት የሚወድ ስለነበር ለሁላችንም ስሙ አባዬ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ትሁት ነበር፡፡ ለዓለማዊ ምቾትም ቦታ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ እንደ ባህታዊ ነበር በርግጥ፡፡ ሲበላም እንደ ወፍ ነካ ነካ እንጂ እንደ ከርሶ አደሮች እስኪፈነዳም ሆኖ አያውቅም፤ ለምሳ ተያይዘን እኔ፣ እሱና ፋሲካ ስንሄድ ሆል ፉድ ወደተባለው የጤና ምግብ ቦታ ሊበላ የሚያነሳው ምግብ ልክ ሁሌም ያስደንቀኝ ነበር፡፡ በደምብ ብላ እንጂ ብንለውም አይሰማንም፤ ማታ ደግሞ ሾርባ ወይም ዳቦ ቁራጭ ብቻ እንደሚበላ ስለምናውቅ ሁሌም ያሳስበን ነበር፡፡ በመጠን መብላት ጎጂ ስላልሆነ ከባድ ችግር ያልነው ጉዳይ ግን አልነበረም፡፡ አባዬ ከመጠጡም እምብዛም ነበር፤ ጤናውንም የሚጠብቅ ሰው ስለነበር በደንገት ሲለየን መደንገጣችን አልቀረም፡፡

ጓድ ተገኜ ህይወቱ የሚገለጸው ለኢትዮጵያ በመታገሉ ነው፤ ንዴቱም ደስታውም ከሀገራችን ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነበርም ማለት እችላለሁ፡፡ ግን ትግስተኛ ነበር፡፡ ቢቆጣም ለራሱ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ የጨቋኞች መቀያየርና መተካካት ሁሌም ያናድደው ነበር፡፡ አባዬን እኔው ላስታውሰው የምፈልገው በኢህአፓነቱ ብቻ ሳይሆን በማንነቱና የቀን ተቀን ሰውነቱ ነው፡፡ ተገኜ ባስተማሪነት በልዩ ልዩ ቦታዎች የሰራና የህዝብን ስሜት፤ ፍላጎትና ኑሮንም የሚያውቅ ነበር፡፡ ኤርትራም ኦጋዴንም፤ ምስራቅ፣ ምዕራብም ሰርቷል፤ ኢትዮጵያንም ያውቅ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ለእሱ ዋናው ጭንቀት ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ አንዴ ሲበሳጭ ኢትዮጵያን ከሰህ መጽሃፍ ጻፍባት አለኝ፡፡ እንደ ድመት ልጆችዋን መብላት አበዛች ብሎኝ ስለነበርም “ቅሬታችንን ሁሉ ላውርድባት ወይ?” ስለው “አይ እሱማ ይበዛል በልኩ ውቀሳት” ያለኝ ትዝ የለኛል፡፡ “ተከሳሽ ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ መጻፍ ጀምሬ ወደ 40 ገጽ ደርሺ ልኬየለት ጨርሰው ብሎ ሲገፋኝ ግዜ ቢያልፍም በህይወት እያለ ሳልጨርሰው በመቆየቴ ዛሬ በጣም ቅር ይለኛል፡፡ ተገኜ ብቻውን የሚኖር፤ ቤተሰብ ያልመሰረተ፣ ያልወለደ ነበርና ህይወቱ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ በግራ በቀኝ ኢህአፓ ላይ ዘመቻና ጥቃቱ ሲበዛ መበሳጨቱ አልቀረም፡፡ ለሀገር በታገልን ምን አደረግናቸው ይልም ነበር፡፡ ለሀገር ስለምንታገል ነው የማይወዱን ስለውም የሚያውቀውን ነገር ነበር የምነግረው፡፡ በኢህአፓ የግለሰብ ማንነት ላይ ትኩረት ስላልነበር፣ ዛሬና አሁን ቅር የሚለኝ ነገር አባዬን ስለማንነቱ ብዙም ጠይቄው አለማወቄ ነው፡፡ ጎንድር መወለዱን ባውቅም የት መሆኑን አላውቅም፡፡ ወንድም አለው እህት አላውቅም፡፡ አባቱ በጸረ ሙሶሊኒ ትግል መሳታፋቸውን አንዴ ሲያወራ ብሰማም ዝርዝሩን አላውቅም፡፡ ታላቄ መሆኑን ብረዳም መቼ እንደተወለደ እሱም አልነገረኝ እኔም ጠይቄው አላውቅም፡፡ የኢህአፓዎች ግንኙነት የትግል ነው እንጂ የውልደትና ማንነት አይደለም፤ አልነበረም እንጂ ከትግልና ድርጅት ውጪ አንተዋወቅም ብል ስህተት አይሆንም፡፡ ተገኜ በልዩ ልዩ የድርጅት ስምሪቶች የተሳተፈና በምስጢር ተልዕኮዎች ግዳጁን የፈጸመ ቢሆንም በሁሉም ጥያቄ ሁሌም ተስማምተን ሰራን ማለት አይደለም፡፡ መቶ በመቶ የሃሳብ አንድነት አይጠበቅም ብቻ ሣይሆን አይፈለግምም፡፡ በመሰረቱና በመርሀ ግብሩ፤ በኢትዮጵያ ላይ መስማማታችን ነው ዋናው፤ ተወያይተንም ስለምንወስን ተገኜ ለአመነበት በሚገባ የሚቆምና ህሊናው በፈቀደለትም ድምጹን የሚሰጥ ጓድ ነበር፡፡

እኔ፤ አባዬ፤ ጓድ ፋሲካ

አባዬን በቀልድ- በሃቅ ላይ ተመስርተንም በፈጠራም እኔና ገጣሚው አሉ ሁሴን ስንተርበው ተበሳጭቶ አያውቅም፡፡ የአሊ ለከፋ ሲጠፋበት ራሱ ቆስቋሽ ወሬ አቅርቦለት አሊ አቀናብሮበት ሲመጣ ይደሰትበት ነበር፡፡ ሁሌ የሚጠቀምባትን “አንት መናጢ”ን ከመድገም ሌላ ምንም አይልም ነበር፡፡ አባዬ ሌላ የማልረሳው ልጆችን በጣም ይወድ ነበር፡፡ ከሁሉም ጋር እየተጫወተ የብዙዎቻችን ልጆች አሳድጓል፤ አጎት ሆኖላቸዋል፡፡ ልጆችም ስለሚወዱት ከነሱ ጋር የሚያጠፋውን ጊዜ የደስታ አድርገውለታል፡፡ በፖለቲካ አንዳዶች ራቅ ሲሉ ልጆቻቸውንም ስለሚያስቀሩ በጣም ያዝን ነበር፡፡ በፖለቲካው መስክ አቋም ቢይዝም በአጠቃላይ ግን ከሁሉም መጣላት የሚሆንለት አልነበረም፡፡ ሰብአዊ ግንኝነቶቹንም በተቻለው ሊጠብቅ ይጥራል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ እኔ በግሌ የምወደው፣ መጽሃፍ ማንበብ ለምትወደው አዛውንት እናቴ አለችበት ሄዶ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን የሚነበቡ መጽሃፍት ይልክላት ወይም ይወስድላት ነበር፡፡ ወስዶላት ሲገናኙም የምትደግመውን መዝሙረ ዳዊት መጽሃፍ ተውሶ አንድ ወይም ሁለት ምዕራፍ ሳያነብ አይመለሰም ነበር፡፡ አዎ አባዬ ሀይማኖተኛ ነበርና እስከመጨረሻው፤ ስር በዝቶበት ካልሆነም ቤተ ክርስቲያን እሁድ እሁድ ይገኝ እንደነበር ብዙዎች ያውቃሉ፡፡ ወዳጅ ጠያቂ ስለነበርም ሲታመሙም ሳይቀር አባዬ እነ ኮለኔል አስናቀና ኮለኔል አምሩንና፤ ሌሎችንም አስታሟል፡፡

ዛሬ መሀይሞች ምሁር በሉን ሲሉና ጥራዝ ነጠቆች አዋቂ ነን ብለው በመድረክ ሲወጠሩ አባዬ መታዘቡ አልቀረም፡፡ እውነቱ ይነገር ከተባለ አባዬ ህዝብን የማይንቅ ብቁ ምሁር ነበር፡፡ መጽሃፍት ጓደኞቹ ነበሩና ሁሌም ዕውቀቱን ለማዳበርና ሁሌም ለመማር ማንበብ ብቻ ሳይሆን እኔ ራሴ አሜሪካ ስሄድ ብዙ መጽሃፍትን አውሶ ያስነበበኝ ነበር፡፡ ተገኜ የሚያነበው የአማርኛም የእንግሊዝኛም መጽሃፍ በዋናነት የታሪክ መጽሃፍትን ሲሆን፤ የጦርነቶች፤ የስለላ ታሪኮች፤ የታዋቂ ሰዎች የህይወት ታሪኮችም ማንበብ ይወድ ነበር፡፡ በቋንቋ ደረጃ እንግሊዝኛ፣ አማርኛና ትግርኛ ይናገር ነበርና የንባብ ዓለሙ ጠባብ አልነበረም፡፡ ተገኜ ለፍኖተ ዴሞክራሲ ሀታታዎችና ትዝብቶችን በሰፊው ሲጽፍ የቆየ ሲሆን እንደ ሌሎቹ ሁሉ ጽሁፎች በጓዶች ሲታረሙ ደስተኛ እንጂ ማን ነክቶብኝ ባይ አልነበረም፡፡ በመጨረሻም ዘረኞቹ ለስልጣን ሲበቁና በውጭ ነዋሪው ጭፍን ድጋፍ ሲሰጣቸው ሲያይ በጥልቅ ማዘኑን ማየት ችያለሁና ስሜቱን ከጎዱት አንዱ አቢይ ክስተትም ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አለኝ፡፡ ከአባዬ ጋር ብዙ የማልረሳቸው አስቂኝ ገጠመኞችን አሳልፈናል፡፡ አብረ በቅርብ በዋሺንግተን ቆይታዬ የሰራነውና አብረንም ምሳ ስንበላ የተጫወትናቸው ሁሉ የምረሳቸው አይደሉም፡፡ ከእሱም ውጪ ማንም “አንት መናጢ” ብሎኝ አያውቅም፡፡ በድንገት ጥሎን ስለሄደና ስለጎዳንም እኔም ለመጨረሻ ጊዜ “አንት መናጢ፣ አፈሩ ይቅለልህ” ብዬ እሰናበተዋለሁ፡፡