የአድዋ ድል የቀለም ትርጓሜ እና በአምስቱ ዓመት ጦርነት . . . ለኢትዮጵያ እነማን ምን ዋሉባት ወይም ዋሉላት?

ከዓለሙ ተበጀ –

ከ1928 እስከ 1933 ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ወረራ ጋይል ጋር ያካሄደችው ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የቀለም ፍትጊያ በግልጽ አፍጥጦ እንዲያይ አድርጓል። ቀድሞውኑም አድዋን ትከትሎ ዋናዎቹ የአውሮፓ መንግስታት የነጭ ሃይል በጥቁር ሕዝብ የደረሰበት ሽንፈት አስቆጭቷቸውና በነሱም ቅኝ ተገዥዎች ላይ የሚያስከትለው መነሳሳት አስግቷቸው ከተሸናፊዋ ጣልያን ጎን ቆመዋል።

ዶ/ር ሹመት ሲሻኝ እንደገለጹት፣ ጣሊያን የጦር ኋይሏንና መሳሪያዎቿን ታግዝባቸው ዘንድ በእንፋሎት የሚሰሩ መርከቦች ብሪታንያ እረድታለች። ከሰላ ላይ በመሃዲሲቶች ተከቦ የነበረውን 2 ሺህ ገደማ የጣሊያን ሃይል ነጻ ለማድረግም ወታደር ልካለች። የዚህም ዓላማ የመሃዲስቶቹን ሃይል ከጣሊያን ግለል በማድረግ ኢትዮጵያን ዳግመኛ የምትወጋበት ፋታ እንድታገኝ ለማድረግ ነበር። የጀርመን ንጉስም በሃገሩ ወደነበረው የጣሊያን ኢምባሲ በመሄድ በአድዋው ሽንፈት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል። አንድ የጀርመንን የውጭ ጉዳይ ቢሮ አመለካከት የሚያንፀባርቅ ጋዜጣ  “የአውሮፓ ክብር አፍሪካ ውስጥ ውርደት ደርሶበታል። ይህን ክብር ከመንበሩ ለመመለስም ሌላ ዘመቻ መካሄድ አለበት” በማለት ጽፏል። የወቅቱ የአስትሮ . ህንጋሪያ አጼ ግዛት መንግስትም በደረሰው ሽንፈት መጸጸቱን ጠቅሶ የጣሊያን መንግስት ለ “እናት ሀገር ደህንነት ምንም ስጋት ሳይገባት” የሚያሻውን ያህል ጦር በኢትዮጵያ ላይ ማዝመት እንደምትችል አሳውቋል።

የባቲካኑ “ቅዱሱ” ካቶሊካዊ አባት ሳይቀሩ በጣሊያን ላይ በደረሰው ሽንፈት እጅግ አዝነዋል። በዚህ የተነሳም ለምሳሌ እ. ኤ. አ በመጋቢት 4/ 1996 እለት ሊካሄዱ ይገባቸው የነበሩ ቤተክርስቲያናዊ ስርዓተ ሁነቶች እንዲስተጓጎሉ አዘዋል። ከአጼ ምኒልክ ጋ የተሻለ ወዳጅነት የነበራት ፈረንሳይም ብትሆን የኢትዮጵያ ድል አስደንግጧታል። አንድ የሃገሪቱ ጋዜጣ “ከአረመኔው ዓለም የውጣ ሃይል ባንድ የስለጠነ ሀገር ላይ ባደረሰው ሽንፈት ፈረንሳይ ተጸጽታለች” ብሏል። አጼ ምኒልክ ለፈረንሳዊው የጅቡቲ ገዥ በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንደጠቀሱት ከአድዋው ጦርነት በኋላ የአውሮፓ መንግስታት በጣሉት ማእቀብ ፈረንሳይም ተባብራለች። በአጠቃላይ በወቅቱ ካውሮፓዊያኑ መንግስታት ኦርቶዶክሳዊቷ ሩሲያ ብቻ ለኢትዮጵያ ወገናዊነትን አሳይታለች። በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ርቀት የዚህን ወገናዊነት ተግባራዊ ጠቀሜታ አሳጣው እንጂ።

ከ40 ዓመት በኋላም ጣሊያን የወታደራዊ ድል ገድል የለሽ ያደረጋትን የአድዋን ቂሙዋን ልትወጣ ፈለገች። ብዙም አልተሳካላት እንጂ ወታደራዊ ዝናዋን ለማድመቅ ተስፋ አድርጋ በአንደኛው የአለም ጦርነት ገብታ ነበር። እ. ኤ. አ በ1922 ሞሶሎኒና የፋሽስት ፓርቲው ስልጣን ላይ ሲወጡ ደግሞ የመስፋፋት በተለይም ኢትዮጵያን ወሮ ለመያዝ ፍላጎቷ ዳግም አገረሸባት እና በ1928 ወረራ አካሄደች።

ከአንደኛው የዓለም ጦርንት በሁዋላ የመንግስታትን ትብብር ለማጠናከርና ሌላ መስል ጦርነትን ለማስቀረት እንዲረዳ ታስቦ የተቋቋመውው የመንግስታቱ ማህበር ልባዊ ሙከራ አድርቶ ቢሆን ኖሮ ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ከመውረር ድርጊቱ ይታቀብ ነበር የሚሉ አንዳንድ ትንታኞች አሉ። በወቅቱ አሜሪካን የማህበሩ አባል አልነበረችም። በናዚ ሂትለር የምትመራው ጀርመንም አባልነቱዋን ሰርዛ ነበር። ከማሃበሩ አባል መንግስታት ፈርጠም ያለ ጡንቻ የነበራቸው ብሪታ ንያና ፈረንሳይ ደግሞ ሞሶሎኒ ከሂትለር ጋር እንዳያብር የነበራቸው ፍርሃት ኢትየጵያን በተመለከተ በሚቀይሱት ፖሊሲ ላይ ተጸኖ አሳድሯል። ስለዚህም ሁለቱ ዋነኛ የምእራብ አውሮፓ “ዴሞክራሲያዊ” መንግስታት ጣሊያንን ላለማስቀየም ወሰኑ። ቅድሚያ የሰጡትም ከኢትዮጵያ ይልቅ አውሮፓ ነክ ለሆነው የራሳቸው ደህንነት ነው።

ፈረንሳይ እና ብርታንያ ጣልያንን ላለማስቀየም ከወሰዱዋቸው እርምዳዎች አንደኛው ኢትዮጵያ እራሱዋን ለመከላከል የሚያስችል መሳሪያ የመግዛት ጥያቄ ስታቀርብ እምቢ ማለት ነበር። እ.ኤ.አ በ1934 እና 1935 መጀመሪያ ላይ ጣሊያን ኤርትራና ሱማሌ ውስጥ የጦር ሃይልና መሳሪያ ስታክማች፣ አጼ ሃይለሥላሴ በብኩላቸው የጦር መሳሪያ ከአውሮፓ ለመግዛት ሞከሩ። በወቅቱም ቀደም ሲል የተጠቀሱት መንግስታት በሁለቱም ጠብኞች ላይ መሳሪያ ማእቀብ አድርገናል አሉ። በጊዜው ጣሊያን እራሱዋን የማስታጠቅ አቅሙ ያላት በቂ ዝግጅትም ያደረገች መሆኑ በግልጽ እንደመታወቁ ማእቀቡ ያነጻጸረው በኢትዮጵያ ላይ ነው ማለት ይቻላል።

ሁለተኛውን የግማሽ ልብ እርምጃቸውን የውሰዱት ደግሞ ወረራው የተጀመረ ሰሞን ነበር። ይህም የመንግስታቱ ማህበር አባላቱ ከጣሊያን ጋር እንዳይገበያዩ ብዛት ባላቸው ሸቀጣሸቀጦች ላይ የጣለው የንግድ ማእቀብ ነው። 51 መንግስታት ደግፈውት በተላለፈው በዚህ ማእቀብ ዝርዝር ውስጥ ለዘመናዊ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችና ለጣሊያን ወረራ መሳካት የግድ አስፈላጊ የነበሩት የነዳጅ እና የከስል ምርቶች እንዳይካተቱ መደረጉም እርምጃው ከሙሉ ልብ እንዳልነበር ይጠቁማል።

ጣልያንን ለማስደሰት ታስቦ ሶስተኛው እርምጃቸው የተውሰደው ደግሞ በህዳር ወር 1928 ላይ ነው። የብሪታንያው የውጭ ጉዳይ ሴክሬተሪ ሆሪ ፓሪስ ላይ ከፈረንሳዩ አቻቸው ከላቫል ጋር ተነጋግረው በደረሱበት ስምምነት መሰረት በታሪክ “የሆሪ..ላቫል እቅድ” ተብሎ የሚጠቀሰው የማስታረቂያ ሰነድ ተዘጋጀ። እቅዱ ሁለት መሰረታዊ ይዞታዋች ነበሩት። አንደኛው የቦታ ልውውጥ አደላደላቸው ነው። በዚህም መሰረት ከስሜን ምስራቅ የሚበዛው ትግራይን፣ በደቡብ ምስራቅ የኦጋደንና የድንከል በርሃን ጨምሮ 60.000 ስኮዬር ማይልስ ጣልያን ከኢትዮጵያ ስትቀበል በልዋጩ ደግሞ ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህርና አሰብ የመተላለፊያ መስመር አክሎ በወራሪዋ ከተያዘባት ኤርትራ 3.000 ስኮየር
1234ማይልስ እንዲሰጣት ነበር የታሰበው። ሁለተኛ ደግሞ የመንግስታቱ ሊግ በሚነድፈው እቅድ መሰረት በጣሊያን ሹማምንት የሚተዳደር አንድ ሰፊ “የኢኮኖሚ ማስፋፊያና የሰፈራ እቅድ ማካሄጃ” ቀጠና ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ ለጣሊያን እንደሚሰጣት መተማመኛ የምታገኝበት ሁነታ እንዲፈጠር ጥሪ ያቀርባል ስነዱ።

በዕቅዱ ላይ ከተመለከተው ትንሹ ክልል /ኤርትራ/ ብቻ በጣሊያን እጅ እንደመሆኑ፣ እና ግማሽ ያህሉ የሃገሪቱ አካል ያለምንም ውጊያ ለእሱዋ እንዲሰጣት እንደማሰባቸው ሆሪና ላቫል ለጣሊያን በጣም ቸር ነው የሆኑት። ሌላው የሚያስገርመው ነገር ደግሞ አካሉዋ ተቆርሶ ሊሰጠው የታሰበችው የኢትዮጵ እሺ ማለት እና የመንግስታቱ ማህበር የመስማማት ጥያቄ ገና ከወዲሁ ያለቅለት ሆኖ መወሰዱ ነበር። አጼ ሃይለስላሴ የሀገራቸውን መክፋፈል በደመነፍስ ይቀበላሉ፣ መኳንንቱን እና የጦር አበጋዞቻቸውንም ሃሳቡን እንዲቀበሉ ያግባባሉ ተብሎ መታሰቡ ደግሞ ይበልጥ የሚገርም ነው። ከተቃወሙም ከዚያ በሁዋላ ከመንግስታቱ ማህበር እርዳታ አገኛለሁ ብለው እንዳያስቡም እንደ ማስጠንቀቂያ ጭምር ነበር እቅዱ። ሃሳቡን ቢቀበሉ ኖሮ ግን ኢትዮጵያ ለበለጠ ጥቃትና ለሰፋ ወረራ መዳረኋን በማጉላት የመንግስታቱ ማህበር የጣሊያንን ሞግዚትነት እንዲቀበለው ነበር የታለመው።

የብሪታንያ ካቢኔ ጊዜ ሰጥቶት እንስከሚነጋገርበት ድረስ እቅዱ በጥብቅ ምስጢራዊ ሆኖ እንዲቆይ ነበር የታሰበው። ሁለቱ ባለስልጣናት ቅዳሜ፣ ህዳር 27/1928 እለት ከስምምነት በደረሱ ማግስት ግን የኢትዮጵያንና የጣሊያንን ውርክብ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት አንድ እርምጃ ስለመወሰዱ የሚያስገነዝብ አጭርና እጅግ ሚስጢራዊ የአንግሎ.-ፈረንሳይ የጋራ መግለጣ ከጋዜጠኞች እጅ ገባ። በቀጣዩ ቀን ጠዋት ላይ ሁለት የፈረንሳይ ጋዜጦች እቅዱን በሚገባ የሚተነትን ጽሁፍ ይዘው ወጡ። ዜናው እንደምን አፈትልኮ ከጋዜጦች እጅ እንደገባ እስካሁንም በደንብ አይታወቅም። ከሰዓት በሁዋላ ደግሞ ዜናው ለለንደን የዜና ምንጮች ደርሰ። የብሪታንያ መንግስትም የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ ሊያልፈው ያልቻለ የህዝብ ተቃውሞ ተፈጠረበት።

በዚህም የተነሳ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ባልድዊን ፕርግራም የያዙበትን በለንደኑ የባህር ሃይል ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ ስርዓት ላይ የመገኘት ሃሳባቸውን ሰርዘው ህዳር 29 ቀን 1928 እለት የካቢኔ አባላታቸውን ለስብሰባ ጠሩ። አነጋጋሪ የሆነ የገነፈለ የህዝብ አስተያየት እስካለ ድረስ ለጉዳዩ አንድ እልባት መስጠት የግድ ሆነ። ነገሩን ሁሉ የሩጫ ነበር። ሌላው ቀርቶ የካቢኔ አባላቱ በተሰበሰቡበት ክፍል ውስጥ የኢትዮጵያ ካርታ አልነበረም ይባላል። ይህም እውነት ከሆነ ደግሞ ምን ያህሉ የሀገሪቱ አካል ለጣልያን እንዲተላለፍ እንደታቀደ እንኳን ተጨባጭ ግንዛቤ ሳይኖራቸው ነበር ማለት ነው የካቢኔ አባላቱ በኢትዮጵያ መጭ እድል ላይ የሚነጋገሩት።

የኢትዮጵያ መሪ አጼ ሃይለስላሴም እቅዱን በጥብቅ የተቃውሙት በኦፊሴል  እንዲያውቁት ከመደረጉ በፊት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ባልድዊን ካቢኔያቸውን በሰበሰቡበት እለት፣ ይህን ጠብ አጫሪ የሚሸልም እቅድ እንደማይቀበሉት እና ብሪታንያም በወሰደችው አቁዋም እንዳዘኑ በመግለጽ ንጉሱ የላኩት መልእክት ለብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ደረሰው። በታህሳስ 1/1928 እለትም ኢትዮጵያዊው ዲፕሎማት ክቡር አክሊሉ ሃብተወልድ የፈረንሳይን የውጭ ጉዳይ ቢሮ በመጎብኘት ስለ እቅዱ ዝርዝር ማብራሪያ ጠየቁ። ለዜና ዘጋቢዎችም “በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለጣሊያን ጠብ አጫሪነት ሽልማት የሚሰጥ ወይም የመንግስታቱ ማህበር ቀደም ሲል ከስምምነት የደረሰባቸውን መሰረታዊ መርሆዎች በተለይም የኢትዮጵያን ፓለቲካዊና የግዛት አንድነት የሚጻረር..” ምንኛውንም እቅድ በመቃወም አቋሙ የኢትዮጵያ መንግስት የጸና መሆኑን ገለጹ። ከሳምንት በኋላም ማለትም ታህሳስ 8/1928 እለት ንጉሰ ነገስቱ ደሴ ላይ ካቋቋሙት ቤተመንግስታቸው ሆነው ቀደም ሲል የተገለፀውን እቅድ እንደማይቀበሉት ለዘጋቢዎች የመግለፃቸው ዜና የመንግስታቱ ማህበር ከነበረበት ጄኔቭ ከተማ ደረሰ።

በአጠቃላይ የብሪታንያ መንግስት ከፈረንሳይ ጋር በማበር ይህንን መሰል ጣሊያንን አባባይ ፖሊሲ ቢያራምድም የህዝቡ አቋም ባመዛኙ አፍቃሪ..ኢትዮጵያ ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ግን መንግስታዊ ያልሆኑ አንዳንድ አካላት ወይም ግለሰቦች የጣሲያንን ወረረራ የሚደግፍ እንቅስቃሴ አላደረጉም ማለት እንዳልሆነ ሊታወስ ይገባል። ለምሳሌ በውቅቱ የኦቨዘርበር እትም አዘጋጅ ጀ.ኤል ጋርቪን “አብስኒያዊያን በነጭ ዘር ላይ ድልን ተቀዳጅተው ቢሆን ኖሮ በጨለማው አህጉርና በሌሎችም አህጉራት መፍትሄ የማይገኝለት ችግር” ይፈጠራል ባይ ነበሩ። የዚሁ አመለካከት ዋና አቀንቃኝ ዘ አርል ኦፍ ማንሰፊልድ “ጣልያን ብትሸነፍ በቀለም ህዝቦች መሃል ረብሻና አመጽን ለማነሳሳት ለሚጥሩት ታላቅ ማበረታቻ ይሆናል፣ በምስራቅ አፍሪካ ይዞታችንም ላይ ከፍተኛ ጥፋት ያስከትላል” በማለት አስጠንቅቀዋል። ለብሪታንያ ክስረትን እንደሚያስከትል የሚያስገነዝብ ንግግር በማድረግም ይከሰሳሉ። በጣሊያን ላይ የኢኮኖሚ ማእቀብ መጣሉም በብሪታንያ ምጣኔ ሃብት /ኢኮኖሚ/ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ውጤትም በወቅቱ የመነጋገሪያ ርእስ ኖኖ ነበር። ለዚህም ትኩረት ለመሳብና ማእቀቡን ከጣሊያን ላይ ለማስነሳት የሚጥር አንድ “በብሪታንያ ከጣሊያን አቃ አስመጭዎች ማህበር” የሚባል አካል ተቋቁሟል።

የቫቲካኑ ጳጳስ የነበሩት ፒዮስ 11ኛም ያሳሰባቸው የነበረው የኢትዮጵያ መወረር ሳይሆን ወረራው ባይሳካ የሚያስከትለው ውጤት ነበር። በወቅቱም የፈረንሳዩን አምባሳደር ተቀብለው ሲያነጋግሩ እንዲህ ነበር ያሉት፣

“ይህ ጠብ እጅግ እረፍት ነስቶኛል። ኢትዮጵያ እንዲያውም በጠቅላላው ጥቁር አፍሪካ ውስጥ ባሉን ካቶሊካዊ ፍላጎቶቻችን ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ካሁኑ ታውቆኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካቶሊክ ሚሲዮናዊያን ሰላይ ተብለው እየተወነጀሉ ነው። ሁኔታው ኔግሮዎችን በነጮች ላይ ለማነሳሳት ጥቁሮች እየተጠቀሙበት ነው። የጣሊያን መሸነፍ በአፍሪካ የአውሮፓ ቅኝ ግዛቶቻችንን እጣ ፈንታ የሚወስን ይሆናል።”
ወረራው ከመጀመሩ በፊት ነሀሴ፣ 21 ቀን 1927 በአለም አቀፍ የካቶሊካዊያን ነርሶች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ደግሞ፣

“…በፍርደ ገምድል ጦርነት ልናምን አንሻም። በሌላ በኩል ጣሊያን እያሰበችው ያለው ጦርነት ያለማቋረጥ በተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉ የግንባር ክልሎችን ደህንነት በማስከበር እራስን ለመከላከል የታለመ፣ በየቀኑ እየጨመረ በመጣው የህዝብ ብዛት የተነሳ አስፈላጊ እየሆነ የመጣ እና ስለዚህም የሀገሪቱን /የጣሊያንን/ ቁሳቂ ደህንነት ለማስጠበቅ ወይም ለመከላከል የሚካሄድ ጣርነት ስለሆነ ፍትሃዊ ነው። በመሆኑም የዚህ አይነቱ ጦርነት እራሱን በራሱ ስለፍትሃዊነቱ ያረጋግጣል ይባላል። በሌላ በኩል ግን አንድ ሃቅ አለ። በዚሁ ልንሸሸው በማንችለው እውነት ላይ ተመርኩዘን ይህ መስፋፋት አስፈላጊ ከሆነ ግንባር ክልሎችን መከላከልና ደህንነታቸውን ማስከበር አስፈላጊ ከሆነ እነኝህ ችግሮች ከጦርነት ይልቅ በሌላ መንገዶች እንዲፈቱ ብቻ ነው የምንሻው።”

ብለዋል። ከሶስት ቀን በሁላ ደግሞ ኦብስርቫቶሬ ሮማኖ ጋዜጣ ላይ “የጳጳሱ አመለካከት ግልጽ ነው። የመስፋፋት አስፈላጊነት ክግምት ውስጥ መግባት ያለበት እንጅ በራሱ መብት አይደለም። በሌላ በኩል ግን ይህ መብት ተግባራዊ ሲሆን የተወሰኑ ገደቦችን ከላበጀና የተወሰነ ዘመናዊነትን ካልተላበሰ ጎጅ ሊሆን ይችላል” የሚለው ጽሁፋቸው ተነቧል። ለካቶሊካዊያን ቀደምት የጦር ወታደሮች ስብስብ ደግሞ ጳጉሜን 2/1927 እለት ባደረጉት ንግግር ለሰላም መስፈን እየጸለዩ አብረውም “የታላቁና የጥሩ ህዝባቸው ተስፋዎች ፍላጎቶችና አስፈላጊ ነገሮች በሌላ ሳይሆን ፍትሃዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቀባይነት እንደሚያገኙና እንደሚሳኩ” የአላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የጳጳሱ አቋም በአጽንዖት ሲታይ ውርክቡ ከጦርነት ይልቅ በድርድር አብሮም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረራ ይዛ ለማግኘት ያለመቻቸውን ጥቅሞች በሚሳኩበት ሁኔታ እንዲፈታ መሆኑ ግልጽ ነው። ዞሮ ዞሮ ግን “ቅዱሱ አባት” ወራሪውን ሃይል አላወገዙም። ወይንም ነህሴ 30 ቀን 1927 ሰላም እንዲወርድ ሰለሚያደርጉት ጸሎት በማመስገን መልእክቱዋን ላስተላለፍችላቸውና በግፍ ለተወረረችው ኢትዮጵያ አላገዙም። አለዚያም በወቅቱ በሚበዛው የአለም ክፍል ተቀባይነት የነበራቸውን የአለማቀፍ ህግ መርሆዎች ተግባራዊነት ለማስከበር ወይንም ለማስታረቅ የተደረገውን የሽምግልና ጥረት ለማገዝ አልሞከሩም።  የስነምግባርና የዳኝነት መሰረቶቹ ከክርስትና መርሆዎች ጋር ይዛመዱ ለነበሩት የመንግስታቱ ማህበርም ማበረታቻ አልሰጡም።  ሌላው ቀርቶ በዓለም የተከለከለ መርዝ እስከመጠቀም በደረሰ ጭካኔ እርምጃ ኢትዮጵያዊያንን  በፍግ የጨፈጨፈውን ወራሪ ሃይል ባለማውገዟ ተጸጽታ ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ እንኩዋ ቫቲካን እግዚአብሄርን ምህረት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ስለመጠየቁዋ የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ዋቤ አላገኘም። በአጠቃላይ የደርሃም ጳጳስ የነበሩት እና በጽናት ለኢትዮጵያ የተከራከሩት ኽርበርት ሄንስሌይ ጄንሰን በወቅቱ.
“…አሁን ያሉት ጳጳስ ለአለም አቀፍ ህግ፣ ለፍትህ፣ ለሰብዓዊነት መከበረ ምን አስተዋጽኦ አድርገዋል? ጳጳሱ ጣሊያናዊ እንደመሆናቸው እንደማንም የህገራቸው ሰው ሁሉ የአርበኝነት ስሜት ያድርባቸዋል ብለን እናስብ ይሆናል። እዚህ ላይ ግን ልዩነት አለ። እሳቸው እንደሌላው ሰው አይተው እንዳላዩ ሊሆኑ አይገባቸውም። ድርጊታቸው ሁሉ በእውነት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል። ቫቲካን በየቦታው ወኪሎች ያሉት፣ መረጃ በሚገባ የሚያገኝና ሙሉ ነጻነት ያለው የዲፖሎማሲ አገልግሎት አላት። ሞሎሎኒ ከጳጳሱ በስተቀር ሁሉንም ጣሊያናዊያን ሊያታልል  ይችል ሆናል። በዚህ  አሳዛኝ የአብስንያ ጦርነት ከሃምሳ በላይ ሀገሮች ጣሊያንን በጠብ አጫሪነት ፈርጀው ሲቃወሙዋት፣ ጳጳሱ ምን አሉ? በሚያሳፍር ሁኔታ ውሎች ሲፈርሱ፣ ተቀባይነት የነበራቸው የጦርነት ህግጋት ሲጣሱ ከጳጳሱ አንደበት ምን ተቃውሞ ተደመጠ? የሀገራቸውን ሰዎች ዓይን ለመግለጥ፣ ህሊናቸውን ለመቀስቀስ፣ ስሜታዊነታቸውን ለመግታት በጳጳሱ ምን ጥረት ተደረገ? አዎ! በየጊዜው ጳጳሱ በተናገሩ ቁጥር ግልጽ ያልሆነ (አሻሚ) እና በዚህም የተነሳ ንግግሮቻቸው ከተግሳጽ ይልቅ ይሁንታን የሚያስመላክቱ ነበሩ። ሁልጊዜ የሚናገሩትም ስለሰላም ነበር። ሰላምን ተቀባይነት ያለው እና አስተማማኝ ስለሚያደርገው ብቸኛ መንገድ ስለ እውነት ድርጊት ግን ትንፍሽ አላሉም። ከእውነተኛ ድርጊት የተፋታ ሰላም የክርስቲያንን ከናፍርት ሊመርዝ ይችላልን? … ግን አንድ ያልታጠቁና እድሜያቸው የገፋ አዛውንት የጣሊያንን አምባገነን እንደምን ከድረጊቱ እንዲቆጠብ አደርገዋለሁ ብለው ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ? ጳጳስ የኢየሱስ ገበዝ ናቸው፡ የኢየሱስ ሃይል ደግሞ በደካማነት ውስጥ ተገልጦ ጽናቱን ይገልጣል። መንፈሳዊ ስልጣኑም አለማዊ ሃይል በሌለበት ሁኔታ በሚገለጥበት ወቅት የበለጠ ደምቆ ይታያል። ምንም እንኩዋን ረዳት የለሽ ምርኮኛ ሆነው ሞሶሎኒ ፊት ለፊት ይህን ያህል አላደረጉም ይሆናል? ቅዱስ አባት ከሃላፊነታቸው ጋር የሚያያዝ ሲሆን ሃይለኛና ፈጣን ናቸው። አንድ የፈረንሳይ ሊቀ ጳጳስ አንድ የቤተክርሲያን ህግ ቢተላለፉ፣ እንደሚወገዙ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። የጣሊያኑ አምባገነን ግን አለምን በአመጽ እና በሽፍጥ ሲያናውጥ ገና አልተነቀፈም። አልተገሰጸም። ልክ እየሱስ እንዳወገዛቸው ፈሪሳዊያን፣ ጳጳሱም “ትንኙን አጣርተው ሲያወጡ፣ ግመሉን ይውጣሉ” በማለት የጻፉት አባባል የጳጳሱን አቁዋም አጠቃሎ ሳይገልጸው አይቀርም።

አሜሪካ ያራመደችው ፖሊሲም ቢሆን ጣሊያንን የሚጠቅም ቢያንስ የማይጎዱ እርምጃዎችን ያካተተ ነው። ሃምሌ ነሃሴ 1927 ላይ ብቻ ውርክቡን በተመለከተ የአሜሪካ መንግስት ሶስት እርምጃዎችን ወስዱዋል። አንደኛው የሃገሪቱ  ፕሬዚዴንት ሮዝቤልት  ለሞሶሎኒ የላኩት መልእክት ሲሆን፣ ሁለተኛው ነሃሴ መጀመሪያ ላይ ህግ ሆኖ የተደነገገው የመጀመሪያው የገለልተኛነት አቋም ነው። ሶስተኛው ደግሞ የአሚሪካ መንግስት “የሪኬት ውል” (ሪኬት ኮንሰሽን) የተባለው እቅድ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እንዳይሆን ያደረገው ግፊት/ጫና  ነበር።
ብርታኒያ እና ፈረንሳይ ለሆራላሻል እቅድ መሳካት አሜሪካ ግፊት እንዲታደርግ ባደረጉት ዲፕሎማሲያዎ ጥረትም ጭምር ነበር ሮዝቤልት ለሞሶሊነ መልእክት የላኩት። ሮም ውስጥ የነበረው ጉዳይ አስፈጽሚያቸው አሌክሳንደር ኪርክ ባቀረበው ሃሳብ መሰረት መልእክቱ ለህዝብ ይፋ አልተደረገም። በውስጡ ግን ፕሬዘዴንቱ የኢትዮጵያንና የጣሊያን ውርክብ በሰላም እልባት እንደሚያገኝ ያላቸውን ቅን ምኞት ግልጸው ጦርነት በሁሉም ሀገሮች ፍላጎት ላይ ጉዳት የሚያስከትል የዓለም አደጋ ይሆናል ብለዋል። ነሃሴ 13 1927 ከሰዓት በሁዋላ ሞሶሎኒ ኪርክርን አነጋግሮ መልእክት ሲቀበለው ግን የሆራላቫል እቅድ ውድቅ ከሆነ የአንድ ቀን ተኩል እድሜ አስቆጥሮ ነበር።

ነሃሴ 24 1927 ደግሞ ሮዝቤልት የመጀመሪያውን የገልልትኛነት አቋም በፊርማቸው ደንግገው አውጡ። ይህንንም ያደርጉት አሜሪካ ከኢትዮጵያና ከጣሊያን ጦርነት፣ ባጠቃላይ ደግሞ የመንግስታቱ ማህበር በጣሊያን ላይ ማእቀብ ቢጥል አውሮፓ ውስጥ ሊከተል ይችላል ተብሎ ከተገመተው ጦርነት እንዳትነካካ ይርዳል በሚል ተስፋ ነው። ድንጋጌው በእንደዚህ አይነት ጦርነት ወቅት ለማንኛውም ተፋላሚ ወገን የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ እንዳይደረግ የሚከለከል ህግ የማውጣት ስልጣንን ለፕሬዚዴንቱ ይሰጣል። በዚህም ፕሬዚዳንታዊ ስልጣን መሰረትም መስከረም 15፣ 1928 ላይ ሮዝቤልት ታንክ አውሮፕላንና የጦር መርከቦችን ጨምሮ ማንኛቸውን መሳሪያ ለተወራሪዋ ኢትዮጵያም ሆነ ለወራሪዋ ጣሊያን እንዳይሸጥ የሚያቅብ ድንጋጌ አወጁ። ማዕቀቡ የተጣለባቸው እቃውች ዝርዝር ሲታይ ጠባብና የጦር ማሳሪያዎችን ያካተተ ነበር።

እርግጥ ነው ፕሬዚዴንቱ የጣሊያን ሸቀጦች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የማድረግ ስልጣን አልተሰጣቸውም፣ አለዚያም ዲፕሎማሲያዊ ወኪሎች ከጣሊያን እንዲወጡ በማድረግ፣ የጣሊያንን ወረራ እውቀና ባለመስጠት፣ የጣሊያንን የባህር ሃይል ለማገድና ሱዊዝ ካናልን ለመዝጋት በመስማማት፣ እንዲሁም ተመሳሳይ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ማእቀቦችን በመጣል የመንግስታቱ ማህበር በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 16 መሰረት ሊወስዳቸው ይችላቸው በነበሩ እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ የመተባበር ስልጣን ፕሬዚዴንቱ አልነበራቸውም። በሌላ በኩል ግን ቀደም ሲል ያነሳነው የነሀሴ 24/1927ቱ የገለልተኛነት አቋም ድንጋጌ የመንግስታቱ ማህበር ጦርነትን አስመልክቶ ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ጋር በተያያዘ የአሜሪካን አቋም ምን እንደሚሆን ምንም የሚለው ነገር የለም። በጣሊያያን ላይ የሚጣሉ ማእቀቦችን በተመለከተ አሜሪካ የምትወስደውን አቋም የመወሰኑ ሃላፊነት ባብዛኛው የተተወዉ ለፕሬዚዴንቱ ነበር። ስለዚህም የዚህ ድንጋጌ አተረጓጎም ልቅ የመሆኑን እድል በመጠቀም ወይንም በማእቀቡ ውስጥ በነበረውና “የጦርነት ማካሄጃ ቁሳቁሶች” በሚለው አባብል ላይ በመመርኮዝ ጠብ አጫሪዋ ጣሊይንን በሚጎዳ መልኩ የእቃዎቹ ዝርዝር ሊያሰፉት ይችሉ ነበር።

አዎ አንዳንድ ሰዎች የገለልተኛነቱ ውሳኔ ሲደነገግና ማእቀቡም ሲጣል ጣሊያን ከአሜርካ የጦር መሳሪያዎችን ለማስገባት ገንዘቡም ሆነ በመርከብ የማጓጓዝ አቅሙ ሲኖራት፣ ኢትዮጵያ ግን ስላልነበራት የምትጎዳው ወራሪዋ ነች ብለው ያሰቡ ነበር። ጉዳዩን በአጽንኦት ላስተዋለው ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው። በነሃሴ 1927 መጨረሻ ላይ የነበረውን የሁለቱን ሀገሮች የጦር ሃይል አቅም ላነጻጸረ የወራሪዋ የጣሊያን ሃይል የበለጠ የታጠቀ ነበር። እንደ ነዳጅ ዘይት ብረት የምግብ ሸቀጦች ቃጫና ሎሎችም ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ቁሳቁሶችን ያለችግር ከውጭ ማስገብት እስከቻለች ድረስ ጣሊያን የራስዋ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎች ነበሩዋት። እናም ማእቀቡ ጣሊያንን ከማበሳጨት ባለፍ የሚያስከትልባት ጉዳት ኢምንት ሲሆን ለኢትዮጵያ ግን ከፍተኛ መርዶ ነው። የማምረት አቅሙ ላልነበራት ለኢትዮጵያ ከሁሉም በላይ የሚያስፈልጋት ማእቀቡ የተጣለበት የጦር መሳሪያ ነበርና። ፈርንሳይ፣ ብሪታንያ፣ የተቀረውም አብዛኛው አውሮፓ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማእቀብ እንደመጣላቸው የገልልተኛነት ድንጋጌው እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ለኢትዮጵያ ከቀሩዋት አማራጭ የግዢ ቦታዎች አንዷ አሜሪካ ነበረች።

አውሮፓ ውስጥም አሜሪካ የወሰድችው የገለልተኛነት አቋም ጣሊያን ላይ በሚጣል ማእቀብ ለመተባበር ፈቃደኛነቱ እንደለሌላት አመላካች ተደርጎ ተወሰደ። በሌላ በኩል ግን የመንግስታቱ ማህበር አባል የሆኑት የአውሮፓ መንግስታት በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረውን የጠብ አጫሪነት እርምጃ ለመቋቋም፣ ለመቅጣትና ለመከላከል አቅሙ ነበራቸው። ለውጤቱ መሳካት ፍቃደኛነቱ ቢኖር ኖሮ ፈረንሳይና ብሪታንያ በዲፕሎማሲያዊ ጫና ሞሶሎኒን ከእርምጃው ሊገታው፣ የኢትዮጵያን የመከላከል አቅም ሊያጎለብትና የመንግስታቱን ማህበር ከመፈራረስ ለማዳን በቂ ነበሩ የሚሉ ጽሀፍት አሉ።

የመንግስታቱ ማህበር በምክር ቤት ከመሰብሰቡ ከጥቂት ቀናት በፊት ማለትም ነሀሴ 25/1927 እለት አንድ የአሜሪካ ኩባንያ በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ለ75 ዓመት ያህል የነዳጅ ዘይት ፍለጋና ልማት ስራ እንዲያካሂድ የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነት የመፈራረም ዜና ሲሰማ የመላው ዓለም ልብ ራደ። የዚያ ጭራሹን ያልተጠበቀ ሁነት ተዋናይ የብሪታንያዊው የንግድ ሥራ ደላላ የሪኬት ውል ሥራ ላይ ሊውል ሳይታሰብ አልቀረም የሚል ግምት በሰፊው ተናፈሰ። በመላው አውሮፓና ሜሪካ በተለይም ጣሊያን ውስጥ ብሪታንያና አሜሪካ ጣሊያንን ከኢትዮጵያ ማስወጣት የፈለጉት ሀገሪቱን ለራሳቸው ማቆየት ስለፈለጉ ነው ከሚል ፈጣን መደምደሚያ ላይ ተደረሰ። ጣና ሃይቅም በተመለከተ ሪኬት ስምምነት ለመፈራረም እየሞከሩ ነው የሚሉ ዘገባዎች ይህንኑ የብሪታንያን የቅኝ አገዛዝ መስፋፋት ፍላጎት አስመልክቶ የሚሰነዘረውን ክስ አባባሱት። የኢትዮጵያ የነዳጅ ዘይት ሀብት ክምችት ክፍተኛ ስለመሆኑ የተጋነነ እምነት መኖሩም ባጠቃላይ ታሪኩን እውነት አስመሰለው።
የብሪታንያ መንግስትም ሪኬት ለዚሁ ጉዳይ የሚውል ገንዘብ ከሀገሩ ስለማሻገሩ የማያውቅ መሆኑን በማስተባበል ወዲያዉኑ መግለጫ አወጣ። “ብሪቲያንያም ጣና ሃይቅን በተመለከተ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያን ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ፍልጎት እንደሌላት፣ ይህንንም የሚመለከት ጉዳይ ቢሆን እንኳ የጣሊያንንና የኢትዮጵያን ውርክብ ላለማባባስ ማንኛውንም ስምምነት ለሌላ ጊዜ እያሸጋገረ መሆኑን አስታወቀ። ከዚህም አልፎ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ስምምነቱን ተግባራዊ ከማድረግ ይታቀቡ ዘንድ እንዲመክራቸው በኢትዮጵያ ያለው ወኪሉን ማዘዙን ገለጸ። ከሦስት ቀን በኋላ ማለትም ነሃሴ 28 ቀን1927 የብሪታንያ መንግሥት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጁን አለማስገባቱን የሚያሳውቅ መግለጫ አወጡ።

በሪኬት ጉጉ አስተያየት ተገፋፍቶ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ስምምነቱን አድርጎ  የነበረው አሜሪካዊው እስታንዳርድ ቫኩዩም ዖይል ካምፓኒ የተባለ ድርጅት ነበር።  አፄ ኃይለሥላሴም ለሁለት ምክንያቶች ከዚሁ ድርጅት ጋር ስምምነቱን አደረጉ። አንዱ ምክንያት የኢትዮጵያ  መንግሥት ሀገር ለመከላከል ጥረት ገንዘብ በጣም ያስፈልገው የነበረ መሆኑና ከኩባንያው እቅድ ጋር በተያያዘ ሊገኝ የሚችለው ገቢ በዚያ ሀገር ቀውጢ ላይ በነበረችበት ወቅት ተስፋ ማጫሩ ነበር።  ሁለተኛው ደግሞ  የአሜሪካ ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም በኢትዮጵያ መኖሩ የሚያስገኘው ዲፕሎማሲያዊና  ፖለቲካዊ  ጠቀሜታ ነው።  ይህም ወራሪው ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ሊረዳ ይችላል የሚል ተስፋ ማሳደሩ አይቀርም።

የተደረገው ስምምነትና በኢትዮጵያ ያጫረው ተሰፋ ግን በጦርነት ላለመነካካት ፖሊሲ ከቀየሰችው ከአሜሪካ ፖሊሲ ጋር የሚቃረን ነበር።  በወቅቱ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ልክ በመስመጥ ላይ እንዳለች ጀልባ ነበረች።  ስለዚህም የአሜሪካ ስቴት ድፓርትመንት ለኦይል ካምፓኒው ወኪሎች መንግሥታቸው ምንም የደህንነት ዋስትና እንደማይሰጣቸው በማስገንዘብ የነዳጅ ዘይት ፍለጋና ልማት ሥራው የቱንም ያህል ትርፋማ ቢሆን በቅርቡ ጦርነት መካሄዱ ከማይቀርባት ሀገር ከበኢትዮጵያ  የገቡትን ውል እንዲሰርዙ መከራቸው።  ይኸው የአሜሪካ መንግሥታዊ አቋምም በጽሁፍ  ነሃሴ 28 ቀን 1927 ለለንደን፣ ለፓሪስ እና ለሮም ተላከ።  ኩባንያውም ውሉን ሰረዘ።  የኢትዮጵያ ተሥፋም በኖ ጠፋ።

አፄ ኃይለሥላሴም በኢትዮጵያ  ለአሜሪካው  ጉዳይ አስፈፃሚ በነገሩ የተሰማቸውን ጥልቅ ቅሬታ አሳወቁት።  አሜሪካ  ለሀገራቸው ምጣኔ ሃብታዊ  እድገት ሊረዳ  የሚችል የቴክኒክ ክሂልና የባለሙያ አቅም ቢኖራትም በኢትዮጵያ  ላይ ፖለቲካዊ ፍላጎት  እንደሌላት መገንዘባቸውን  ገለጹለት።  ወዳጅነታቸውን  ለማረጋገጥና አሜሪካ ለኢትዮጵያ ያላትን በጎ  ዝንባሌ ለማሳየት  ውሉን ተዋውለው እንደነበር አስገነዘቡት።  ይህ ሁሉ  እውነት እንደሆነ ጥርጥር የለውም።  ግን እንደ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ሁሉ የአሜሪካ መንግሥት  ቀዳሚ ፍላጎት ኢትዮጵያን መከላከል ወይም ማሻሻል ሳይሆን  እራሱን  ከውርክቡ በማግለል ከጠቡ አለመነካካት፣ ጣሊያንን አዋዝቶ  መያዝ ነበር።

የኢትዮጵያ ደጋፊዎችን ስንመለከት ደግሞ፣ ቀድሞም የአድዋ ድል ለጥቁር  ህዝቦች ታላቅ የምሥራች ነበር። ከበፊቱም ባርነት በህግ ሳይታገድ እንዲቆይ የሚሟገቱ ወገኖች ከጥቁር ህዝብ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም የሰብዓዊነትና የስልጣኔ ዋቢ አሻራ ዋጋ ለማሳጣት በሚጥሩበት በዚያን ወቅት በመዳፋቸው ስር ላሉት ጥቁሮች ከኔነት መጽናኛ ምርኩዛቸው አንዱ ስለኢትዮጵያ የሚሰሙት ታላቅ አፈ ታሪክ ነበር።  የምዕራቡን የባርነት ሥርዓት ለማቆየት ግብ ታሪክን የሚያጣምሙ የኃይማኖት፣ የፍልስፍናና የሳይንስ ሰባኪዎች በበዙበት በዚያ በ19ኛው ከፍለ ዘመን፣  ጥቁር ሰባኪዎች በቀላሉ በእጃቸው ሊገባ ከቻለው አስረጂ ምንጭ ከመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ  ስለአፍሪካዊያኑ ስለኢትዮጵያ እና ግብፅ ስልጣኔና ገናና ታሪክ አነበቡ።

መዝሙረ ዳዊት 67፡31 ላይ “መኳንንት ከግብፅ ይወጣሉ፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ተዘረጋለች”፣ መጽሀፈ  ኤርምያስ 13፡23 ላይ ደግም “በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን፣ ወይስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?”  የሚሉትን መሰል አባባሎች በጥልቀት እየተረጎሙ ሰበኩ።  ኢየሱስ በተሰቀለበት ዕለት መስቀል ተሸክሞ  የረዳውንን የሰመዖንን አፍሪካዊነት፣ በሀዋርያት ስራ ውስጥ  የተገለጸው አማኝ ሞገስ ያለው ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን መሆኑን አስተማሩ። ጥቁር ዘርን በተመለከተ የነኝህ የነኝህ ዋቢዎች መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ  መኖራቸው ሁዋላ ላይ በእንግሊዝኛው “ኢትዮጵያኒዝም ተብሎ ለተሰየመውና  በዚያ ባርነት በተንሰራፋበት ጨለማ ወቅት ጥቁሮች በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣ በሰበዓዊነታቸው እንዲያምኑ ላገዘው አፍቃሪ ኢትዮጵያ ተራማጅ እንቅስቃሴ ዋና ምንጭ ሳይሆን አልቀረም።

አፍቃሪ ኢትዮጵያዊነት ከደቡብ አፍሪካ አንስቶ  እስከ ካሪቢያን፣ አልፎም እስከ ደቡብ አሜሪካ ድረስ በመዝለቅ አንዱ የጥቁሮች ኃይማኖታዊ አላባ ወይም በፈረንጅኛው ኤለመንት ሆኖ ቆይቷል።  በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ  ያሉ ሰብዕናዎችንና ክስተቶችን በአፍሪካዊነት መነጸር የሚያይ ማህበራዊ፣ ኃይማኖታዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ነው። በወቅቱ ተንሰራፍቶ የነበረውን የክርስትና ሰበካም የጥቁሮችን የበታችነት አስፍኖ ለማቆየት ዓላማ እውነታው የተጣመመበት ትምህርት እንደሆነም አድርጎ  ይቆጥረው ነበር። እንደ የልቪናግተን አባባል “ኢትዮጵያኒዝም የጥቁሮችን መገበር ተገቢነት ለማስረገጥ በአስረጂነት ከሚቀርቡት የመጽሀፍ ቅዱስ የሃም ልጆች እና የኖህ እርግማን አፈ ታሪኮች በተቃራኒ የቆመ ዕይታ ነበር ማለት ይቻላል። ባጠቃላይ ሊዮናርድ ባረት:

“ኢትዮጵያዊን የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጆች ነን ብለው ያምናሉ። ለዚህም ማስረጃቸውን ይጠቅሳሉ። በተጨማሪም አምልኮዎችን፣ ክብረ በዓላትን፣ ቅዱስ የሰበካ ጉባኤዎችን፣ መስዋዕት ማቅረብን ባጭሩ ሰለአማልክት ክብር የሚከወኑ ሁሉንም ድርጊቶች የጀመርን ነን ይላሉ። ስለዚህ ከሰው ልጆች ሁሉ የበለጡ ሃይማኖተኞች፣ የሚያቀርቡትም መስዋዕት ከሁሉም በላይ አማልክትን የሚያስደስት ነው ብለው ያምናሉ።  ሃይማኖተኛነታቸው የተነሳም በማንም ባዕድ አገዛዝ ስር እንዳይወድቁ ማድረግን በመሳሰሉት ጸጋዎች አማልክት እንደባረኳቸው ያስረዳሉ። ምንጊዜም በመካከላቸው ላለው ህብረት ምስጋና ይግባውና ሁልጊዜም ነፃነታቸውን እንዳስከበሩ ይኖራሉ።”

በማለት የጠቀሱት፣ የሲሲሊው ጸሀፊ የዲዮደሩስ አባባል ስለ ኢትዮጵያና ህዝቧ የነበረውን ጥንታዊ ግንዛቤ ባጭሩ ሳያስቀምጠው አይቀርም።

ይህን መሰሉ ግንዛቤ የወለደው የኢትዮጵያኒዝም እሳቤም በማርቆስ ጋርቬይ ጊዜ  ከርዕዮተ  ዓለምነት አልፎ በተግባር የሚገለጽ እንቅስቃሴ ሆኗል።  በእሳቸው እንቅስቃሴ  የሚታመንበት አምላክ የኢትዮጵያ አምላክ ነው። እ; ኤ፡አ በ1920  ኒዮርክ ውስጥ  ዓለም አቀፍ የጥቁር ዘር ዕድገት ማህበር  /ዘ ዩንቨርሳል ኔግሮ  ኢምፕሮቭመንት አሶሲዬሽን/  ጉባኤ የዓለም ጥቁር መብቶች አዋጅን /ድክላሬሽን ኦፍ ዘ ራይትስ ኦፍ ዘ ኔግሮ ፒዩፕልስ ኦፍ ዘ ወርልድ/  ባጸደቀበት ወቅት ያወጣውና  ሁሉን አቀፍ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በማለት የሰየመው መዝሙር ስንኞች ወደ አማርኛ ሲመለሱ እንዲህ ይላሉ:

ኢትዮጵያ የአባቶቻችን ምድር፣
አማልክት ሊጎበኙሽ፣ የሚመርጡሽ በፍቅር፣
በሌሊት ድንገት ሲመጣ፣
ማዕበል የተቀላቀለበት ደመና፣
ጦራችን ገንፍሎ ወጣ፣
ድል ማድረግ አለብን በውጊያው፣
ጎራዴዎች ሲያበለጨለጩ፣
ሲመዘዙ ካፎቴያቸው፣
ድል ለኛ ሞገስ ነው፣
በቀይ፣ በጥቁርና ባረንጓዴው ለምንመራው፣

_ አዝማች _

ገስግሱ፣
ወደ ድል ገስግሱ፣
አፍሪካን ነፃነት አልብሱ፣
ጠላትን ለመግጠም ተነሱ፣
ከቀዩ፣ ከጥቁሩና ካረንጓዴው ሃይል ጋር ገስግሱ፣
ኢትዮጵያ ጠላቶችሽ ወድቀው፣
ተፍረከረኩ፣
በሃይል ተመተው፣
በጉልበታቸው ተንበረከኩ፣
ልጆችሽ በጋለ ፍቅር፣
ተናገሩ፣
ርቀት ካላቸው ባህር፣
ማዶዎች መሰከሩ፣
ዬሆ! ታላቁ እኛን ሰምቶናል፣
ለቅሶአችንን፣ እንባችንን አይቶልናል፣
በፍቅሩ መንፈስ አንቀሳቅሶናል፣
በመጭዎቹ ዓመታት፣
አንድ ላይ ያሰባስበናል።

ማርቆስ ጋርቬይም በጽሁፋቸው ውስጥ “እኛ ጥቁሮች አንድ ዓይነት አርአያ አግኝተናል።  ምንም እንኳ የእኛ አምላክ ቀለም የሌለው ቢሆንም ሰው የሚያየው በራሱ መነፀር ነው። ነጮች አምላካቸውን የሚያዩት በነጭ  መነፀር ነውና  እኛም በኢትዮጵያ  መነፀር እያየን እናመልካዋለን”  ብለዋል።  በአፂ ምኒልክ መሪነት የኢትዮጵያ  ሃይል በጣሊያን ወራሪ ላይ በአድዋ የተቀዳጀው ድልም ድልድይ ሆኖ የጥንታዊቷን ኢትዮጵያ የታላቅነት ክብር ከዘመናዊ ዓለም ጋር አገናኘው። ታዲያ  ይህ የማገናኛ  ድልድይ ስራ እ፡ኤ፡አ  በ1890 ዎቹ ከፍፃሜ  ይድረስ እንጂ ግንባታው የተጀመረው የተቀረው የአፍሪካ ክፍል በውጭ ሃይላት አገዛዝ ቀንበር ስር ሲወድቅ ኢትዮጵያዊያን ብቻ በተከታታይ የተሰነዘረባቸውን ወረራ በድል ሲመልሱ ነበር።  በዚያው ክፍለ ዘመን እንኳ በ1870ዎቹ የግብፃዊያንን፣ በ1880ዎቹ የመሃዲስቶችን ተደጋጋሚ ጥቃቶች መክተው መልሰዋል።  የአድዋ ድል ደግሞ ይህን የነፃነት ቀናዒነት ይበልጥ  አደመቀው። የዓለምንም ቀልብ ሳበ።  የአውሮፓ መንግሥታት ዲፕሎማቶቻቸውን  ወደ አዲስ አበባ እንዲልኩ፣ ከኢትዮጵያ ጋር 19  ድንበርን የሚመለከቱ ስምምነቶችን እንዲፈራረሙ አደረጋቸው።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ  ለነበሩት የአፍቃሪ ኢትዮጵያዊነት እንቅስቃሴ መሪዎችም የአድዋው ድል የሞራል እርሾ  ሆኗቸዋል።  ከእንቅስቃሴው ግንባር ቀደም መሪዎች አንዱ ጀምስ ድዋኔ ግብጽና ሱዳን ውስጥ ያሉትን ክርስቲያን አፍሪካዊያን ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው መፍትሄ ይፈልጉለት ዘንድ ለምኒልክ ደብዳቤ የፃፉት የአድዋውን ድል ተከትሎ ነበር። ለዚህም ጉዳይ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ ሞክረዋል። የነፃዋ  ኢትዮጵያ ተምሳሌትነት በዙሉ እና በሌሎቹ የደቡብ አፍሪካ ክፍሎች ውስጥ ጠንክሮ  ሠርጾ ነበር። እ፡ኤ፡አ፡ በ1935 _1936  ናታልና ዙሉ ክፍላተ ሀገራት ውስጥ  ስለኢትዮጵያ ይደረግ የነበረውን የአዳር ጸሎት ለመከታተል የሚጎርፉት አዳዲስ መዕመናን ቁጥር እጅግ የትዬ ለሌ ነበር።  መልከ ፃዲቅ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን  እና የአብስኒያ ኮፕቲክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሚለው ስያሜ የተሰጣቸው ገናና አብያተ ክርስቲያናት ነበሩ።

እ፡ኤ፡አ፡ በ1930ዎቹ ከጀማይካ፣ ምዕራብ ኪንግስተን ደሳሳ ጎጆዎች ሲፈልቅ የአልባሌ ሰዎች ስብስብ ከመባል አልፎ፣ በተጀመረበት ሀገር ህዝብ ውስጥ  የማይነቃነቅ መሰረት የጣለ ብቻ ሳይሆን ከካሪቢያን ወጥቶ በሰሜን አሜሪካ፣ በብሪትሽ አይልስ፣ በአፍሪካ  ውስጥ መስፋፋት የቻለው የራስ ተፈሪያዊያን እንቅስቃሴ አመጣጥም ውልዴቱ ከዚህ የኢትዮጵያና የጥቁሮች ህዝባዊ እንቅስቃሴ ትስስር ጋር የተያያዘ ነው።  በሌላ አባባል የአፄ ኃይለሥላሴ መንገስ ወይም የእሳቸው የጀማይካ ጉዞና  የዝናብ መዝነብ ያመጣው ድንገቴ ክስተት አይደለም ለማለት ነው።

ከሃይማኖቱ ውጭም በአርነት ትግሉ መስክ በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩት እህት የአፍሪካ ሀገሮች ታጋዮችም ኢትዮጵያ ፋና ወጊ መብራታቸውና የራዕይ ምንጫቸው ነበረች። ለዚህም ነው የናይጀሪያ ድኀረ ነፃነት የመጀመሪታ ፕሬዚዴንት የነበሩት ዶክተር አዚኪዊ:

“ኢትዮጵያ ጥቁር ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርባት የመጨረሻው ሀገር ነች። በዚህ ክፍለ  አህጉር ላይ የአፍሪካ ቀደም አባቶች የመሰረቱት መንግሥት የታሪክ ዋቢ ነች።  ኢትዮጵያ  ከዘመን ወደ ዘመን እየተሸጋገረች ህልውናዋን ጠብቃ መኖሯ የሚደነቅና መደነቅም ያለበት ነው።”

በማለት ተናግረው የነበረው።  ከአድዋው ድል አርባ ዓመት በሁዋላ ጣሊያን ቂሟን ልትወጣ የመላው ጥቁር ህዝብ ዕንቁ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ስታካሂድ በግልጽም ይሁን በተዘዋዋሪ የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታት ከእሷ ጎን ቆመዋል። በተቃራኒው ግን በአፍሪካም ይሁን በተቀረው ዓለም የተቀጣጠለውን አፍቃሪ አፍሪካዊነት የትግል ስሜት አነስቷል። እልህ አጭሯል። በአጠቃላይ መላው ጥቁር ህዝብ፣ በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም ለፍትህ የታመኑ አውሮፓዊያን ነጮችም ለኢትዮጵያ ያላቸውን ወገናዊነት አጠናክሯል። የነኝህም ጥረት በውጭ የነበረውን ህዝባዊ ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ ያደላ እንዲሆን አድርጎታል።

ባህላዊ እሴቶቻቸውን  ያልጣሉ  የአፍሪካ ምሁራን ተሰባስበው ከነበሩባቸው  የአህጉሩ ከተሞች፣ ከካርቢያን ደሴቶች፣ ከጥቁር አሜሪካዊያን በኩል ወረራው ያጫረው የመጠቃት ስሜት ተስተውሏል።  በጀማይካ ኪንግስተን ከተማ፣በኩባ ስኳር አምራች ክፍለ ሀገራት፣በማዕከላዊ አሜሪካ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች፣ በነቁጧ በግሪናዳ እና በሃርለም ጥቁሮች ከኢ ትዮጵያ ጎን ቆሞ ለመዋጋት የሚጠይቅ ፊርማ አሰባስበው ለባለሥልጣን አቅርበዋል።   የሃርለም ጥቁሮች ዕድሉ ሳይሰጣቸ  ሲቀርም በኒዮ ርክ እና በኒውጀርሲ ከተሞች  መነገዶች ላይ በአካባቢው  ከነበሩ ጣሊያናዊያን ጋር ተጋጭተዋል።  ለብዙ ጥቁሮች፣  ኢትዮጵያ የአፍሪካ ክፍለ አህጉርን ፖለቲካዊ ነፃነት ለመታደግ የመጨረሻው የመከላከያ  ግንባር ነበረች።  በአንድ አውሮፓዊ ሀገር ላይ አስገራሚ ድልን ያስመዘገበች ባለድንቅ ታሪክ ሀገር።  እናም የዚህች ብቸኛ ነፃ ጥቁር ሃገር በድጋሚ በጣሊያን መወረር፣ በጥቁር ምሁራን ዘንድ ያጫረውን እልህ ለመገንዘብ የሚከተሉትን ክስተቶች  ማስተዋል ብቻ በቂ ነው።

አንድ ለትምህርት ወደ አሜሪካ ይጓዝ የነበረ ጋናዊ ወጣት  ለንደን ውስጥ በጋዜጣ ላይ “ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ወረረ”  የሚለው ዜና ተጽፎ  ሲያነብ የተሰማውን ሲገልጽ:

“መላው ለንደን በእኔ ላይ በተናጠል  ጦርነት ያወጀብኝ ሆ ኖ ተሰማኝ።  ከዚያም ለጥቂት ደቂቃዎች ዕቁብም የሌለው እያንዳንዱ መንገደኛ ላይ አፍጥጨ እነኛ  ሰዎች የቅኝ አገዛዝ መራራነትን ሊገነዘቡ ይችሉ እንደሆነ እያሰላሰልኩ ከመደመም፣ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሥርዓት መውደቅ የበኩሌን ትግል ላበረክት የምችልበት ዕለት እንዲመጣ ከመጸለይ  ሌላ  ምንም ማድረግ አልቻልኩም። ”ብሏል።

ይህን የተናገሩት ከነፃነት በኋላ የጋና የመጀመሪያ  መሪ የሆኑትና የአሜሪካ  የስላላ ድርጅት ደመወዝተኛ በነበረ የራሳቸው ወታደራዊ መኮንን መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባቸው  ከዋሜ ንኩርማ ነበሩ።  ከሴራሊዮን ዋላስ ጆንሰንም የጣሊያንን ወረራ በመቃወም አፍሪካን ሞርኒግ ፖስት ላይ ባወጡት ጽሁፍ ሰበብ እ  ኤ አ  በ1936 ታስረው 50 ፓውንድ ተቀጥተዋል።  የተከሰሱበት ወንጀል ብጥብጥ ለማነሳሳት መሞከር የሚል ሲሆን ከጽሁፋቸው ለመጥቀስ:

“አውሮፓዊ የሚያምንበት፣ አፍሪካ ውስጥ  ባሉ ቤተክርስቲያኖቹ የሚቆምለት አንድ አምላክ አለው።  ስሙ ማታለል ተብሎ  በሚጻፈው አምላክ ያምናል።  ህጉ እናንተ የሰለጣናችሁ  አውሮፓውያን ያልሰለጠኑትን አፍሪካውያን በማሽንገን ማሰልጠን አለባችሁ። እናንተ  ክርስቲያን አውሮፓውያን አረመናውያኑን  አፍሪካውያን  በቦምብ፣ በመርዝ ጋዝና በመሳሰለው ክርስቲያን ማድረግ አለባችሁ በሚለው ያምናል።”

የሚል  ይገኝበታል።  የዌስት ኤንድ፣ የአፍሪካ ምሁራንንና ቀስቃሾችን አካቶ  የያዘው የዋላስ ጆንሰንና  የጓደኞቹ ቡድን በአባላቱ ቁጥር ትንሽ፣ በሂደት ግን ተከታዮችን ያፈራና ውጤታማ  ሥራ የሰራ ነበር።  ቡድኑ ከቅኝ አገዛዝ ለመላቀቅ የሚያስችል ርዕዮተ ዓለም የመ ቅረጽ ትግል በፋና ወጊነት  ጀምሯል።

አፍቃሪ ኢትዮጵያው ቁጭት ባስከተለው መነሳሳትም ድጋፋቸውን ለኢትዮጵያ  ህዝብ ለመስጠት ብዛት ያላቸው ኮሚቴዎች በየቦታው ተቋቁመዋል። በብሪታንያ the International African Friends of Ethiopia (IAFE)፣ በአሜሪካ the American Committee for Ethiopia (ACE)፣ በትሪናዳ the Afro-West Indian League, the West Indian Youth Welfare League, the Negro Welfare Cultural and Social Association, the National Association of the African Progeny፣ በብሪትሽ ጉያና ጆርጅ ታውን the Afro-American Association, the League of Coloured Races፣ በሃይቲ the Ligue  haitienne pour la Defense du Peuple Ethiopien፣ በማርቲኒኪ the Group Jean, the Front Commun፣ በፓሪስ the Ligue de la Defense de la Race Negre በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

በምሳሌነት ከተመለከቱት ውስጥ የ IAFE ዋና ዋና ዓላማዎች 1ኛ/ በፋሽስት ጣሊያን  ወረራ ለተካሄደባት ኢትዮጵያ የብሪታንያን ህዝብ ድጋፍ ማስገኘት  እና 2ኛ/ በሚቻለው አቅምና በማንኛውም መንገድ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ፖለቲካዊ ነጻነትን ለመስጠበቅ እገዛ መስጠት ነበር።  የኮሚቴ ሊቀመንበር ሮበርት ጀምስ ሲሆኑ ጸሀፊው ደግሞ  ጆሞ ኬንያታ ነበሩ። ጆሞ  ኬንያታ Labour Monthly ላይ ”ከአብስኒያ ላይ እጃችሁን አንሱ!“  በሚል ርዕስ ባወጡት ጽሁፍ ኢትዮጵያን መርዳት ፋሽዝምን መዋጋት መሆኑን አስገንዝበዋል። “ኢትዮጵያ ለወራሪው ሃይል የሚኖራትን ምላሽ ሲያስገነዝቡም:

”ኢትዮጵያ በንጉሠ ነገስቷ መሪነት፣ በወታደሮቿ፣ በጀግንነቷና  በባህላዊ እሴቶቿ ትመካለች።  መንበርከክ የማይታሰብ ነው።  ሁልጊዜም እንደምታደርገው ይህን ወሰን ያጣ የኢምፔሪያሊዝም ድፍረት በመመከት ነፃነቷን ለመጠበቅ አሁንም ትዋጋለች።”

ያሉት።  የዚሁ ኮሚቴ ገንዘብ ያዥ  የነበሩት ደግሞ የማርቆስ ጋርቤይ ባለቤት ወ/ሮ  አሚ አሸውድ ጋርቤይ  ናቸው። ከስራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላቱም ጆርጅ ፓድመር፣  ከትሪናዳ ሳሚ ማኒንግ፣ ከሶማሊያ  ማሃመድ ሰይድ ይጠቀሳሉ።

በ1921  በተካሄደው አፍቃሪ አፍሪካ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የግሪናዳው አልበርት መሪይሰው፣  እንግሊዝ ማንሸስተር ውስጥ የነበረው የኔግሮ  ዌልፌር  ማህበር ፐሬዚዴንት ዶከተር ፒተር ማክዶናልድ ሚሊያርድም ሌሎቹ የኮሚቴው አባላት ናቸው።

እ ኤ አ በ1936  መጀመሪያ ላይም የክብር ጸሃፊው  ፐሮፌሰር ኤች ኤስ ጀብንስ የሆኑት የአብስኒያ ማህበር የሚባል ተቋቋመ።  ማህበሩ ለንደን ውስጥ  ቢሮ  በመክፈት ለኢትዮጵያ እገዛ ለማስገኘት በቀየሰው ዓላማ መሰረት አንድ ሺህ  ፓውንድ የማሰባሰብ ጥሪ አቀረበ።  ከዚህም ሌላ ለኢትዮጵያ  የገንዘብ ብድር፣ እንዲሁም በመንግሥታቱ ማህበር ሊወሰዱ ይችሉ ለነበሩ ማዕቀቦች እና እርምጃዎች ህዝባዊ ድጋፍ የማሰገኘት እቅድ ነበረው።  ካባላቱም ውስጥ  ለኢትዮጵያ በነበራቸው ያላሰለሰ ድጋፍ ከታወቁት ያፓርላማ አባላት ራ ቨይቭያን አዳምስና ጀፈሪ ማንደር  በተጨማሪ፣ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን አስመልክቶ  በመጻፍ የታወቁት ጌታው ኖርማን ኤንጅል ይገኙበታል።

ከዚያም በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1935  ላይ  የአምስተርዳሙ የዓለም ጸረ ጦርነት ጉባኤ ለኢትዮጵያ ያለውን ድጋፍ የሚገልጥና  የወራሪውን ጠበ አጫሪነት የሚኮንን መግለጫ አውጥቶ  ነበር።  በዚሁ ዓመት ሚያዝያ ወር ውስጥ  ካርሎ ሮሰሊ የተባሉ ሰው  Giustizia Liberta  ላይ  በተከታታይ ባወጧቸው ጽሁፎች ጣሊያንን  በጥብቅ ተቃውመዋል።  እነኝህም መጣጥፎቻቸው How to Conduct the Campaign Against the War in Africa በሚል ርዕስ በመጽሀፍነት ለህትመት በቅተዋል።  ሌላው  የኢትዮጵያ ባለውለታ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ  ፕሬዚዴንት የነበሩት  ቪክቶር ባሻ ናቸው።  የለንደኗ  ሲልብያ  ፓንክረስም እንደዚያው።

የካርቢያን ጥቁሮችም ከፍተኛ በሆነ ድርጅታዊ ቅንብር ኢትዮጵያን ለማገዝ እጅግ ደክመዋል።  በእያንዳንዱ ደሴት ቢያንስ  አንድ ለኢትዮጵያ  ተዋጊ አርበኞች መዲሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶች መግዣ የሚውል ገንዘብ የሚያሰባስብ ድርጅት ነበር።   ጥቁር ሴቶችም በበኩላቸው ከፍተኛ  ሚና  ተጫውተዋል።  የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀን የሚል ዝግጅት እያደረጉም ገንዘብ ለማሰባሰብ ጥረዋል።  ከውስጣቸውም የ the Negro Welfare Cultural and Social Association መሪ የነበሩት ኢልማ ፍራንኮስ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ናቸው።  ማህበራቸው የተቃውሞ ስልፎችን አደራጅቷል፣  የመደብ ብዝበዛን ከዘር/ጎሳ ብዝበዛ ጋር  በማገናዘብ ከፍተኛ ቅስቀሳ አካሂዷል። የ New Times እና የ Ethiopian News ቅጂዎችም  በብዛት እንዲሰራጩ አድርጓል።  ማርቲኒኪ ውስጥም አፍቃሪ የሰራተኛው መደብ  የሆኑ የፖለቲካ አቀነባባሪዎችን የያዘው the Comite de Defense du Peuple Ethiopien ተመስርቶ  “ኢትዮጵያውያን በዘሮቻቸው ወንድሞቻችን ናቸው። እንደኛ  የተጨቆነ ዘር፣ የጥቁር ዘር’’ የሚል የድጋፍ ጥሪ ያስተላልፍ ነበር።  በትሪናዳም ዕቃ አውራጅና ጫኝ ሠራተኞች  በጣሊያን መርከቦች ላይ ላለመሥራት እምቢ  ብለው ነበር።  በጀማይካ፣ ኪንግስተን የUniversal Negro Improvement Association ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትም በ “ዘር ተዋረድ  የሃም ልጅነታቸው  ወደ ኢትዮጵያ  ገብተው ለመዋጋት ብዙ ሰዎች ፊርማቸውን በማሳረፍ የጠየቁበት ወረቀት ለባለሥልጣናት ቀርቧል።  በሌሎች የብሪታንያ ቅኝ ግዛቶችም የተለያዩ  ቡድኖችና ግለሰቦች ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበዋል።  አንድ ሰው ከሆንዱራስ በጀማይካ  ለቅኝ አገዛዙ ባለሥልጣ በጻፉት ደብዳቤ ”ለመዝመት ዝግጁ ነንና ፈጣን ምላሽ ይስጡን።  እኛ እዚያ ከመድረሳችን በፊት የመጨረሻው  ጣሊያናዊ  እንዲሞት አንሻም።“  ብለዋል።

በኩባም ሳልባዶር ግራሲያ አ ጉዬሮ እና ሌሎችም አፍሪካ ኩባዊያን የኮምኒስት ፓርቲውን ይሁንታ አግኝተው አፍቃሪ ኢትዮጵያ የሆነ ብሄራዊ ኮሚቴ አቋቁመዋል።  La Voz de Ethiopia የሚል የሬዲዮ  ስርጭትም ጀምረዋል።  አደላንቴ የሚባለው አፍሪካ ኩባዊ ጋዜጣም ባወጣቸው መጣጥፎችም በኢትዮጵያ የተካሄደውን ወረራ ከኩባ ዳግም ቅኝ አገዛዝ ጋር በማገናዘብ በስልጣኔ ስም ቅኝ አገዛዝን ለማጠናከር የታለመ መሆኑን ተንትኗል።  2000 ኩባዊያንም ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው ለመዋጋት ፈቃደኛ እንደነበሩ ተዘገቧል። 60 ምርጥ ነርሶችም ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድና ሙያዊ ግልጋሎታቸውን ለማበርከት ፈቃደኛ ነበሩ። በአጭሩ ኩባዊ ገጣሚ ኒኮላስ ጉዮሊን በሞሶሎኒ ላይ:

ምኑ የባህር ወንበደ ሰይጣን ነው!
ይህ ሞሶሎኒ!
ከዚያ ባልጩት መሳይ የፊት ትይታው!
እና ከነኛ ስግብግብ ጥፍሮቹ ጋር!

በማለት የገለጹት የእልህ ስሜት በብዙ የሀገራቸው ዜጎች ልቦና ውስጥ  ይንበለበል ነበር።

የኢትዮጵያ ወዳጆች እና ኢትዮጵያዊያን የጥበብ አርበኞች ለምሳሌ ዮፍታሄ ንጉሴ “አጥንቱን ልልቀመው” እያሉ በብዕራቸው ጥላትን ሲዋጉ፣ ወራሪው ደግሞ ከአድዋ ሽንፈቱ አርባ ዓመት በሁዋላ ቂሙን ለመወጣት በአደረገው ጦርነት ያገኘውን ድል እንዲህ እያለ አሞግሶ ነበር – አድዋ በሚል ርዕስ በኒኖ ራስተሊ ተጽፈው፣ ዲኖ ኦሊቪሪ በሙዚቃ በተቀናበሩት ስንኞች፡

አሸነፈ ተመመ፣ ሄደ በርምጃ ጦሩ፣

ድልን ካድማስ አድማስ፣ እያስተጋባ አየሩ፣

በሚሊዮን የሚቆጠሩ፣

ጥፍሮች በምርኮ ተንጰረጰሩ፣

ባደባባይ በአካል ታዩ፣ መሠከሩ፣

አልቻሉም ሊያመልጡ፣ ሊሰወሩ፣

ቦታውን ጣሊያኖቹ፣

በ እጃቸው አስገቡ፣ ተቆጣጣሩ፣ ወንዶቹ፣

በፊታቸው ፈገግታ እያስነበቡ፣

በስሜት እየዘመሩ!

አድዋ ነፃ ወጣች፣

በ እጃችን ተመልሳ ገባች፣

በአድዋ ድል ተመዘገበች፣

ተወለዱ ዳግም ጀግኖች፣

ለድል ገሥግሱ፣ ገሥግሱ …

መላው ዓለም አወቀ፣

የአድዋ የበቀል ፍሬያችንን አደነቀ፣

የ እኛም ነፍስ በደስታ ጩኸት ፈነደቀ፣

አታሞው ተሰማ አስተጋብቶ፣

የምድሩን ጩኸት ተክቶ፣

የደስታ እምባና ልባዊ ምኞት ፈንቅሎ።

ይህ መሬት፣

አንድ ዕለት፣

አፈረ የሆኑበት፣

ሠማዕታት ከሥሩ አሉበት፣

ጥላዎች

የደም ቀለም አሻራዎች፣

በልህ ይቃጠሉ የነበሩ፣

በደስታ እየዘመሩ።

አድዋ ነፃ ወጣች፣

በ እጃችን ተመልሳ ገባች፣

በ አድዋ ድል ተመዘገበች፣

ተወለዱ ዳግም ጀግኖች፣

ለድል ገሥግሱ፣ ገሥግሱ …

መላው ዓለም አወቀ፣

የ አድዋ የበቀል ፍሬያችንን አደነቀ፣

የ እኛም ነፍስ፣ በደስታ ጩኸት ፈነደቀ።

ያን ጊዜስ እንደዚህ ቢሉም በአባት እናቶቻችን ተጋድሎ አድዋ ተመልሳ ከሕጋዊው ባለቤቷ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እጅ ካምስት ዓመት በሁዋላ ገብታለች።  ዛሬስ?  የታሪክ ምፀቱ፣ ከአድዋ በበቀሉ፣ ካርባ ዓመት በሁዋላ ጣሊያን ቂሟን ለመወጣት ስትመጣ ባንዳ ሆነው ባገለገሉ ሰዎች ልጆች እና የልጅ ልጆች በሆኑ የራሳችን  ሰዎች የአድዋ     ድል ሲንኳሰስ፣ ሲያሻቸውም በደም     የተገነባው የጋራ     ታሪክነቱ     ሲካድ፣     በዚያ ከአራቱም ማዕዘናት የሀገራችን ክፍሎች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያዊን በአንድነትና በወኔ ቆመው ጠላትን እየተፋለሙ
በወደቁበት የአድዋ አፈር ላይ የቋንቋ     መስመር     ዘርግተው እየመተሩ ብሄር ብሄረሰቦች ወካይ የሚሏቸውን ቤቶች ሲሰሩ ምን ይሰማን ይሆን?  ደም የተቃቡን ባዕዳንስ  ምን ይሰማቸው ይሆን?  ኢትዮጵያ እስካለች ነው ኢትዮጵያዊያን በጋራ ተሰባስበን አድዋን በጋራነቱ ልናከብረው የምንችለው።  ታሪክ     ላንድ     ማህበረሰብ     ምርኩዙ     ነው። ምርኩዛችንን በዝምታ አሳልፎ መስጠቱ ያለውን አደጋ ተገንዝበን የአድዋ ድልን ማሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ክብሩን ማስከበርም ግዴታችን ይመስለኛል። ዝነኛው ገጣሚና ጠሀፊ ተውኔት ዮፍታሄ ንጉሴ በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት በጣፉት እላይ በገለጥኩት “አጥንቱን ልልቀመው”  ግጥማቸው  ውስጥ:

አጥንቱን ልልቀመው _ መቃብር  ቆፍሬ፣

ጎበናን ከሸዋ _  አሉላን ከትግሬ፣

ስመኝ አድሪያለሁ _ ትላንትና ዛሬ፣

አሉላን ለጥይት _ ጎበናን ለጭሬ::
ተሰበሰቡና _ ተማማሉ  ማላ፣

አሉላ ተትግሬ _ ጎበና ተጋላ::

ጎበና ሴት ልጁን _ ሊያስተምር ፈረስ፣

አሉላ ሴት ልጁን _ ጥይት ሊያስተኩስ::

አገሬ ተባብራ _ ካልፈጠረች እርካብ፣

ነገራችን ሁሉ _ የእንቧይ ካብ የእንቧይ ካብ::

ትምህርት እንዲስፋፋ _ ጉልበት እንዲጠና፣

አራቱ ጉባዔ _ ይነሱልንና፣

መኮንን ደረሶ _ አሉላ ጎበና፣

አገራችን ትማር _ አሁን እንደገና፣

ጎበና ተፈረስህ _ ጋር ተነሳ እንደገና::

ያሉት ጥሪ  አሁንም በሀገራችን ፈፋ ሜዳ፣ ከተማ ገጠር  እያስተጋባ  ይመስለኛል::  ምን ያህሎቻችን በእዝነ ህሊናችን  ጥሪውን እያዳመጥነው እና  ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠነው እንደሆነ እራሳችን ለራሳችን ጠይቀን  መልስ እንዲንሰጥ በመጠየቅ፣ ጽሁፌን በጥያቄ እዘጋለሁ::

ክብር ለአድዋ ሰማዕታት!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!