የእሥረኛውን ስንቅ


(ሪሳሪስ በ1969 ዓ. ም. ጽፎት የእጅ ጽሁፍ ቅጂው በዝግጅት ክፍላችን እጅ የሚገኝ) – አዲስ አበባ። አንድ ማለዳ። 1969 ዓ/ምህረት። ቁርሴን ከአሮጊቷ ጋር እንደ ልማዴ እየተነዛነዝኩኝ፣

“ታናሽ ወንድሜ በተራው አይወስድም ወይ ? ···” እየተነጫነጭኩኝ፣ እንደምንም ዋጥኩኝ እና እንደተለመደው ለእሥረኛው ሰውዬ ምግብ ለማድረስ በማለዳ ወጣሁኝ።

ከቤታችንም እልፍ ብሎ ካለው አውቶቡስ ማቆሚያ የምግብ ሳህኔን አቅፌ ሰጠባበቅ፣ አንድ ከሌሊት ዘበኝነት የሚመለሱ የሠፈራችን ሽማግሌ የመጀመሪያው አውቶቡስ በቅርቡ እንዳለፈ ከሰላምታ ጋራ አብረው ነገሩኝ። መጠበቅ ግድ ሆነ።

ወደ እሥር ቤቱ ገና ሳልደርስ ተመልሼ ምን ምን እንደምሰራ ሳወጣ ሳወርድ መምጣቷንም ሳላስተውል አንዲት ጠና ያለች ሴት ድምጧን አጥፍታ ለካ አጠገቤ ደርሳ ኖሯል። ባዶ እግሯን ነች። ፊቷ ላይ ያለው የስቃይ ምልክት እንቅፋት አሁን የመታት አስመስሏታል። ምናምን ለመጠየቅ ህፃናት ተቆጪ አባትን እንደሚጠጉት ዓይነት በትልቅ ችግር ተጠጋችኝ እና ዓየነ ቆቧን በሚያሳዝን አኳኋን እያንቀጠቀጠች:

“ጋሽዬ እህት እንዳለህ ጥደቅብኝ” ስትል ተነፈሰች።

እኔም ይሄ ከ“እህት” ጋራ ምን ግንኙነት አለው እያልኩ ስጨነቅ፣ መሬት መሬት እየተመለከተች፣ በአንድ እጇም ብረቱን ተደግፋ፣ በእግሯ አውራ ጣቶች መሬቱን እየወጋጋች፣ ቅልስልስ ባለ ማቃሰት ያለበት አነጋገር:

“ባለቤቴ ላምባ ለመግዛት ወጥቶ ”ህዝብ ሠራዊት/ ጠረ አብዮት” ብለው አሰሩት አሉ። አንዲት ልጄ ምድጃ ላይ ወድቃ ተቃጥላብኝ ለማሳከም መጥቼ እዚሁ ቀልጨ ቀረሁ · · · ጋሼ እህት እንዳለዎት ባኮትን።”

አተኩሬ እመለከታት ጀመርኩኝ። አሁንም እንዳቀረቀረች:

“ግርድና ሁለት ቤት ሞክሬ ነበር። አንደኛው እንደወጣ ጠፍቶ ቀረ። አንደኛው ደግሞ አስረግዞ አባረረኝ።” አለች እና የጠዋቱን ውሃ ንፍጧን በአደፈው ነጠላ አጥድታ ለመጥረግ ሳትጨነቅ ለቃለቀችው እና ንግግሯን ቀጠለች:

“ልጄን በቀደም ወስጄ ሚሲዮን በራፍ · · ·” ቀስ አለች እና · · · “ሚሲዮን በራፍ አስቀመጥኩት። አሁን እመጫት ነኝ ጋሽዬ · · · ተጠዳዲቼም አልጨረስኩኝም · · · አንዲት ለነብስ ያሉ ባልቴት ወድቄ አይተው በረንዳቸው አስጠገተውኝ ነበር። ባለቤትዮው ማታ ሲመጣ “የሰው ሰው በኋላ ደግሞ. . . ብሎ አባረረኝ · · · ጋሽዬ እህት እንዳለህ አትጣለኝ!· · · ምች እንዳይጠናወተኝ ብዬ ነው እዚህ ሥር ያደርኩት። · · · እህት የለህም? ”

አሁን የግዷን ቀና አለች። ዓይኖቿን ተመለከትኩኝ። ከማልቀስ እና ጭስ ብዛት ሞጭሙጨዋል። ከሥርም ኮዳ ሠርተዋል። የዕውነት! ሆዴ ተገላበጠ። አንድ በአንድ አጠናት ጀመር። አልፎ አልፎ የእሳት ፍንጣቂ የበሳሳው ያደፈ ቀሚሷን በቀኝ እጇ ከሆዷ ጋራ በጣም ጥብቅ አድርጋ ይዛለች። ትልቅ ሰው እንዲህ ሲያፍር አይቼ አላውቅም። አሁንም ትንፋሽ በበዛው የልመና ንግግር ቀጠለች።

“ሀገር ቤት እገባለሁ ብዬም አላስብ፣ እንዳው እዚህ እንደውሻ እንዳልሞት ብዬ ነው የምንፈራገጠው ያለሁት · · · ጋሽዬ እባኮትን እህት እንዳለዎት አይጨክኑ። ”

ተረበሽኩኝ። አሁንም አተኩሬ እመለከታት ቀጠልኩኝ። ሙሉ ለሙሉ አትመለከትም። ቀና ጎንበስ ነው።

“ለዓይን አስጠይፌ ለመጠጋት ከርፍቼ መሞቴ ነው ወንድምዬ · · · ያለህን · · · ያለህን ” ማልቀስ ጀመረች። የሚንጠባጠብ ዕንባ አይደለም። ዓይኗ እንደ ቀዳዳ ነው የሚያፈስ። የማደርገው ግራ ገባኝ። የተደገፈችውን ብረት በእጇ እያሻሸች:

“ጎንበስ ብዬ እግርህን እንዳልስም ማህጠኔ ቁስሉ አልዳነም ጋሽዬ · · · እህት የለህም? · · · ያለህን ጥደቅብኝ ጋሽዬ እባክህ?”

እህት አለኝ።

በደንብ ተመለከትኳት እና ኪሴ የነበረውን “ያለኝን” አሥራ አምስት ሳንቲም እና የእሥረኛውን ስንቅ እጇ ላይ አድርጌላት አውቶቡሱ ሲመጣ ዘልዬ ገባሁኝ። ያው ነው፣ እሷም እሥረኛ ነች ።