ጥራታቸውን ያልጠበቁ ዕቃዎች ማህበረሰቡን አማረሩ

ፍኖተ ዴሞክራሲ –  (ግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ) – ጥራታቸውን ያልጠበቁ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች ህብረተሰቡን እየጎዱ ነው – የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግምባር አባላት ናቸው የተባሉ ስድስት ግለሰቦች ደቡብ ሱዳን ውስጥ ታሰሩ – የሶማሌላንድ ሚኒስትር የወያኔው አገዛዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር እንዳማያሳስባቸው ገለጹ።

ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች በአብዛኛው ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸውንና ቁጥጥር ለማድረግ ስልጣን የተሰጠው ድርጅት ስራውን በሚገባ ማከናውን እንደተሳነው የወያኔ የዜና ምንጮች ገልጸዋል። ደረጃቸውን ያልጠበቁና ጥራት የጎደላቸው ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ የቻሉት የሰለጠኑ የባለሙያዎች አለመኖራቸው እንደ ምክንያት ይሰጥ እንጅ ዋና ጉዳይ ሙስና መሆኑን አንዳንድ ወገኖች በምሬት ይገልጻሉ። ባለፉት ዓመታት የወያኔ የንግድ ኩባንያዎች ጥራት የሌላቸውን እቃዎች በጥቂት ገንዘብ ከውጭ በማስመጣትና አገር ውስጥ በከተኛ ዋጋ በመሸጥ ከፍተኛ ገንዘብ ሲያካብቱ የቆዩ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ቁልፍ ቁልፍ ቦታ ላይ ያሉ የወያኔ ባለስልጣኖች ከፍተኛ ጉቦ በመቀበልም እነዚሁ ዕቃዎች እንዲገቡ አድርገዋል። ለጤና ጠንቅ የሆኑ የምግብ ዕቃዎች፤ ጥራት የሌላችው ግብአቶች፤ ጊዚያቸው ያለፈ መድሐኒቶች፤ ደረጃቸው ውድቅ የሆነ ሲሚንቶና የማሽነሪ ዕቃዎች እና ሌሎች በርካታ ዕቃዎች ጥራትና ደረጃቸው ሳይመረመር ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የነበሩት ገንዘብ በቃኝ በማይሉ በአገዛዙ ባለስልጣኖች መሆኑ ገሀድ ነው የሚሉ ወገኖች በርካታ ናችው።

የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግምባር አባሎች ናቸው የተባሉ ስድስት ሰዎች በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ በጁባ ውስጥ በመንግስቱ የጸጥታ ኃይሎች መታሰራቸውን ሱዳን ትሪቡን የተባለው የሱዳን ጋዜጣ ዘግቧል። ከጥቂት በፊት ከወያኔ አገዛዝ ጋር ተደራድሮ እጁን ሰጥቷል ተብሎ የተወራለት ቱዋት ፖል ሰዎቹ እንዲያዙ ያደረገው የግምባሩ ቃል አቀባይ ነው ብሎ ከሷል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ የቱዋት ፖል ክስን አጣጥሎ ቱዋት ፖል ድርጅቱን ሳያማክር ለወያኔ እጁን የሰጠ ከሀዲ ነው ካለ በኋላ ድርጅቱ በደቡብ ሱዳን መንግስት እየተረዳ የሚንቀሳቀስ መሆኑን አረጋግጧል። በጁባ መሳሪያ ለመግዛት ጥረት ሲያደርጉ የተያዙ የድርጅቱ አባላት መኖራቸውን ግን ያመነ መሆኑ ጋዜጣው ዘግቧል።

ባለፈው ሳምንት የወያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ጋር በጋራ በሰጠው መግለጫ ከእንግዲህ ወዲህ የስማሊያ መንግስት እውቅና የሌለውን ሱማሊያን የሚመለከት ማናቸውንም ጉዳይ አናስተናግድም የሚል ቃል መናገሩ የማያሳስባቸው መሆኑን የሶማሌላንድ የአገር ግዛት ሚኒስትር ከሃርጊሳ ከተማ በሰጡት መግለጫ ገለጹ። ሱማሌላንድ የሶማሊያ አካል ስላልሆነች ሱማሌላንድ በስም እስካልተጥራች ድረስ አያሳስበንም ብለዋል። አዲሱ የሶማሌያ መንግስት ሱማሌላንድ አሁንም የሶማሊያ ግዛት ናት የሚል አቋም ያለው ሲሆን በቅርቡ የተባበሩት አረብ ኢምሬት በሱማሌላንድ ውስጥ ትልቅ የጦር ሰፈር መመስረቷ የወያኔን አገዛዝ በከፍተኛ ደረጃ ያሳሰበው መሆኑን ይታወቃል።

ዝርዝር ዜና ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ያንብቡ