የተምች ትል እየተስፋፋ ነው

(ግንቦት 03 ቀን 2009 ዓ.ም.) – እህል ጨራሽ የሆነው የተምች ትል እየተስፋፋ ነው – ከሳኡዲ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ችግር ውስጥ እንደሚወድቁ ተገለጸ  – የወያኔ አገዛዝ በአባይ ጉዳይ የኡጋንዳና የሩዋንዳን እርዳታ እየጠየቀ መሆኑ ታወቀ – የአልሸባብ ታጣቂዎች በሶማሊያ የደፈጣ ጥቃት አካሄዱ።

በምዕራብና በደቡብ ኢትዮጵያ የተከሰተው እህል ጨራሽ ተምች ሰፋፊ አካባቢዎችን በማዳረስ እየተስፋፋ መሆኑን ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች እየገለጹት ይገኛሉ። ባጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በ31 ሺ ሄክታር መሬት ላይ የበቀለውን እህል ተምቹ ያበላሸው መሆኑን የወያኔ ባለስልጣኖች ሳይቀሩ እየገለጹት ሲሆን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋት ላይ መሆኑም ታውቋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በጅማና በአካባቢው ታይቶ የነበረው ተምች ወደ ኢሉባቦር፤ ቡኖ በደሌና ምሥራቅ ወለጋ ተስፋፍቶ ወደ ዘጠኝ ሺ ሄክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የበቀለ በቆሎን አበላሽቷል ተብሏል። በደቡብ ኢትዮጵያም ተስፋፍቶ በርካታ አካባቢዎችን አዳርሷል። ተምቹን ለማጥፋት እስካሁን የወያኔ አገዛዝ የወሰደው እርምጃ ያልሰራ መሆኑ የተነገረ ሲሆን ተምቹ በዚህ ስፋትና ፍጥነት እየተባዛ ከሄደ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊከሰት የሚችል መሆኑን በመጠቆም ብዙዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ሳኡዲ አረቢያ ሕገ ወጥ ናቸው ብላ ከምታባርራቸው ኢትዮጵያውያን መካከል አብዛኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከፍተኛ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል አንዳንድ ወገኖች እየጠቆሙ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት ለ7.7 ሚሊዮን ረሃብተኛ ምግብ ማቅረብ ያቀተው አገዛዝ ከሰው አገር በገፍ ተባረው የመጡ ኢትዮጵያውያንን ማስተናገድ የማይችል መሆኑን አጥበቀው ይገልጻሉ። በረሃብ ከሚሰቃዩት ኢትዮጵያውያንን ከመርዳት ባለፈ የሱዳንንና የሶማሊያን ስደተኞች ረሃብተኞችን የሚረዱት የእርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ያላቸው ገንዘብ እየተሟጠጠ መሆኑን እየገለጹ ሲሆን ከሳኡዲ ተባረው የሚመጡት ኢትዮጵያውን የሚረዳቸው አጥተው ችግር ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።

በግብጽና በወያኔ አገዛዝና በሱዳን መካከል ቀደም ብሎ የተመሰረተው ግንኙነትና በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የተደረገው ስምምነት በሱዳን እና በግብጽ መካከል በሃላይብ ትሪያንግል የይገባኛል ጥያቄ ዙሪያ በሱዳንና በግብጽ መካከል በተፈጠረው አለመግባባትና እንዲሁም በአባይ ድልድይ ምክንያት በወያኔ በግብጽ መካከል በጠፈጠረ ውጥረት አደጋ ላይ መሆኑ ታውቋል። የወያኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በግብጽ ቆይታ ካደረገ በኋላ በካይሮ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የሶስትዮሽ ስብሰባ እስካሁን መካሄዱ ያልተገለጸ ሲሆን አለመካሄዱ ውጥረቱ መባባሱን ያሳያል ተብሏል። የወያኔ አገዛዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ተብየው ቀደም ብሎ ወደ ኡጋንዳ ከዚያም ወደ ሩዋንዳ ሄዶ ውይይት ያካሄደው በአባይ ጉዳይ ላይ የአባይ ተፋሰስ አገሮችን ድጋፍ ፍለጋ መሆኑን በርካታ ውስጠ አዋቂዎች እየተናገሩ ይገኛሉ።

ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በሶማሊያ በወያኔ አገዛዝ በተሰማሩት ወታደሮች እና በ አልሸባብ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ተከፍቶ ጉዳት የደረሰ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገረዋል። ጋርሳና በተባለችው መንደር የአልሸባብ ኃይሎች ባካሄዱት የደፈጣ ውጊያ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ማወቅ ባይቻልም የተኩስ ልውውጡ ለረጅም ሰዓት እንድተካሄደ የአይን እማኞች ተናገረዋል።

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ዝርዝር ዜና ያዳምጡ