ህይወት በቀጠፈው ቆሻሻ ላይ ሌላ ቆሻሻ – – –

ወጣቶችን ሥራ የማስያዝ ዕቅድ እንዳልሰራ ታወቀ   – የቀላል ባቡር አገልግሎት ከፍተኛ ችግር እየገጠመው ነው – ቆሼ ላይ አሁኑም ቆሻሻ እየተጣለ ነው – ወደ አውሮፓ የሚሄዱ አፍሪካውያን ስደተኞች በባርነት እየተሸጡ ነው ተባለ::

ወጣቶችን ከሥራ አጥነት ለማላቀቅ ከፍተኛ እመርታ ተገኝቷል በማለት የወያኔ አገዛዝ ላለፉት ጥቂት ወራት ሲመጻደቅና ከበሮ ሲደልቅ የቆየ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ባለፉት ስምንት ወራት የታቀደው ተግባራዊ እንዳልሆነ አገዛዙ አምኗል። የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ለምክር ቤት ተብየው ባቀረበው ዘገባ 3.3 ሚሊዮን ወጣቶችን ሥራ ለማስያዝ ታቅዶ የነበረ መሆኑና ሥራ ሊይዙ የቻሉት ቁጥር 900 ሺ እንደሆነ ተገልጿል። ሥራ ይዘዋል የተባሉት ወጣቶች ቁጥር በጣም የተጋነነ መሆኑን የሚገልጹ ክፍሎች የሥራ ዕድል የተባሉት እዚህ ግቡ የማይባሉ መሆኑን ዘርዝረው በዩኒቨርስቲ ዲግሪ ለተመረቁ የኮብ ስቶን ማንጠፍ ሥራ መስጠት የሚያኮራ ሳይሆን የሚያሳዝን ክስተት ነው ይላሉ።

መጀመሪያውኑ በእቅድ ያልተሰራው የአዲስ አበባው የቀላል ባቡር አገልግሎት ከፍተኛ እክልና ችግር እየገጠመው መሆኑ እየተነገረ ነው። ዛሬ ሌሊት ከቃሊቲ ወደ ዳግማዊ ሚኒሊክ አደባባይ በሚሂደው የባቡር መስመር ላይ አንድ ሲኖትራክ መኪና መንገድ ሲያቋርጥ አደጋ በማድረሱ ከግምሽ ሚሊዮን በላይ የሚገመት ንብረት የወደመ ከመሆኑ በላይ እስከረፋዱ ድረስ የባቡሩ አገልግሎት በመቋረጡ በተጓጓዦች ላይ ከፍተኛ ችግር የፈጠረ መሆኑ ታውቋል። የወያኔ ባለሥልጣኖች ለቻይናው ኩባንያ ቀላል ባቡር እንዲሰራ ኮንትራት የሰጡት፣ ጠርቀም ያለ ገንዘብ ለመብላት እንጅ የሕዝቡን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል ካለመሆኑ ሌላ የማቋረጫ መንገዶችም ሆኑ ሌሎች የግንባታው ክፍሎች ከአደጋ ለመከላከልና የሕዝቡን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር ታቅደው የተገነቡ ባለመሆናቸው ከተሠራ ጀምሮ የተከሰቱት በርካታ አደጋዎች በሰው ህይወትና በንብረት ላ ይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። የመብራቱም መቆራረጥ ተጓጓዡን ሕዝብ ሲያማርር የቆየ መሆኑም የሚታወቅ ነው።

ከጥቂት ቀናት በፊት የቆሻሻው ክምር ተደርምሶ ከ200 በላይ የሚገመቱ ዜጎችን ህይወታቸውን ያጡበት በረጲ የሚገኘው ቆሼ አሁንም የከተማዋን ቆሻሻ እያስተናገደች መሆኗ አንዳንድ ክፍሎች እየተናገሩ ነው። ቀደም ብሎ በሰንዳፋ በ15 ሚሊዮን ዶላር ወጭ በፈረንሳይ የኮንስትራክሽን ኩባንያ አማካይነት ተሰርቶ የነበረው የቆሻሻ መጣያ ቦታ የአካባቢው ሕዝብ ከፍተኛ አመጽና ተቃውሞ በማሳየቱ ሥራውን ማቋረጡ ይታወሳል። ቦታው የእርሻ ቦታና ሕዝብ በብዛት የሚኖርበት አካባቢ በመሆኑ ለቆሻሻ መጣያ የማይመች መሆኑና ተቃውሞ ሊነሳበት እንደሚችል ግልጽ ነበር። የሰንዳፋ የሕዝብ ተቃውሞ እስከቀጠለና በሌሎች ቦታዎች ቆሻሻን ለማራገፍ የክልል ባለሥልጣኖችንና የሕዝቡን ይሁንታን የሚጠይቅ እስከሆነ ድረስ የአዲስ አበባው አስተዳደር የከተማዋን ቆሻሻ በቆሼ ላይ ከማራገፍ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም እየተባለ ነው።

ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ ላለፉት 5 ወራት ታስሮ ከነበረበት በቦሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው ፓሊስ ጣቢያ ወደ ማዕከላዊ ምርመራ የተዛወረ መሆኑ ጉዳዩን በቅርብ የተከታተሉ ወገኖች እየገለጹ ይገኛሉ። ማዕከላዊ የሚባለው አሰቃቂ ምርመራ የሚካሄድበት ቦታ በመሆን የሚታወቅ ሲሆን ጋዜጠኛው ወደዚያ የተወሰደው ለከፍተኛ ምርመራ ሳይሆን አይቀርም የሚል ስጋት ፈጥሯል። በተያያዘ ዜና በትናንትናው ዕለት በዋለው የፍርድ ቤት ችሎት በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ ውሳነ ሳያስተላልፍ የቀረ መሆኑና ለሚያዚያ 20 2009 ዓ.ም የተቀጠረ መሆኑ ተገልጿል።

በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ የሚሄዱ ስደተኞች ለገበያ እየቀረቡ በባርነት እየተሸጡ መሆናቸው የዓለም አቀፉ የስደተኛ ተቋም ገለጸ። በሁኔታው ውስጥ ካለፉ ግለሰቦች የተሰማ መሆኑን የሚገልጸው ተቋም ስደተኞች በባርያ ገበያ ለአገልግሎት የሚሸጡ መሆናቸውንና የእጅ ጥበብ ያላቸው ሰዎች ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያወጡ ይገልጻል። ሴቶችም በቁባትነት ለማገልገል እንደሚሸጡ አብራርቷል። በሊቢያ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች በተለይም በደቡብ ሊቢያ በሚገኙ ከተሞች እነዚህ የባርያ ገበያዎች መስፋፋታቸው አሳሳቢ በመሆኑ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል በማለት ተቋሙ አቋሙን አሳውቋል።

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ዝርዝር ዜና ያዳምጡ