ህገ መንግስቱን ማሻሻል ወይስ መለወጥ??

• *ህገ መንግስት፤ መንግስትን ማሰርያ እንጂ ህዝብን ማሰርያ አይደለም
• *ከገዥዎቹ ህግ የሚሰጠው ህዝብ ምንጊዜም ባሪያ ነው
• *ማንኛውም ህግ ወደ ህዝብ ማነጣጠር የለበትም

(አዲስ አድማስ) – በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የአገሪቱ ህገ መንግስት መሻሻል አለበት የሚል ጽኑ አቋም አላቸው፡፡ አንዳንድ ወገኖች ከእነ አካቴው እንደማይወክላቸው በመግለጽ መለወጥ እንዳለበትም ይሞግታሉ፡፡ አንጋፋው የህግ ባለሙያ አቶ ተማም አባቡልጉ በበኩላቸው፤ አሁን ያለው ህገ መንግስት ተቀዶ ተጥሎ አዲስ ህገ መንግስት መርቀቅ አለበት በማለት ይከራከራሉ፡፡ ለምን እንደሆነም ምክንያታቸውን በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡ ህገ መንግስቱ ባለበት ሁኔታም የአንዳንድ ህጎችና አዋጆች መሻሻል ተገቢ አለመሆኑን ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡ አዲስ በተረቀቀው የፀረ ጥላቻ ንግግር እና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት መቆጣጠሪያ አዋጅ ላይም ተቃውሞ አላቸው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መሪዎች ከምርጫው በፊት ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት ብለዋል፡፡ እንደ ህግ ባለሙያነትዎ በህገ መንግስቱ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ሲጀመር በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ተግባር ላይ ውሎ አያውቅም፡፡ ህገ መንግስቶቹ ሲወጡ የነበረው ህዝብ የሃገር ባለቤት እንዲሆን ሳይሆን ስልጣን ላይ ያለው አካል እንዲመለክ ለማድረግ ነው፡፡ እስካሁን የወጡ ህገ መንግስቶች ይህን ባህሪ የተላበሱ ናቸው:: አሁን ያለው ህገ መንግስትም ህዝብን ጠቅሞ አያውቅም፡፡ ህውሓት ህገ መንግስቱን ያወጣው ለህዝብ ሳይሆን ራሱ እንዲመለክበት ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ማስፈራሪያ ነው፤ በተግባር ስራ ላይ ውሎ አያውቅም፡፡

አሁን ያለው የፌደራሊዝም አወቃቀርና ህገ መንግስቱ ምንና ምን ናቸው?

አሁን ያለው የፌደራል አወቃቀር ከህገ መንግስቱ በፊት የተሰራ ነው፡፡ ቋንቋን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ፈፅሞ ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ አይደለም፡፡ ምናልባት ፌደራሊዝሙን መሰረት አድርጎ ሊሆን ይችላል የተረቀቀው፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱም ተተግብሮ አያውቅም፤ ፌደራሊዝሙም ህገ መንግስትን መሰረት አድርጎ የተዋቀረ አይደለም፡፡

እርስዎ “ህገ መንግስቱ ተቀድዶ መጣል አለበት” የሚል አቋም ነው ያለዎት፡፡ ምክንያትዎ ምንድን ነው?

በዚህ ጉዳይ ባወጣሁት መፅሐፍ ላይም በግልፅ ሃሳቤን አስቀምጫሁ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሲጀመር ህገ መንግስት የለውም፤ ኖሮትም አያውቅም፡፡ ህገ መንግስቱ የህውሓት/ኢህአዴግ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም፡፡ የህውሓት የፖለቲካ ፕሮግራም ነው፣ የተወሰኑ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ገብተውበት የፀደቀው፡፡ ህገ መንግስቱ ሙሉ ለሙሉ የህግ አላባውያን የሌሉበት የፖለቲካ ሴራ ነው፡፡ ለዚህ ነው በላዩ ላይ የሰፈሩት በሙሉ የማይፈፀሙ ሆነው የምናገኛቸው፡፡ ህገ መንግስቱ ላሉት የሌለውን የሰጠ ለሌሉት ደግሞ የሌለውን የሰጠ ነው:: ህገ መንግስቱ ባለቤት ዜጋ ሳይሆን ብሄር ብሄረሰቦች ናቸው፡፡ ብሄር ብሄረሰቦች ደግሞ ህጋዊ ሰውነት የላቸውም ይላል – ህገ መንግስቱ:: ለዚህ ነው ላሉት የሌለውን የሰጠ፣ ለሌሉት ደግሞ የሌለውን የሰጠ የሆነው፡፡ “የህውሓት ቅኝ አገዛዝ እና አዲሲቷ ኢትዮጵያ” በሚለው መፅሃፌ ይሄን በዝርዝር አቅርቤዋለሁ፡፡ እንግሊዝ በአረቦች ላይ የፈፀመችው ደባ አለ፡፡ የአረብ ሃገራት ህገ መንግስት ለምሳሌ በፍልስጤም ወጥቶ የነበረው ህግ፡- መሃመድን፣ ሃሊማን ወይም ግለሰብን አያውቅም፡፡ የሚያውቀው ሱኒ፣ ሺአ የሚባሉትን የእምነት ሴክተሮች ነው:: ሱኒ፣ ሺአ ደግሞ የህግ ሰውነት ስለሌላቸው መብታቸውን መጠየቅ የሚችሉበት እድል የለም፡፡ ይሄ የኢትዮጵ ህገ መንግስትም ዋነኛ ባህሪ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ለጫላ ሳይሆን ኦሮሞ ለሚባል ቡድን ነው የሚቆመው፡፡ ኦሮሞ ደግሞ ህጋዊ ሰውነት የለውም፡፡ ስለዚህ እንደ ሰው መብቱን ለመጠየቅ አይችልም፡፡ ለዚህ ነው ህገ መንግስቱ የማይተገበር ነው የምለው፡፡

ህገ መንግስቱ ምንም የሚፈፀም ነገር የለውም፡፡ ህውሓት፤ ብሔር ብሔረሰቦች እያለ እድሜ ልኩን እንዲገዛ የተደረገበት ሴራ ነው፡፡ ከዚህ መነሻ ነው ህገ መንግስቱ ተቀዳዶ ተጥሎ ሌላ መውጣት ያለበት፡፡ ሌላም ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአዲስ አበባን ጉዳይ የሚደነግገውን አንቀፅ 49 ማንሳት እንችላለን፡፡ በዚህ አንቀፅ የልዩ ጥቅም ጉዳይ ተደንግጓል፡፡ ልዩ መብት ምንድን ነው? ልዩ መብት ምን እንደሆነ እስካሁን አይታወቅም፤ ማበረታቻ ነው? ቅድሚያ መስጠት ነው? ምንድን ነው ልዩ ጥቅም? ምንነቱ የማይታወቅ ጉዳይ ነው የተቀመጠው:: ህውሓት ይሄን ሆን ብሎ ያደረገው ነው፡፡ የማይቻል ጉዳይ ነው በህገ መንግስቱ አስቀምጦ የሚያነታርከን:: ልዩ ጥቅም ምን እንደሆነ እንኳ በአግባቡ የሚያጠይቅ አይደለም፡፡ ይሄ የፖለቲካ ሴራ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ሙሉ ለሙሉ ሴራ ነው፡፡
ህገ መንግስቱን በማርቀቅ ሂደት የህውሓት ተወካዮች አልተሳተፉም ይባላል፤ ማስረጃም የሚያቀርቡ አሉ፡፡ ይሄን እንዴት ይመለከቱታል?

እነሱ በሂደቱ ኖሩ አልኖሩ አይደለም ቁምነገሩ፡፡ ሃሳቡ የማን ነው? የሚለው ነው:: ሀሳቡን ካቀበሏቸው በወቅቱ በአርቃቂ ኮሚሽኑ የነበሩ ያንን ማድረግ አይሳናቸውም:: አንድ ሃሳብ ተሰጣቸው፤ ህገ መንግስት አድርጉና አስፋፍታችሁ አውጡ ተባሉ፤ ያ ነው የተደረገው፡፡ ሃሳቡን ያመነጩት ህውሓቶች ናቸው፤ ሃገሪቱን የሚመሩት ህውሓቶች ናቸው:: ኢህአዴግን የፈጠረው ህውሓት ነው:: ኦህዴድን፣ ብአዴንን የፈጠረው ህውሓት ነው:: ስርአቱን የፈጠረው ህውሓት ነው፡፡ ይው ነው ሃቁ፡፡ ስለዚህ ህገ መንግስቱን በማርቀቅ ሂደት ህውሓት እጁ የለበትም የሚለውን እኔ ለማመን እቸገራለሁ፡፡ ህውሓት ሃገሪቷን እንዴት እንደሰራት፣ ምን ሲያደርጋት እንደነበር ለሚረዳ ሰው፤ ይሄ መከራከሪያ ውሃ የሚቋጥር አይሆንም፡፡ ሌሎች በህገ መንግስቱ ሃሳባቸው እንዳይገባ አስቀድሞ ያባረረው ህውሓት አይደለም እንዴ? የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ለኔ በአጠቃላይ የፖለቲካ ሴራዎች ድሪቶ ነው:: የህግ ባለሙያዎች ያላዩት ህገ መንግስት ነው፡፡ የልዩ ጥቅም ድንጋጌ ማለት ምን እንደሆነ፣ በህግ ባለሙያዎች ባለመታየቱ ነው፣ ዛሬ ትርጉም አልባና ለንትርክ በር ከፋች የሆነው፡፡

ህገ መንግስቱ መሻሻል ነው ያለበት ወይስ ሙሉ ለሙሉ መቀየር? የእርስዎ ግልፅ አቋም ምንድን ነው?

ህገ መንግስት ሃሳብ ነው፡፡ ምን ማለት ነው? አንድ ህዝብ፣ አንድ ሃሳብ አለው፡፡ ያንን ሃሳብ ወደ ሚጠጋ አምጥቶ ሁሉም ተስማምቶበት፣ ሃሳብ ወደ አንቀፅ የሚቀመጥበት ሰነድ ነው፤ ህገ መንግስት፡፡ ይሄኛው የህውሓት ሃሳብ እንጂ የህዝብ ሃሳብ ያልሆነ ህገ መንግስት ነው፡፡ የአሜሪካ ህገ መንግስትን ብንመለከት፣ መግቢያው፣ “እኛ የአሜሪካ ህዝቦች ያገኘነውን ህዝባዊ ነፃነትና ድል ለማቆየት–” “የሚል ሀሳብ ነው ያለው፡፡ የኛ እንደዚያ አይደለም፡፡ “እኛ ብሔር ብሔረሰቦች” ነው የሚለው፡፡ ይሄ ህዝባዊ ሃሳብ አይደለም፡፡ የህውሓት የፖለቲካ ሃሳብ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማሰር የወጣ ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ ተጥሎ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ገዥውን የሚያስርበት ህገ መንግስት ነው እንደ አዲስ መዘጋጀት ያለበት:: ህገ መንግስት መንግስትን ማሰርያ ህግ እንጂ ህዝብን ማሰርያ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይሄ ህገ መንግስት፤ የኢትዮጵያን ህዝብ አስሮ የከረመ ተብሎ መጣል ነው ያለበት፡፡

ከዚያ በኋላስ ምንድን ነው የሚደረገው?

ቻርተር እንመሰርታለና፡፡ አንድ የጋራ ቻርተር ተመስርቶ ስራውን መስራት ይቻላል:: እነ ዶ/ር ዐቢይም ጊዜያዊ ቻርተር ማቋቋም ነው ያለባቸው፡፡ በዚያ ጊዜያዊ ቻርተር ስር ደግሞ አዲስ ህገ መንግስት ማዘጋጀት ይቻላል:: የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃ ህዝብ አይደለም፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ከገዥዎች ህግ የሚሰጠው ሆኖ ነው የኖረው:: ከገዥዎቹ ህግ የሚሰጠው ህዝብ ደግሞ ምንጊዜም ባሪያ ነው፡፡ በሰጪው ፍቃድ ነው ሊሄድ የሚችለው፡፡ ህዝቡ ወደ ህግ ባለቤትነት መሸጋገር አለበት፡፡ ለዚህ ነው ህዝቡ ነፃነቱን እንዲያገኝ ከተፈለገ የቅኝ መግዣውን ህግ መጣል መቅደም ያለበት፡፡ ይሄ ህገ መንግስት ተቀዶ የተጣለበት ቀን ሁሉ መከበር አለበት:: ህገ መንግስት ከተሰጠው ህዝብ፣ ወደ ህገ መንግስት ያገኘ ህዝብ፤ ዲሞክራሲ ከተሰጠው ህዝብ፣ ወደ ዲሞክራሲ ያገኘ ህዝብ መሻገር አለብን:: እኔ በመፅሃፌ “ሃገርን ለህዝብ መመለስ” ብዬ ገልጫለሁ ነገሩን፡፡ ይሄን የሚሰራ አካል ተቋቁሞ ስራው መጀመር አለበት፡፡ ያ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያውያን ትመለሳለች:: ዘላቂ የመንግስት ስርአት ማቆም የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው፡፡

በሌላ በኩል፤ የፀረ ሽብር አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን የመሳሰሉ አዋጆች እየተሻሻሉ ነው፡፡ እነዚህ ህጎች የሚሻሻሉበትን መንገድ እርስዎ እንዴት ይመለከቱታል?

እነዚህን አሳሪ አዋጆች ይህ ህገ መንግስት ባለበት ሁኔታ ማሻሻልም መለወጥም ለኔ ትርጉም የለውም፡፡ እነዚህ አዋጆች ሲሻሻሉ ተሳታፊ እንድሆን ተጠርቼ ነበር፤ ፍቃደኛ አልሆንኩም:: ምክንያቱም አንደኛ፤ ይሄን ህግ ለማሻሻል እየተሞከረ ያለው በፓርቲዎች ድርድር ውጤት አይደለም፡፡ ሁለተኛ፤ ህገ መንግስቱ ተቀይሮ በአዲስ ህገ መንግስት መሰረት አይደለም ህጎች እየተሻሻሉ ያሉት፡፡ ስለዚህ በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ መሆን አልፈለግሁም፡፡ ማንኛውም ህግ ሲወጣ፣ በዋናው ህግ ወይም ህገ መንግስት መነሻና መሰረት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ አዋጆች ሲሻሻሉ፣ የነበረውን ህገ መንግስት አጣቅሰው ነው የሚሻሻሉት፡፡ ያ ህገ መንግስት ደግሞ ተቀባይነት የለውም፡፡ ይሄ ህገ መንግስት እያለ ሌሎች ህጎችን በማሻሻል ብቻ በሀገሪቱ ማህበራዊ ፍትህን ማምጣት ይቻላል የሚል እምነትም የለኝም፡፡ የፀረ ሽብር አዋጁ ደግሞ መሻሻል ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ መሻር ነው ያለበት፡፡ አሁን ከመሃል ያዋከቡት ነገር ነው እየሆነ ያለው፡፡ ሁልጊዜ ከመሃል እየጀመርን ነው የምንከሽፈው፤ ስለዚህ ከስር እንጀምር ነው ሁሌም የምለው፡፡ መነጋገርና መከባበር የሚመጣው ከስር ሲጀመር ነው፡፡ አሁን ህግን ማሻሻል አያስፈልግም፡፡

የፀረ-ጥላቻ ንግግርና ሃሰተኛ የመረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር የተረቀቀው ህግስ? ምን ያህል ጠቃሚ ነው?

ይሄ አዋጅ የጎሪጥ መታየት ያለበት አዋጅ ነው:: የጎሪጥ መታየት ብቻ ሳይሆን በኛ ሃገር የህግ አተገባበር ሁኔታ አስፈላጊ ህግም አይመስለኝም፡፡ በእርግጠኝነት የምናገረው ጀርመን በ1ኛው የዓለም ጦርነት ተሸንፋ ወይማር የሚባል ሪፖብሊክ ተመሰረተ፤ ኢኮኖሚው ወደቀ፣ ቨርሳይል ስምምነት ተፈረመ፡፡ ጀርመን ውርደት ውስጥ ገባችና መንግስቱም ደካማ ስለነበር፣ ቁርጥ ያለ ሀሳብ የሚናገሩ እንደነ ሂትለር ያሉ መሪዎች ስልጣን ያዙ፡፡ አንድ ማህበረሰብ እርግጠኝነት ሲያጣ ወደ ነበረበት ነው የሚመለሰው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም እገሌ እንዲህ አድርጎ፣ እከሌ እንዲህ ብሎ ነበር ወደሚል ነው ሁልጊዜ የምንመለሰው፡፡ ህዝብ የሚሄድበትን መስመር ሲያጣ የሚገባበት ቅርቃር ውጤት ነው፤ ይሄ የፀረ ጥላቻ ህግ:: መስመር አቅጣጫ የማጣት ውጤት ነው፡፡ ሃገሪቷ አቅጣጫ ስታጣ ነው ይሄ ህግ የወጣው፡፡ አሁንም መልሶ ህዝብን ማሰሪያ ህግ ነው እየወጣ ያለው እንጂ መሪዎች በአግባቡ ህዝባቸውን እንዲያስተዳድሩ የሚያስራቸው ህግ አይደለም:: አሁንም እየተደረገ ያለው፣ ህዝቡን እንሰረው ከሚል እሳቤ የሚመነጭ ነው፡፡ ነገር ግን መንግስቱ ነው አሁን ሊታሰርልን የሚገባው:: መንግስቱ ነው ሃገራችንን ሊመልስልንና አቅጣጫ ሊያስቀምጥልን የሚገባው፡፡ ሰው የሚጠላላው የሚሰዳደበው፣ አቅጣጫ ሲያጣ ነው፡፡ ህዝብ ንፁህ አቅጣጫ ሲያጣ፣ ወደ እርስበርስ መጠራጠርና መፈራረጅ ይገባል፡፡ ህዝቡ አቅጣጫ ሲያጣ ነው በተስፋ መቁረጥ፣ ወደ ጥላቻ የሚገባው፡፡ መጠየቅ ያለብን፣ አሁንም ሀገራችንን መልሱ ነው፡፡ ህግማንኛውም ወደ ህዝብ ማነጣጠር የለበትም፡፡ አቅጣጫና ፍኖተ ካርታ የተቀመጠለት ህዝብ ወደ ጥላቻ ፖለቲካ አይገባም፡፡ ብዙ ሃገራትን በምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ ጥላቻ ነግሶባቸወ የነበሩና የዘር ፍጅት የደረሰባቸው ሃገራት እኮ ከዚያ አስከፊ አደጋ የወጡት የሃገር ሃሳብና አቅጣጫ ነጥሮ በመቀመጡ ነው፡፡ ለኛም የሚጠቅመን ይሄው መንገድ ነው፡፡