ወቅታዊ ዜና

ፍኖተ ዴሞክራሲ ሬዲዮ (ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም.)  በባህር ዳር ከተማ ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ አስከፊውን የወያኔ አገዛዝን በመቃወም በአደባባይ ሰልፍ ወጥቷል። ሰልፈኛው ወያኔን የሚያወግዙና ፍትህ የሚጠይቁ የተለያዩ መፈክሮች በንዴትና በእልህ ሲያሰማ የነበረ ሲሆን የወያኔው ምልክት የሌለባቸው ሰንደቅ ዓላማዎችና የተያለያዩ መልክቶች የተጻፉባቸው በርከት ያሉ ሰሌዳዎች ተይዘው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ሲሰሙ ከነበሩትና ከተያዙት መፈክሮች መካከል “ ፖሊስና መከላከያ የሕዝብ ነው”፤ “ወያኔ ሌባ ነው” ይለያል ዘንድሮ” ጎጃም ጎንደር ወልቃይት ሁሉም የኛ ነው”፤ “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኝ እጄ ትርሳኝ”፤ “ዳር ሲቆረስ መሀል ዳር ይሆናል” ”ሁላችንም ኮሎኔል ደመቀ ነን”፤ ”ኢትዮጵያዊነትን መጠየቀ አሸባሪነት አይደለም”፣ ”በኦሮሚያ ወንድሞቻችንን የገደሉ በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ”፤ ”ነጻነት በጃችን ነው!”፣ ”ከወያኔ አገዛዝ ነጻ የምንወጣበት ዛሬ ነው!”፣ ”ኃይለማርያም ደሳለኝና ካሳ ተክለብርሃን ወልቃይት የትግራይ ነች ማለታቸው በአማራ ሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል ከማለት አይለይም” ወዘተ… ሰልፈኛው  ከተሰለፈባቸው አካባቢዎች ባሉ ተሰቅለው የነበሩ የወያኔን ባንዲራ አንስቶ በእውነተኛው ሰንደቅ ዓላማ ለውጧል። የስልክና የኢንተርኔት ግንኙነቶች ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ባይቻልም ከተለያዩ ምንጮች ለማወቅ እንደተቻለው የወያኔው አግአዚ ጦር በሰልፈኛው ላይ የኃይል እርምጃ ወስዶ ቁጥራቸው ያልታወቀ ወጣቶች መሞታቸውና በርካታ መቁስላቸውን ለማወቅ ተችሏል። ከጎንደር የመጡ ወገኖች ከተማው መግቢያ ወደከተማዋ ለመግባት ሲከለከሉ እነሱን ለማስገባት ለእርዳታ ከመጣው ሰልፈኛ ጋር ግጭት ተፈጥሮ ጉዳት ደርሷል። ኮበል ከሚባለው የወያኔ የማምረቻ ድርጅት ውስጥ የነበሩ አግአዚ ጦር ወደ ሕዝቡ ተኩሶ በርካታ ሰዎችን የገደለና ያቆሰሉ ሲሆን ሕዝቡም በንዴት የማምራቻ ድርጅቱን በእሳት አጋይቶታል ይባላል። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የከባድ መሳሪያ ድምጽ ሲሰማ እንደነበርም ምንጮቹ ይናገራሉ። ከባህር ዳር ወደ አዲስ ዘመን የሚወስደው መንገድ በሕዝቡ መዘጋቱና የወያኔ ደጋፊዎች ንብረት የሆኑ መኪናዎችና ንብረቶች መውደማቸውም ይሰማል።

ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም በአይከል በኩል በመተማና በሽህዲ መካከል የአካባቢው ሕዝብ የሚንቀሳቀሰውን ጦር በማስቆም የተወሰኑ መኪናዎች ያቃጠለ መሆኑ ይነገራል። በአሁኑ ወቅትም በመተማ፤ በሸህዲ እና በቋራ በወያኔ አግአዚ ወታደሮች እና በሕዝቡ መካከል ውጊያ እየተደረገ መሆኑንም አንዳንድ ምንጮች ይጠቁማሉ። በሁመራ ጎንደር መንገድ ከሳንጃ አካባቢም ለእርዳታ ወደ ጎንደር በሚንቀሳቀስ ጦር ላይ የአካባቢው ሕዝብ ጥቃት ሰንስዝሮ ወታድሮቹ እጃቸውን የሰጡ መሆናቸውም ይነገራል።

በወረታ በአዲስ ዘመንና በዳባት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውና የወያኔ አግአዚ ኃይሎች ጥቃት ፈጸመው ጉዳት ማድረሳቸው ይወራል። በትናንትናው ዕለት በተለያዩ ከተሞች በተደረጉት ሰልፎች ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን በርካታ ሰዎች ተይዘው መታሰራቸውም ተዘግቧል። በሁሉም ከተሞች የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት አልተቻለም።
ዝርዝር ዜና  ያንብቡ  ወይም ያዳምጡ