የነዳጅ እጥረት እየተባባሰ ነው

(ፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ) – የነዳጅ እጥረት እየተባባሰ ነው ተባለ – የተምች መንጋ በሌሎች ቦታዎች ተስፋፋ – ፈለገ ዮርዳኖስ የሚባለው ድርጅት ነዋሪዎችን እያስመረረ ነው – በአቶ በቀለ ገርባ ላይ ይቀርባል የተባለው መረጃ ሳይቀርብ ቀርቷል – በሻዕቢያና በወያኔ መካከል የጸጥታ ውጥረት የቀጠለው የድምበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ ባለመደረጉ ተባለ።

የነዳጅ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ እየተከሰተ መሆኑ እየታየ ነው። ባሁኑ ወቅት የተከሰተው የነዳጅ እጥረት መላው ሀገሪቱን ያዳረሰ ሲሆን እጥረቱ የቤንዚንና የናፍጣን አቅርቦትን ያጠቃለለ መሆኑን ታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ የነዳጅ የመኪና ሰልፍ በአንዳንድ ቦታዎ ከአንድ ኪሎሜትር በላይ መሆኑ የታየ ሲሆን መንገዶች ላይ መጨናነቅ ማስከተሉ እየተስተዋለ ነው፡፡ ለተከሰተው እጥረት ዋና ምክንያት የወያኔ አገዛዝ ወደ አገር ውስጥ ለገባው ነዳጅ የሚከፈለውን እዳ ለመክፈል የውጭ ምንዛሬ የሌለው በመሆኑ ነው በማለት ለጉዳዩ ቅርበት ያለቸው ወገኖች እየገለጹ ይገኛሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደብብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተሰራጭቶ የነበረው እህል የሚጨርሰው የተምች መንጋ በሌሎች አካባቢዎች የተስፋፋ መሆኑን የወያኔው የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሰሞኑን ገልጿል። በደቡብ አካባቢ 9 አውራጃዎችና እንዲሁም በኦሮሞ አካባቢ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የታየው ይኸው ተምች ከ 10 ሺ ሄክታር በላይ የበቀሉ ሰብሎችን ያበላሸ መሆኑ ተገልጿል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ እየተስፋፋ ከሄደ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከ35 ሺ ሄክታር በላይ በበቀሉ ሰብሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የተገመተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አስፈላጊው መከላከያ እየተወሰደ መሆኑን ገልጿል። ተምቹ በበቆሎ፤ በማሽላ፤ በባቄላ በለውዝና በድንች ምርቶች ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑ ታውቋል።

ፈለገ ዮርዳኖስ በሚል ስም የተቋቋመው ድርጅት ነዋሪዎችን እያስመረረ መሆኑ የዜና ምንጮች ገልጸዋል። ከተቋቋመ ዓመታትን ያስቆጠረውና በወያኔ አባላትና ደጋፊዎች የሚንቀሳቀሰው ይኽው ድርጅት ከዚህ በፊት የበርካታ ዜጎችን መሬት በመቀማት ከፍተኛ ግፍ የፈጸመ ሲሆን ከሰሞኑ ደግሞ ከገነት ሆቴል በታች ያሉትንና በቡልጋሪያ ኤምባሲ አካባቢ የሚገኙትን ነዋሪዎች በሶስት ቀን ውስጥ ከቤታቸው እንዲለቁ ማድረጉ ነዋሪዎችን ያስመረረ መሆኑን የዜና ምንጮች ጠቅሰዋል። ነዋሪዎቹ ተገቢው ካሳ እና ምትክ መሬት ሳይሰጣቸው እንዲለቁ መደረጋቸው አሳዛኝ ነው የሚሉ ዜጎች በሶስት ቀን ገደብ እንዲነሱ መገደዳቸው የግፍ ግፍ ነው ይላሉ።

በዛሬው ቀን እነ አቶ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተባለው ተቋም የድምጽና የምስል ማስረጃዎችን የሚያስተረጉሙ ባለሙያዎችን ሳያቀርብ ቀርቷል። “ ከዛሬ በኋላ ማስረጃው እንዲተረጎም በሚል ቀጠሮ ከተሰጠ፤ እኔ የክርክሩ አካል አልሆንም። ፍርድ ቤቱም ለመቅረብ ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ ይታወቅልኝ” በማለት አቶ በቀለ ገርባ የተናገሩ ሲሆን ዳኞች ለኢብኮ ማስጠንቀያ አዘል ምክር ሰጥተው እስከ ሚያዚያ 18 ቀን የማስረጃዎችን ትርጉም ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብና ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ብይን ለመስጠት ቀጥረዋል።

ከፍኖተ ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ አንድነት ድምጽ ሬዲዮ ዝርዝር ዜና ያዳምጡ