የለውጡ ድግስ፤ የጨረባ ተስካር ሆኖ እንዳይቀር !

በፍኖተ ዴሞክራሲ   የኢትዮጵያ አንድነት ራዲዮ –  ወቅታዊው  የኢትዮጵያ ጉዳይ ከዕለት ወደ ዕለት  እየተባባሰ መሄዱን ፤ እንኳንስ ዜጎቿ፤ መላው ዐለም የተገነዘበው ሀቅ በመሆኑ፤ በዚያ ላይ  ማተኮሩ፤ አሰልች ይሆናል። ውሃ ቅዳ -ውሃ መልስ ከመሆን አያልፍም። በአሁኑ ወቅት፤  ሁለት ተፃራሪ ኃይሎች ተፋጥጠው ቆመዋል። የሞት- ሽረት ውጊያ እያደረጉ ናቸው። አንደኛው ለመሞት፤ ሌላኛው ለሽረት። ዘረኛው አገዛዝ በፃዕረ- ሞት ቃሬዛ ውስጥ ይፈራገጣል። ምልዐተ-ሕዝቡ  ደግሞ፤  የድል  አክሊሉን ለመጎናፀፍ  ይታገላል! ሁለቱም ፤ በማይታረቅ ቅራኔ   ጉድባ ውስጥ ናቸው።  መልዐተ-ሕዝቡ፤ ከጉድባው ወጥቶ የነፃነት ዐየር ሲተነፍስ፤  ወያኔና ተባባሪዎቹ ደግሞ፤ ከገቡበት ጉድባ ሳይወጡ፤ ከኢትዮጵያ መድረ-ገፅ  የሰናበታሉ።

በዚኽም፤ ለአንዴና ለማጨረሻ ጊዜ፤ በዘር ላይ የተመሠረተው ዕኩይና ከፋፋይ ሥርዓት ከምድረ-ኢትዮጵያ ይወገዳል። በብዙሃን ብሄር-ብሄረሰብ የተመሠረተችው ሀገራችን፤ ዕውነተኛውን ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት  ገንብታ ነፃነቷን ታስከብራለች። ጠላቶቿ እየፈሯት፤  ወዳጆቿ እያከበሯት ትኖራለች።

ይኽ  መፈፀሙ፤ ምኞት ሳይሆን፤ የታሪክ ሃቅ ነው።  የኢትዮጵያ ሕዝብ፤  ለዕድሜው፤ ዕድሜ የስጠው እንጅ፤ የመጨረሻው ድል አድራጊ መሆኑ አይቀሬ ነው።  ሆኖም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተባብሮና አምርሮ፤ ካልታገለ፤  የሚፈልገውን ውጤት መስመዝገብ አይችልም።  “ምኞት አበባ ነው፤ መስራት ግን ፍሬ ነው ” እንዲሉ፤ የነፃነት አክሊልን ለመጎናፀፍ ፤ በግድ ተግቶ መሥራትን ይጠይቃል። ሳያቋርጡ መቀጥል፤ ሳይታክቱ መታገል፤ ሳይነጣጠሉ  መተባበር፤  ሳይበታተኑ ኅብረት መፍጠር፤ ከወያኔ ሰላዮች መጠንቀቅ፤ የራስንም ምሥጥር መጠበቅ፤  ተደማምሮ  የድል ውጤትን ያበስራል።

ወያኔዎች፤ ኢትዮጵያን አሁን ከደረሰችበት አጣብቂኝ ደረጃ ለማድርስው፤ ተግተው መስራታቸውን አለመገንዘብ፤ ተላላነት ብቻ ሳይሆን፤ ትጥቅ አስፈችም ነው። የሚቃወሙትን ባላንጣ ማንነት በሚገባ ማወቅና  የራስንም ቁመና በቅጡ መፈተሽ፤ የትግል ሀ ሁ  መሆን ይገባዋል፡፡  በአኩሪም ሆነ፤ በአሳፋሪ ታሪክ ላይ ብቻ እየተኩራሩና እየተፏከቱ  መኖር፤ የታሪክ እስረኛ ከመሆን አያድንም። ታሪክ በሕያውነቱ ሊያገለግል የሚችለው፤ በሁሉም ገፅታው፤ የጋራ ታሪካችን መሆኑን ተቀብለን፤   ለመፃዒው ዕድላችን በጋራ መወስን ስንችል ብቻ ነው።

ወያኔዎች ባመጡብን  መርገምት ቋንቋ፤ ማለትም፡–

እነርሱና እኛ፤ መጤዎችና ተወላጆች፤  ውህዳንና ብዙሃን፤  ዘራፊዎችና ወራሪዎች፤  ጡት ቆራጮችና  ብልት ሰላቢዎች፤  እየተባባልን የጋራ ሀገር ግንብተን አብሮ መኖር ያስቸግረናል። ይኽ ደግሞ የሚጠቅመው፤ የሕዝቡን አንድነትና  የሀገር ቀጣይነትን ለማይፈልጉ ብቻ ነው። ” ያለፈው ቅራና፤ የሚመጣው መጫኛ”  ብሎ ካልታሰበ፤  የታሪክን መጋኛ እያሰነቁ የመጭው ገመምተኛ ሆኖ መቅረት ይሆናል። ብሄር ተኮር አስተሳሰብን እያጎለበቱ መጓዝ፤ ሀገራዊ አመለካከትን እያጫጨ ያጠፋውል። በጋራ ሀገር ሁሉም ዜጋ የጋራ ተጠቃሚ መሆን ካለበት፤ መልኅቁ ፤ ኢትዮጵያውነት ብቻ ነው። አራት ነጥብ!

የተደላደለ ነፃነት የሚገኘው፤ ዴሞክራሲያዊ  ሕገመንግሥት ሲረጋገጥ  ነው።ይኽ ሊሳካ የሚችለው ደግሞ፤ ገደብ-የለሽ ሕዝባዊ ተሳትፎ በተግባር ሲተረጎም  ብቻ  ይሆናል።  ነገር ግን፤ ሁሉም  ዋስትና  የሚያገኘው፤የህግ  ልዕልና ሲረጋገጥ ነው።  ይኽ መሠረታዊ ጉዳይ እስካልተረጋገጠ ድረስ፤  ሀገራችን በሠላም ትኖራለች ማለት ዘበት ነው። ይኽ ደግሞ ወያኔ በሥልጣን እያለ ፤ የምድረባዳ ውልብልቢት ሆኖ ይቀራል እንጅ፤  በተግባር ሊተረጎ አይችልም።  ከእንግዲህ  ወዲህ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በምድረባዳ ውልብልቢት እየኳተነ ፤ በቀቢፀ-ተስፋ  እየጓጓ  መኖር ሰልችቶታል።  የተጫነውን ቀንበር ሰባብሮ  መገላገል አለበት። ሊገልገል የሚችልው ደግሞ፤በራሱ ትግልና ቆራጥ ውሳኔ ብቻ ነው።

ዕፍኝ  ለማይሞሉ ዘረኛ  ሥርዓት  አራማጆች  ሰጥ ለጥ ብሎ መገዛት ፤ የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን፤ ለተተኪው ትውልድ አስነዋሪ  ቅርስ ማውረስ ይሆናል። ይኽ፤  የሀገራችን ሕዝብ ባኅል ሊሆን አይገባውም። ተወደደም ተጠላ፤የወቅቱ ትውልድ፤  የራሱን ችግር አስወግዶ መገላገል ይጠበቅበታል።  የራሱን ዕዳ፤ ተተኪው  ትውልድ እንዲከፍል ሊፈረድበት አይገባም።  የአሁኑ ትውልድ  የታሪክ ዕዳ ከፋይ እንዲሆን  ሊወሰንበት አይችልም።  በታሪክ እስረኛነት ወኅኒ  ቤት ገብቶ ሊማቅቅ የሚችለው ወያኔ ብቻ ነው።  ወያኔ የዘራውን የሚያጭድበትም ወቅት እየመጣ ነው። ይኽ ወቅት፤  በኢትዮጵያ አድማስ እያንዣበበ ይታያል።

በአሁኑ ወቅት፤፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ድል አድራጊነት የተገነዘቡት የወያኔ ደጋፊዎች ባዕዳን ሳይቀሩ፤  ትላንት ወያኔን ሥልጣን ለማውጣት ባድረጉት ደባ “ተፀፅተው” የአዞ ዕምባቸውን እያፈሰሱ  መሆናቸውን ተገንዝበናል።  ስማቸውን  መጥቀሱ፤ ለእነርሱ ክብር ስለሚሆን፤ ያነንን አናደርግም።  ተጨባጩን ወቅታዊ  የሀገራችንን ሁኔታ በዕርግጥ ተገነዝበናል የሚሉ ከሆነ ግን፤ ወያኔን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት፤ ተጨባጭና አሳማኝ ተግባር ማሳየት ይገባቸዋል። የዲፕሎማቲክ አዞ እምባ ማለቀሳችው ግን ማንንም ሊያሳምን አይችልም። ከመጀመሪያውም ቢሆን፤  ሎንዶን ላይ ወያኔን ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ያደረጉት፤ ከራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም አኳያ እንደነበር  ስለምንራዳ፤  ዛሬም  ሆነ  ወደፊት፤   የእንቅስቃሲያቸው  መሠሰረት፤  ያው ዞሮዞሮ፤ ከራሳቸው ጥቅም አንፃር እንደሚሆን እንገነዘባለን።

ያም ሆኖ ግን፤ ከውህዳኑ  የጎሳ መንግሥት ይልቅ፤ መላዋን የኢትዮጵያን ብዙሃን  ሕዝብ ካቀፈ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ መንግሥት ጋር  ስትራተጂያዊ ወዳጅነት  ቢመሰርቱ የባጃቸው ነበር። ይኽንንም በሚገባ አልተረዱትም ማለት አይቻልም።  ይልቁንም፤ ሁኔታውንና ወቅቱን ጠብቀው፤ ፖሊሲያቸውን ቢገለብጡ  አያስገርመንም።

ይኽንን ለማለት ምክንያት አለ።

“ቋሚ ወዳጅ ወይም ቋሚ ጠላት የሚባል ነገር አይኖርም። የሚኖረው ቋሚ ጥቅም ብቻ ነው።”  ብለው ስለሚያምኑ፤ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ፤ ቋሚ ጥቅማቸውን ሊያስጠብቁ የሚችሉት፤ ቋሚ ከሆነው ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ብቻ ነው።

ይኽም በበኩሉ የራሱ ምክንያት አለው።   በመሠረቱ፤ ኢትዮጵያን ለሚያፈቅሯት ሁሉ፤ ስትራተጃዊ ወዳጅ ለመሆን የሚያስችላት ጠንካራ  ቁመና ያላት ሀገር በመሆኗ ነው።  በጠንካራ ቁመና ላይ  የተመሠረተ ማንነቷን  ገለጭ የሆኑትም፤ የሚከተሉት ኩነቶች ናቸው።

1ኛ.  በመልከ- ዐምድር አቀማመጧ፤ እጅግ ጠቃሚና ወሳኝ፤ ስትራተጂያዊ  ጉዳዮችን  ተቆጣጣሪና  ብቸኛ ባለቤት መሆኗ፤ ተፈላጊነቷ፤ ዕንግዳ ደራሽ ሳይሆን፤ ዘመን ተሻጋሪ ነው፡፡

የቀይ ባህር፤ የሕንድ ውቅያኖስ፤ የባብኤል መንደብ፤ የአፍሪካ ቀንድ፤ የዐባይ ወንዝ ምንጭ መፍለቂያ  መሆኗ፤ ተፈላጊነቷ በዘመንና ትውልድ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። ታዲያ ኢትዮጵያን በወዳጅነት ካልቀረቧት በስተቀር፤ የሚኖራቸው ምርጫ፤ ኢትዮጵያን አዳክሞ፤ የነርሱ ተጠማኝና ደሃ ሆና እንድትቀር ማድረግ ነው። ይኽንንም ዛሬ በወያኔ አገልጋይነት  ተረክበውታል። አግኝተውታል።  ይኽ ሁኔታ ግን፤ ተወደደም  ተጠላ፤  መለወጡ አይቀርም። ኢትዮጵያውያን ጀግኖች፤ አሸለቡ እንጅ አላንቀላፉም።እሳቱም ተዳፈነ እንጅ፤ አልጠፋም። ሀገራችን ፤ ዐይነ ስውራን የሚኖሩባት ምድር አይደለችም። ስትራተጂያዊ ዕይታ ያለቸው ዜጎቿ፤ ከገባችበት ዳፍንት ያወጧታል!

2ኛ. ወደ መቶ ሚሊዮን የሚገመቱት ዜጎቿ፤  በሕዝብ ብዛት፤ በአፍሪካ አህጉር በሦስተኛ  ደረጃ ያስቀምጣታል።የቁጥሩ ብዛት ብቻ ሳይሆን፤ ረዥምና አኩሪ ታሪክ ፤ የበለፀገና  አስከባሪ ባኅል፤ በጎራማይሌ ውበት ያሸበረቀ  ትውልድ፤  የታላላቅ ሃይማኖቶች አስተናጋጅ መሆኗ፤ በራሷ ፊደልና  ቋንቋ በግሏ ሥልጣኔ  የምትተማመን  መሆኗ፤ ከኮሎኒያሊስቶች ወረራ ራሷን ጠብቃ መቆየቷ፤ የጥቁር ሕዝቦች መልካም ተምሰሌትና ምስክር መሆኗ ተደማምሮ ፤ሀገራችንን ከምዕራብያን ዕይታ ውጭ ሳያደርጋት ቆይቷል። ወደ ፊትም ቢሆን በቀላሉ አይተዋትም። ለነርሱ ጥቅም አስጠባቂ የሆኑ አገልጋዮች እያዘጋጁ  ይቆጣጠሯታል። ዛሬ፤ የሕዝቡን አምርሮ መነሳት በመገንዘብ፤ ወያኔን በሌላ ፈረስ ለመለወጥ ዝግጅቱ ቀጥሏል።  በቅደም -ተከተል ተራ የሚጠብቁ ጥቅመኞች አሰፍስፈው ቆመዋል።

3ኛ. የተቀዋሚ ጎራ የሚባለውም፤ የሚንዥብበውን ዐደጋ በቅጡ የተረዳ አልመሰለም። ቢረዳማ ኖሮ፤ ሠነድ ከማዘጋጀት ያለፈ፤ በተጨባጭ ተግባር ላይ ሊረባረብ  በተገባው  ነበር። ያ ሳይሆን፤ በሀገር ቤትና በየአህጉሩ የሚገኘው፤  ለውጥ ፈላጊው ክፍል፤ በየፊናውና  በየግሉ ሠነድ በማዘጋጀትና ስብሰባ በመጠራራት ላይ ብቻ ይረባረባል።  የተቃዋሚው ክፍልና ወያኔን ተፃርሮ የቀመው ኢትዮጵያዊ ምኁር ሠነድ በማዘጋጀት በኩል ክብረ-ወሰን  ተጎናፅፈዋል ቢባል የምፀት  አነጋገር  ነው  አይባልም። በሠነድ ምልዕነት ቢሆንማ ኖሮ፤  የእንግሊዞቹን  ማግና ካርታ  (Magna Karta)  የመሰለ ሠነድ እንደሌለ፤ የብዙዎቹ ዕምነት ነው፡፡ ለሽግግር ወቅት የሚሆን ሠነድ አስቀድሞ  የማዘጋጀቱ አስፈላጊነት አከራካሪ ባይሆንም፤ ብሄር – ተኮር  ከመሆን አልፎ ፤ ወደ ሀገራዊ  አንድነት ደረጃ ካልተሸጋገረ፤ መላውን የሀገሪቱን ዜጎች ድጋፍ ለማግኘት ቁመና አይኖረውም።

4ኛ.  በርከት ያሉት ተቃዋሚ ኃይሎች ለአገራቸው የሚቆረቆሩ ቢሆን ኖሮ ፤ ለአለፉት 27 ዐመታት ፣ አያሌ ተጨባጭ ተግባራት ማከናውን በቻሉ ነበር።  በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ትግል መሪ አልባ- ሆኖ፤ በራሱ በግሉ እንቅስቃሴ፤ ወያኔን እያርበተበተ በመምጣቱ፤ሁሉም ከየማጀቱ በመውጣት፤  እኔ አለሁ ፤ እኔን አትርሱኝ  በማለት ይደመጣል  ።  በዕርግጥ ሁሉም በየፊናው መንቀሳቀሱ ባልከፋ ነበር።  በየፊናው የመንቀሳቀሱ ሂደት ግን በአንድ ማዕከላዊ ምዕራፍ ካልተካተተ ፤ የሚሰማው ድምፅ ፤ የጨረባ ተስካር ለማውጣት  ያለፈ ጫጫታ ከመሆን አያልፍም።  እስከ ዛሬ ድረስ የሕዝቡ ትግል፤ እየፈጩ ጥሬ፤ እየጋገሩ ሊጥ፤ እየሰበሰቡ ሿ-ብትን፤ ሆኖ የቀረውም፤ ማዕከላዊ  ዕዝ፤ ቁጥጥርና ክትትል የሌለው በመሆኑ ነው። የአሁኑ ሕዝባዊ ዐመፅም ይኽን  ሁሉ አሟልቶ አግኝቷል ማለት የሚቻል አይደለም። ሁሉም በየፊናው ግን፤ እኔ ነኝ የምመራው እያለ በብዥታ ውስጥ ይዳክራል ። ሕዝባዊው  አመፅ ግን ማንም ሁነኛ መሪ እንደሌለው፤ አመፁን የሚያካሂደው እራሱ በባለቤቱ ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሳምሮ ያውቀዋል።

የሎንዶን ዳግም – ምፅዓት አምሳያ ጉባዔ እየተቀረበ መምጣቱን ያሸተቱት ቡድኖች ፤ የቅድመ- ስብስባ ዝግጅት በማድረግ እየተሯሯጡ ይገኛሉ። ከመጣደፋቸው የተነሳ፤ ሁሉን ያካተተ ፤ ያቀፈ፤ ማንንም ያላገለለ፤ ሰፊ መሰናዶውን ወደ ጎን   በመተው ፤ “የጥሎ- ማለፍ  ” ጨዋታ እሽቅድድምን መርጠዋል  ። ይኽ ደግሞ ፤ ለዘላቂ ሠላምና መረጋጋት አይጠቅምም ። እንዲያውም ፤ ለሌላ አዲስ ቀውስ  በር -ከፋች ይሆናል ። ሀገሪቱ ደግሞ ፤ አዲስ  ግርግር  ፈጣሪ  ሁኔታ አያስፈልጋትም ። ” የገበያ ግርገር ፤ለሌባ  ስለሚመቸው  ”      ሁሉን አሳታፊ የሽግግር  ሂደት እንዲመጣ የማይፈልጉ ቀውስ -ፈጣሪዎች  ግን ይፈልጉታል ። ምክንያቱም፤ የቅድሚያ ምኞታቸው በአቋራጭ ሥልጣን መያዝ በመሆኑ ነው።ይኽች የፈረደባትን  የምንሊክን ግቢ ሥልጥን ኮረቻ ለመቆናጠጠ፤ ሁሉም በማቋመጥ ላይ እንደሆነ፤ከአደባባይ ምሥጥር በላይ ሆኗል።

ወያኔ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቆሌው እየተገፈፈ  በመምጣቱ፤  እርሱን ለመተካት፤ የተውሰኑ ቡድኖች ፤ “የሽብራ ግርፍ ” ውሽልሽል ጎጆ ቀልሰው ፤  አስመሳይ ኅብረት  መፈጠርን ይመኛሉ። ሀገሪቱ ከወያኔ በኋላ፤ መፍረሷ አይቀርም  የሚል ትዕንቢት አንግበው፤ ጭንቀት- ወለድ አማራጮችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይመኛሉ።

ሀ.  ወታደሩ፤ መፈንቅለ – መንግሥት አድርጎ ሥልጣን መያዝ አለበት!
ለ.   አንድ ሀገር ወዳድ ሰው / ቡድን  ስብዓዊነትን የተላበሰ  አባገነን / Benevolent Despot   በአስቸኳይ ይምጣ!
ሐ.   የምዕራባውያኑን አፅድቆት  ያገኘ  ጊዚያዊ አስተዳደር  ይቋቋም!
መ.   የአደራ መንግሥት  የሚባለውን፤ እስቲ ደግሞ  እንሞክረው  !
ሰ.   የስደት መንግሥት  ማቋቋሙ  ምናልበት ይበጀን ይሆን?

የአማራጮቹ ዝርዝር ረዥም ሊሆን ይችላል  ።ተደገግመው የሚሰሙት ግን በዋናነት እንኝሁ ይመስላሉ። ሁሉም ቢጠራቀሙ ግን፤ የሀገሪቱን ስትራተጂያዊና መሠረታዊ  መፍተሄን ሊያመጡ አይችሉም። ከጭንቀትና ጥበት የመነጩ መሆናቸውን መገንዘብ ቢቻልም፤ በእኛ  ፅንዑ  ዕምነት ፤ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ ኢትዮጵያ  በግርግር አትፈርስም ፤ ሕዝቦቿም  ሽህ ዘመናትን  ባስቆጠረ አብሮነት፤ አብረው የኖሩ ስለሆነ በቀላሉ ሊበጥጠስ በማይችል በብዙ ጠንካራ  ድርና ማግ ትስስሮች/ ቆርኝቶች የተዋሃዱ ናቸው ። አንድነታቸው፤  በወያኔ ሳል ደንግጦ የሚፈራርስ አይሆንም። አፍራሾቿ ይፈራርሳሉ እንጅ፤ ኢትዮጵያስ አትፈርስም ! ይኽ ዕምነት የመላው ሕዝቦቿ ዕምነት ነው!

የወቅቱ ጥያቄ፤ ታዲያ አሁን ምን ይደረግ ?  ነው።  በብዙሃኑ   ዕምነት፤ የሚከተሉት ኩነቶች ባስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆኑ ይፈለጋል።

1ኛ. ሁሉን ያካተተና የጋራ ተጠቃሚ የሆነው ሁሉ የኅብረት ጉባዔ መጠራት አለበት !
2ኛ. ለሽግግር ሂደት  የሚጠቅም ሀገራዊ   ሠነድ ላይ  ተስማምቶ በጋራ መስራት አለበት !
3ኛ.  የሕዝቡ ዐመፅ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ። ለዚህ ጥንካሬ ሁለት ተጨማሪ እንቅስቃሴዎች ወገንተኝነትን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል። እነርሱ፡

ሀ. መለዮ ለባሹ፤ ከሕዝብ ወገን መቆም እንዳለበት ታሪካዊ ግዳጁ መሆኑን ሊያውቀው ይገባል ።  አፈሙዙን፤ ማዞር ያለበት ወደ ወደ ሕዝቡ ሳይሆን፤ የሕዝብ ጠላት በሁኑት በወያኔዎቹ መሆኑን ማወቅ ግዴታው ነው።  አኩሪ ታሪክ ሰርቶ ማለፍ እንጅ፤  ወንጀል ፈጽሞ መገኘት፤ በታሪክም ፤በትውልድም፤  በህግም የሚያስጠይቅ እንደሆነ አስቅድሞ ሊገነዘበው ይገባል።

ለ .  መላው የአዲስ አበባ ነዋሪ ሕዝብ፤ ከቀሪው የሀገሪቱ ሕዝብ ትግል ጋር መተባበር ይጠበቅበታል ። የክፍላተ- ሀገር  ሕዝብ በሚያደርገው  ዐመፅ  አብሮ መቆም አለበት። እስካሁን ያንን ሲያደርግ አልታየም።  የሚጠበቅበትን ሚና መጫወቱን ፤ አላስመዘገበም።  የመላው የአዲስ አበባ ሕዝብ ሆ ! ብሎ ከዳር እስከዳር ከተነሳ፤ ወያኔዎቹን ለማርበትበት፤ የማይናቅ ቁመና አለው።  ለዚኽም ታሪካዊ ማጣቀሻ አለ ።   በአስራ ዘጠኝ  መቶ ስድሳ ስድስት/ 1966 ዓም  ሕዝባዊ ዐመፅ፤ የአዲስ አበባ ሕዝብ ያደረገው   የ4 ቀን ሥራ ማቆም አድማ፤ የነበረውን አገዛዝ ሊያፈርሰው ችሏል። ይኽ አመፅ ታሪካዊ ነበር። ዳግማዊ   ታሪክ መስራት የባለ ታሪኮች ተግባር ነው።

ሐ.  የኦሮሞና የ ዐማራን የህብረት ትግል  ለማደናቀፍ ወያኔ የሚያደርገውን ትንኮል ነቅቶ በመጠበቅ ማክሸፍ ፤ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው።

የተቀጣጠለው የሕብረት ትግል አይቆምም! የለውጡ  መሰናዶ እንቅስቃሴ የጨረባ ተስካር አይሆንም!

ኢትዮጵያ  ለዘለዓለም  ትኖራለች!

 

pdf_print