ዳኛውማ የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝብ ነው (ክፍል ሁለት)

ኢያሱ ዓለማየሁ (ኢሕአፓ) –

ቀና ብሎ ሚገኝ ብርቅ እንጂ ነው ክብር፣

ተጎንብሶ ሚገኝ የወደቀ ነገር፤ የረከሰ ነገር። ጸጋዬ ገብረ መድህን ደብተራው (በኢሕአፓ ነጻ ሜዳ) በክፍል አንድ ለታደለች ኃይለሚካኤልና መላኩ ተገኝ (ሟቾች) በኢህ አፓ ላይ ላሰራጩት ሀሰትና ክስ ምላሽ ለመስጠት ሞክሬያለሁ። በኢሕአፓ ሲዘመትና ስንመልስ፣ ስመልስ የመጀመሪያችን አይደለም–የረጅም የትግሉ ውጣ ውረድ ተመክሮአችን ነው። በደጉ ዘመን ለመኢሶንም ለሌሎችም ምላሽ ሰጪ፤ መላኩ ራሱ አንዱ እንደነበር ትዝ ሲለኝ ዝቅጠት ሲመጣ ምን ያህል አዋራጅና አጥፊ እንደሚሆን እንደገና መገንዘብ የግድ ሆኗል።

በተያያዘ ግን እንደገና መነሳት ያለበት ዋና ጥያቄ ለምን በኢሕአፓ ላይ ዘመቻው አላቋርጥ አለ የሚለው ነው። ያው እንደሚጠበቀው የአጼው ስርዓት ናፋቂዎች ሁሉ ስርዓታችንየሚሉትን ተራማጁ ወጣት ለሽንፈት ስለዳረገው በኢሕአፓ ላይ ጥላቻ አላቸው። አሁንም ወንጀላቸውን ያልተረዱና ያላወራረዱ ደርጎችና የደርግ ርዝራዦች ዛሬም ለድርጅቱ ውድቀትና ጥፋትን ይመኙለታል። ኢሕአፓ አባቴን፤ወንድሜን ዘመዴን ገደለብኝ ብለው ቂም የያዙም አሉ። ሁሉም የራሳቸውን ጸያፍ ሚናና ታሪክ ማስታወስ ፈላጊዎች አይደሉም። ገንጣዮችና ጠባቦች በሞላ ኢሕአፓ ስለታገላቸውና ሀገር ስለጠበቀ አሁንም ሊያጠፉት ተፍጨርጫሪ ናቸው። የሀገር ሉዓላዊነትን ሲዳፈሩ ድርጅቱ አሌ ብሎ የታገላቸው ሁሉም–የቅርቦቹም የሩቆቹም አይወዱትም። የአሜሪካን የረጅም ዓመታት ቂምና የአረቦችን ጥላቻ ያጤኗል። ወያኔ ከ27 ዓመታት በላይ ኢሕአፓን ጠላት ብሎ ወግቶታል፤ ዛሬምቅጥረኞቹን አሰማርቶበት አለ፤ የስብሃት ነጋና ስዩም መስፍን ዓይን ያወጣ ጸረ ኢሕ አፓ ቅጥፈት ምስክር ነው። በአጭሩ ግን የኢትዮጵያ የቆዩም አዲሶችም ጠላቶች ጸረ ኢሕአፓ ናቸው። ከዚህ አንጻር የብዙ መጻሕፍት መቸክቸክ በደፈናው አዎንታዊ ሊባል የሚችል ቢመስልም አልሆን ብሏል። በበኩሌ ከ500 ገጾች በላይ ስለራሳቸው ጀብዱ ብለው ይሚቸከችኩት ይገርሙኛል። የረባ ስምሪት በሆነና መንፈሳዊ ቅናት ይዞን ቢሆንመልካም በነበረ። መደመር፤ ትውልድ እንዳይረሳ፤ አንጃ ወ ክሊኩ፤ የኢሕአፓ እንቆቅልሽ፤ ምስክርነት፤ አማራ ከየት ወደየት፤ የነጻነት ጎሕ፤ የደም ዘመን፤ ነበረ፤ የኢሕ አሠ ታሪክ፤ ማነው ዳኛው፤ ወዘተ… ወዘተ… መጽሃፍት ወረቀት ከመጨረስ ሌላ ለህዝብ ምንም ፋይዳ የላቸውም። ዋናው ችግራቸው ሀሰትን ይዘው ሚሸናከሉ መሆናቸው ነው። አዲሱን ትውልድ ሀቁን አይነግሩትም፤ስለራሳቸው ሞነጨሩ ሞነጫጨሩ እንጂ ለወጣቱየሚጠቅም መልዕከት የላቸውም። አንድ ሰው ዕድሜውም ሳይገፋና ምንም ታሪካዊ ስራ ሳያከናውን እንዴትስ የህይወት ታሪኬ ብሎ ከ 500 ገጽ በላይ ይከትባል ? በትግሉ ሂደት በስራ ብዙ የሀገር መሪዎችን አግኝቼ ነበር… ወዘተ ብዬ ብቸከችክ ከጉራ ውጪ ምን ሊጠቅም? ታዲያ ምን ይሁን ? ለዛሬው ወጣትና ትውልድ ሀቁ ተተርኮለት ለመጣበት ትግል በዕውቀትም እንዲታጠቅ ማድረግ እንጂ በትምህርት እሳት ነበርኩ፤ ሳድግ ጫማ አልነበረኝም ነበር ትረካን ምን ልዩ ያደርገዋል? ምንስ ነው ጥቅሙ?

ከዚህ በተያያዘ ደግሞ ጋዜጠኛ ናቸው የሚባሉት ጉዶች (ሟቾቹን በቅርቡ ቃለ መጠይቃ ያቀረቡላቸውን ሁለት ግለሰቦች በተለይ ይመለክታል) ስለሚጠይቋቸው ግለሰቦች ዘርህ ዘርሽ ማነው ከማለት አልፈው (በሽፍንፍን እርሶን ማን ልበል የሚለው ጥያቄ) ስለግለሰቦቹም በበቂ ታሪካቸውን አያውቁም። ሴትየዋ ወያኔነቷን ለሀገር አግልግያለሁ በሚል ሽፋን ልታልፈው ስትሞክር በዝምታ ያለፏት ሲሆን ሌላው ጠያቂ ሟቹን ሰውየ (መላኩ ተገኝ)ደግሞ የጠየቀው ስለ ወያኔ ደጋፊነቱና አገልጋይነቱ ሳይሆንሰውየው ያልነበረበትን በለሳን ጠርቶ በሠራዊት እዚያ ነበርክ ብሎታል። ሰውየውም የትጥቅ ትግሉን እናቁም ባይ መሆኑን ከቶም ሳያነሳ በለሳ ነበርክ ሲባል አልነበርኩም ብሎ ሀቁን ለመናገር አልደፈረም። ያልሆነን ነበረ፣ ነበርን ማለት የዘንድሮ ቀጣፊዎች ዋና መለያ ሆኗል። ኮለኔሉ ሲገበዝና የማያውቀውን አወቅኩ ሲልም ታዝበናልና ውሸት በገነነበት ስርዓትና አገዛዝ የፖለቲካው መድረክ በቀጣፊዎች ቢጣበብ የሚገርም አይሆንም። በዚህ አንጻር ሟቹ ሰውየ ስለ ኢሕአፓ ታሪክ መጻፍ ጉዳይ ቁም ንገር ሊባል የሚችል መናገሩን መካድ አይቻልም። ለምን የድርጅቱን ታሪክ አትጽፉም ባዮች ብዙ ናቸው። መጻፉ አልከበደም ግን ሀቁን መጻፍ እንደ መተርተሩ የሚቀልም አይደለም። ድርጅቱ አሁንም በትግል ላይ ስላለም ታሪክ ብሎ መገለጥ የሌለበትን አስፍሮ ራሱን ሊጎዳም መጠበቅ የለበትም–“ምስጢር የባቄላ ወፍጮ አይደለም” የሚለው ዛሬም አክብሩኝ ይላል። የኢሕአፓ ታሪክ ሰፊና የዳጎሰ ነውናም አንድ ወይ የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ የሚጽፉትም አይደል። ሀቁ ግን አሁንም እየታገሉ ባሉት የኢሕአፓ ልጆች እጅ እንጂ ድርጅቱን ከራቁ 30 አርባ ዓመት ባሳለፉ አንጃዎችና ከሀዲዎች እጅ አይደለም። አሲምባ ከተደረገው ትግል በበለጠ ሰፊ ትግል የተደረገው ሠራዊቱ ወደ ጎንደርና ጎጃም ከገባ በኋላ መሆኑን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል–በስፋትም በይዘትም። ይህ እንዳለ ሆኖም ታሪክን ለማስከበር በየጊዜው ስንጥር ዘመን አሳልፈናል። ነበር፣ ምስክርነት ወዘተ ብለው ሀሰት ላሳፈሩት፤ ዕንቆቅልሽ፣ የደም ዘመን ወዘተ.. ብለው የፈጠራ ጽሁፍን ላቀረቡት ምላሽ ሰጥተናቸዋል። አማራ ክየት ወደየት ላሉትም ገና ያኔ አማራ መሆን ፋሽን ባልሆነበት ጊዜ ምላሽ ሰጥተናል። ለወያኔ አሳን ወደ ተራራ፤ ከድጡ ወደ ማጡ፤ ከማጡ መስመጡ ወዘተ… በሚሉ ጽሁፎች ጥበታቸውንናጸረ ኢትዮጵያ መሆናቸውን ተችተን ብዙ ጽፈናል፤ አሉታዊ ሚናቸውን በጽሁፍም፣ በፍኖተ ራዲዮም አጋልጠን እርቃናቸውን ስናወጣ የዋሹትንም በዚያው ዜሮ አድርገነዋል። የሰማዕት ጓዶች ታሪክን ለመዘከርና ለማስከበር ይኸውም ዛሬም ውሸታሞቹን ሟቾች ቀጣፊዎች እያልናቸው ነው።

ስለ ኢሕአፓ ማንም አይጻፍ ባዮች ናቸው ይሉናል። በበኩሌ የዘንድሮ ወጣቶች እንደሚሉት የሚመቸኝ አነጋገር ነው–የማያውቁ፤ በድርጅቱም የትግል ታሪክ ብልጭ ድርግም ያሉ፤ ሊጽፉ ባይሞክሩ ደግ ነው። የማያውቁት ወይም ከድርጅቱ ከተለያዩት 40 ዓመት እያለፋቸው የድርጅቱን ወሳኝ ታሪክ ጻፍን ባይሉ በሚገባ የሚሻል ነው። ፍቅር ያሳብዳል ቢባልም በዚያው ልክ የዘንድሮ ፍቅር ሳይጀምሩት ያልቃል፤ ግለቱ የታጠበ መሀረብም አያደርቅም ተብሏል። የጌታቸውና ብርሃነ መስቀል ሚስቶች ለባሎቻቸው ያላቸውን ፍቅር በመጽሐፍ መልክ መግለጣቸው እንዳለ ሆኖ በዚህ አስታከው ታሪካችንን ሲክዱ፤ ሲያዛቡና በተለይም ውድ ህይወታቸውን ለትግል የሰዉትን ጓዶቻችንን ሲዘልፉ በዝምታ ልናልፍ ከቶም አንችልም። ሟቾቹ በየምክንያታቸው የብርሃነ መስቀል አምላኪዎች ናቸው። ውድ ሕይወትን መሰዋት ቀላል እንዳልሆነ ንገሩን ባይሉ ይመረጣል። ከዚህ አያይዛ ሴትየዋ ድርጅቱንበማይሆን መንገድ ከሳለች። ክሊኩ ለአባላት መርዝ (ሳያናይድ) እያደለ ሲያስገድል እርሱ ግን በዚህ አልተጠቀመም ብላለች። ያሳዝናል። በቂ ሳይናይድ ክኒን ኖሮን በነበረን ለሁሉም ታድሎ፤ ለነኢንጂነር አስማን፤ ማርቆስ ሐጎስ፤ተስፋዬ ደበሳይ፤ዮሴፍ አዳነ፤ ፍቅሬ ዘርጋው…ወዘተ… ተሰጥቷቸው በነበር ለአሰቃቂ ግብረ ስየልና አስከፊ ሞት ባልተዳረጉም ነበር። እሷ ባታውቀውም መርዝ ክኒን የሚሰጥበትም መመዘኛ ነበር። የሟቿ ባል እንደ ፊዴል ካስትሮ ተይዞ ታሪክ ነጻ ያወጣኛል (ሂስትሪ ዊል አብሶልቭ ሚ)ብሎ በፍርድ ቤት ለፍፎ ታሪክ ሲሰራና ህዝብ ተሰልፎ ሲያስፈታው ባይታየው (ባይቃዥ) ኖሮ፤ ደፋር ቢሆን ኖሮ ሳይናይድ ክኒኑን ውጦ ራሱን ሰውቶ በተስፋዬ ወልደሥላሴ ነፍሰ ገዳዮች ታንቆም ሊገደል ባልበቃ ነበር። ሳያናይድ መዋጥ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን መርዝ ለሌሎች ጓዶች ሰጥተውና ከሥቃይ ገላግለዋቸው እነሱ ግን ስየል ተቀብለው የተሰዉ ጓዶቻችንን ስትዘልፍ ተሳቀን፤ ባለጌ፣ ህሊና ቢስ ወያኔ ብንላት ሲያንሳት ነው። ደግሞ የማታውቀውን ዘሩን እንተውና ያስተማራትን ተስፋዪ ደበሳይን ለመዝለፍ ምንም የሞራል ብቃትና ማጠየቂያም አልነበራትም። ከመሞቱ በፊት ብርሃነ መስቀልን ሊያገኝ ፈልጎ ነበር፤ አቅዋም ቀይሮ ነበር በሚል ስለ ተስፋዬ ልታቀርብ የሞክረችውም አጥንቱ ይውጋትና ውሸቷን ነው። ብርሃነ መስቀል ለእኔ ላከው ያለችውን ደብዳቤ በተመለከተ በአጠቃላይ ሁኔታው ላይ ተነጋግረን ተስፋዬ ወደ አሲምባ እለፍ እኔም መጣሁ ባለው መሠረት ከሱዳን ወደ አሲምባ አልፌ ስጠብቀው የተሰዋ ቢሆንም በአንጃዎች ላይ ድርጅቱ የነበረውን አቅዋም ሙሉ በሙሉ ይደግፍ እንደነበር አውቃለሁ። ስታስበውስ ክሊክም አንጃም መሆን እንዴት ይገጥማል?

ለመቀጠል፤

ታደለች ወደ አዲስ አበባ እንደገባች በጻፈችልኝ ሁለት ደብዳቤዎች የተቸችልኝ ጉዳይ አንዱ የብርሃነ መስቀል ተክለሰውነት ያለችውን ሲሆን ሁለተኛው ደግም በሰሜን አሜሪካ ያሉ ጓዶች የስታሊንና ማኦ አዳናቂ የሆኑትን ተቃውማ ነበር። ይህን ደብዳቤዋን ለማዕከላዊ ኮሚቴን ጓዶች አስተላልፊያለሁ። ከዚያ ቀጥላ ደግም የጻፈችው ደብዳቤ ግልብጥ ብሎ የባሏን አቅዋም የሚያስተጋባ ሆኖ ሳገኘው ይህንንም ለአመራሩ ልኬ ምን ሆነች ስል ተስፋዬ የሰጠኝ መልስ፤ ክፍሉ ታደሰ በአዲስ አበባ በህቡዕ ከነበረው ባሏ ጋር አሳዘነኝ ብሎ እንድትገናኝ እንዳደረጋትና ባሏ እንደቀየራትም ነው፤ ወይም አቅዋም እንደቀየረች ነው። ከዚያ በኋላ በእሷና በእኔ በኩል የነበረው ግንኙነት አመቺ ባለመሆኑ ሲቋረጥ ለመጨረሻ ግን ብርሃነ መስቀል የጻፈልኝን ደብዳቤ ወደ ፈረንሳይ በምትበር የአየር መንገዱ አስተናጋጅ በኩል ልካልኛለች–ቀለጠ አለች እንጂ በአምጪዋ በኩል መልሴን ልኬያለሁ። ባለቤቱ እንደጻፈችው ክሊክ የሚላቸውን (ተስፋዬን፤ ክፍሉና ዘሩን) የሚከስ ነበር። ዋናው መልዕክቱ ከደርግ ጋር ተባብረን መስራት አለብን የሚል ሲሆን (በወያኔ ጊዜ ብቅ እንዳለው አንጃተበላን ይላል) ዋናው አጽንኦቱ በከተማ ጥይት መተኮስ ላይ ሳይሆን (“ተራማጅ መንግሥት ላይ ጥይት መተኮስ በርግጥም ስህተት ነው” ማለቱ ይታወሰኛል”) ከዋና ጸሃፊ ቦታው አለአግባብ መውረዱ ላይ ነበር። አንተም ጉባኤ የፖለቲካ ቢሮ አባል ብሎ መድቦህ በኮንፈረንስ ሊያነሱህ አይችሉም ካለም በኋላ ጉባኤ እንዲጠራና እስከዚያውም በዋና ጸሃፊ ቦታው እንዲቀጥል እንድጠይቅና እንድተባብረውና ጉባኤም እንዲጠራ እንድሰራ ጠይቆኛል። ከሠራዊቱ ከድተው ወደ ደርግ እጅ የሰጡት ሰባቶቹ ላይ ውግዘትና ሌላም እርምጃ እንዲወሰድ የፈለገውን አመራሩ ጉዳዩን መርምሮ እምቢ በማለቱና የሠራዊቱን አባሎችም አይመለስብን ባሉት መሠረት ወደሜዳ እንዳይመለስ መደረጉና በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ይቀጥል ቢባልም ጸሃፊም ፖሊት ቢሮም አባል አለመሆኑ እንዳስቆጣው ግልጽ ነው። ሟቹ ሰውዬ (መላኩ ተገኝ) ብርሃነ ላይ ይህ ውሳኔ መወሰዱ ስህተት ነበር፤ ወደ መነጠልም ገፋፍቶታል ሲል ግለሰብ ከብዙሃን የድርጅት ውሳኔ በላይ ነው ሲል አስረግጧል። የብርሃነ ሎሌ መሆኑንም ሳይወድ አረጋግጧል ማለት ይቻላል። በመሥራች ጉባኤ የተገፋውና ሁላችንም ተስማምተን ዋና ጸሃፊ የሚል ሥልጣን እንዲኖር መደረጉ ስህተትና ጥፋት መሆኑ በተጨባጭ በተግባር ስለታየም የዋና ጸሀፊ ው ቦታ በአመራሩ /ኮንፈረንሱ ተሰርዟል። በሰራዊቱ የነበሩትበርካታ ጓዶች የብርሃነ ጠባይና አሰራር ጸረ ዴሞክራሲና ስታሊናዊ ነው ሲሉ መመስከራቸውም የሚካድ አይደለም። ይህን ዝንባሌ ቀደም ብለን አይተን ወደ ስልጠናና ሠራዊት ምደባ ሲወሰን እኒና ብንያም እሱን ልትቆጣጠሩት ትችላላችሁ ብለው መድበውን ብንያም በመንገድ በበረሃ ሲሰዋ እኔም ወደ መከካለኛ ምሥራቅ ስራ ተሰጥቶኝ ስቀር የታሰበው ሳይሆን ቀርቶ ጓዶችን የሚንቀው ብርሃነ ሊፈነጭ ችሎ የጓዶችን ተቃውሞ ማትረፉን ዛሬም በህይወት ያሉ የኢሕአሠ የያኔ አባላት ይመስክራሉ። ያኔ በሜዳ ገና ስላልነበርኩ የተባለውን አቀርባለሁ እንጂ ነበርኩ ባይ ምስክር አይደለሁም። ለደብዳቤው ግን በላኩት መልስ እስከመጪው ጉባኤ እንዲታገስና የግል እርምጃ እንዳይወስድ (“አንተንም ድርጅቱንም የሚጎዳ”) የሚል ማሳሰቢያን ያዘለ ሲሆን ከሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ መነሳቴንም እንደምደግፍ ገልጬለታለሁ። የደብዳቤውን ቅጅ በነበርኩበት አስቀምጬ ወደ ሜዳ አመራሩ ጋ ወስጄው ሁሉም የአንጃውን ግልጽ አቅዋም ሊያነቡት ችለዋል-36 ገጽ ሙሉ አቅዋም ማብራሪያ ነበርና። ዛሬ ዋናውተቃውሟችን በከተማ ተኩስ የሚለውን /የሚመለከት ነበር ብለው ሊመጻደቁ የሚሞክሩት ያዋጣናል ያሉት የኋላ መብራት አንጂ መሠረታዊ ልዩነቱ ከደርግ ጋር እንደ መኢሶን ሆነን እንስራ ወይስ በተቃውሞ ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት ብለን እንቀጥል በሚለው ላይ ነው። ሽፍንፍንና ውሸት ለምን አስፈለገ?


ጊዜ ሲያስጠፉን እንጂ ይህ ሁሉ መነገሩ እምብዛም ለአዲሱ ትውልድ ወሳኝ ትምህርት ባልሆነም ነበር። ከዚያ ወቅት ትግል ጠቃሚው ተመክሮ ለትግል የተወሰደ የመደራጀት ጥረትና (ስልቱ፤ ራስ አነሳሽነቱ፤ ወኔውና ቆራጥነቱ ወዘተ) በተለይም ጊዜያዊ ህዝባዊ መንግሥት አማራጭና አታጋይ መፈክርነቱ ነው። ይህ መፈክር–ለመጀመሪያ ጊዜ (ልክ እንደ ሙት ከተማ የትግል ስልት) በኢሕ አፓ የተነሳ ሲሆን እውን ሆኖ ኖሮ ቢሆን ሀገራችን ከዓመታት ስቃይና ሰቆቃ ትድን እንደንበር ምንም ጥርጥር የለውም። ዛሬም ከዘረኞች የቄሮ ግፍና ውጥንቅጥ በወጣን ነበር በጊዜ። ከዚህ አማራጭ ባሻገርም የህብረት ግንባር አማራጭን ከደርግ ጋር ተመሳጥረው ባቀረቡም ጊዜ ኢሕ አፓ ህብረት ለምን ተነስቶ የሚል ምላሽ ሰጠ የሚሉትም እንዲሁ ቅጥፈት እንደሆነ ይታወቃል። ዴሞክራሲ ይረጋገጥ፤ በህብረቱ ሁሉም ሀይሎች ይጠሩ ይሳተፉ ወዘተ ብለን መሆን ያለበትን ሂደት አብራርተን በአዎንታዊ አቀረብን እንጂ (የወቅቱ የዴሞክራሲያ ህትመት ላይ ሰፍሮ አለ) ህብረት አንፈልግም እምቢኝ አላልንም። ወደ ከተማ የራስ መከላከል እርምጃም ስንገባ (በወቅቱ ስራ አስኪያጅ ኮሚቴው ባወጣው ጦርነት ታውጆብናል መግለጫ ማጠየቂያው በግልጽ ተቀምጧል) ከገጠር ወደ ከተማ የሚለውን መሠረታዊ መርህ ሽረናል ብለንም አልነበር። የከተማው ተኩስ የሀይል ሚዛን ሲለወጥም ተፋፍሞ መቀጠሉ ጉዳት ማድረሱን ድርጅቱ ራሱ በቋራ ሁለተኛው ጉባኤው አምኖ ግለሂስ የወሰደበት ሲሆንየመከላከል እርምጃ ግን ጥፋት ስህተት ነው ሊሉ የከጀሉት አንጃ ግራንጃዎችና የደርግ ወያኔ ቅጥረኞች ብቻ ናቸው። ዛሬም ቢሆን ለፍጅት ተዳርጎ በዘረኞች ሚታረደው ህዝብ ትጥቅ አንስቶ ራሱን መከላከል ይገባዋል ባይ መሆናችንን ሁሉም ሊያውቅ ይገባዋል።

ማንኛውም ሰው እናት አለው እንደተባለው ለአምባገእኖችም የሚወዷቸው እናቶች አሏቸው። ብርሃነ መስቀል ብዙ ቀና ጎኖች እንደነበሩት ሁሉ መጥፎ ጎኖችም ነበሩት። ራስ ወዳድና ራሱን አዳናቂ፤ የተክለሰውነት አምላኪ ስለነበርም በታሪክ ትልቅ ሰው ለመሆን ቦታ አለኝ ብሎ የሚያምን ነበር። በዚህም መሠረት የሕይወት ታሪኩን ለመጻፍ የሚረዱ ሰነዶችና መረጃዎችን ከሀገር ስንወጣ ይዞ ወጥቶ እንደነበር በቀጥታ አውቃለሁ። ብርህነ ማኦን ቻይና አግኝቶ ምክር እንደለገሳቸው (ቻይናም ሄዶ አየውቅም)፤ የሞዛምቢኩ ሳሞራ ማቬል ጋር ሆኖ ሞዛምቢክ እንደተዋጋ (በአልጄርስ ከነበሩ የአፍሪካ የነጻ አውጪ ድርጅት መሪዎች ጋር እንኳን ምንም ቀጥታ ግንኙነት አልነበረውም) ወዘተ ወዘተ የሀሰት ወሬ ይናፈስ ነበር። ዛሬ ካልካደች ባለቤቱም ብትሆን መጥፎ ዝንባሌ ነው ብላ ጽፋልኝ ነበር በቀጥታ። በአንጃነት ጌታቸው አልተሰለፈም ብላ ባሏን አዳንቃ ሚስትየዋ ብትጽፍም፤ ብርሃነ አብረው በአንጃነት መሰማራታቸውን አልደበቀም። ድርጅታችን ከመጀመሪያው የተክለ ሰውነት ጠር ነበርና (ከሰሜን ኮሪያም አንዱ ያራራቀን ጉዳይ ነው) ቻይና ማኦ ብለን የቻይና ጭፍን ተከታይ አልሆንም። ሟቹ ግለሰብ (መላኩ ተገኝ) የብርሃነ መስቀል ተክለ ሰብ አዳናቂና አምላኪ ነበር። ብርሃነ እንደ ተወርዋሪ ኮከብ ከረጅም ጊዜ በኋላ ሚታይ ብርቅ ነው ብሎም ጽፏል። የቱኒዝያ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንትን የቡርጊባን ዝና የመንግሥቱ ራዲዮ ሲያናፍስለት “በቱኒዝያ ህዝብ ዓለም ይቀናል–ምክንያቱም ሁለት ጸሃዮች ስላለን፤ አንደኛው በሰማይ ላይ ሁለተኛው በመሬት ላይ ያለን ቡርጊባችን” ይል የነበረውን ያስታውሰኛል። የሚስትየዋ እንኳን መቸስ ማል ጎደኒ፤ የሰውየው ግን ምን ይባላል!! ጸረ ተከለ ሰውነት በመሆናችንና በጋራ አመራርና ሀላፊነት አጥብቀን ስለምናምንም በድርጅታችን ውስጥ አምባገነን ወይም አዛዥ ሊሆኑ የከጀሉትን ሁሉ ታግለን አክሽፈናቸዋል። ለእኛ ዴሞክራሲ ቃል ሳይሆን መመሪያችን መርሃችን ነውና አድሃሪ ስርዓትን ልንዋጋ ልንሰዋ ቆርጠን እያለን በድርጅታችን ውስጥ ህግና አላማ እንጂ የግለሰብ ተገዢ ልንሆን አልተዋጠልንም። አልፎም ድርጅትን እንደ ጣኦት አናይም ያልነው በድርጅት በርክተናል። ቆምጨጭ አልን፤ አዛዥ ናዛዥ ነን፤ ወዘተ ብለው የተኮፈሱት ተወጥረውና ወጥረው ፈንድተው በጎዳናው ለመቅረታቸው ብዙ መረጃ አለን። ሟቹ አንዱ ምስክር ነው። ለአመራር ቦታ ሲታጭ የመበላሸት የመጀመሪያ እርምጃውን መውሰዱን የሚያውቁት ያውቃሉ። የኢሕአፓ አመራር ኮሚቴ አባሎች አብዛኞቹ በትግሉ ተሰልፈው ተሰውተዋል እንጂ ለሌላው ሂድ ሙት እዝና መርዝ ዋጥ ብለው ሰጥተው ከመስዋእትነት የሸሹ አይደሉም። በመሆኑም ነው ሟቾቹ በሙጣጭ ሊመለመሉ የቻሉት። በታሪክ አጋጣሚ ለአመራር ቦታም በመብቃታቸው ድርጅታችንን በውሳኔ ሊያፈርሱ ጥረው ለጥቂት እንዳሸነፍናቸው የምንዘረዝረው ይሆናል። ይቀጥላል …